ረጅሙ የመተላለፊያ ዋሻ በሜክሲኮና በአሜሪካ ድንበር ላይ ተገኘ

በዋሻው ውስጥ ያለ ሐዲድ

የፎቶው ባለመብት, CBP/REUTERS

ታትሟል

አሜሪካን ከሜክሲኮ ጋር በሚያዋስናት ድንበር በኩል ሰዎች በድብቅ የሚተላለፉበት ረጅም የምድር ውስጥ መተላለፊያ ዋሻ ማግኘታቸውን ባለስልጣናት አስታወቁ። መተላለፊያው እስካሁን ከተገኙት በርዝመቱ ቀዳሚው ነው ተብሏል።

መተላለፊያ ዋሻው ከአንድ ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው ሲሆን በውስጡ አሳንሰር፣ የመጓጓዣ ሐዲድ፣ የፍሳሽ መስመርና የአየር ማስተላለፊያ መስመሮች የተዘረጉለት ሲሆን በተጨማሪም ከፍተኛ መጠን ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸከሙ ገመዶችና የፀሐይል ኃይል መሰብሰቢያ ሳህኖችም በውስጡ ተገኝተዋል።

1 ሺህ 313 ሜትሮች ርዝመት እንዳለው የተነገረለት የመተላለፊያ ዋሻው ቲጁዋን የምትባለውን የሜክሲኮ የኢንዱስትሪ ከተማን ከአሜሪካዋ የካሊፎርኒያ ግዛት ሳንዴጎ አካባቢ ጋር የሚያገናኝ መሆኑን የአሜሪካ ባለስልጣናት ተናግረዋል።

የመተላለፊያ ዋሻው በተገኘበት ጊዜ የተያዘ ሰውም ሆነ አደንዛዥ ዕጽ የለም። ባለስልጣናትም ከዚህ ዋሻ ጋር በተያያዘ ማንን እንደሚጠረጥሩ ከመናገር ተቆጥበዋል።

ነገር ግን አሜሪካ በዓለም ትልቁ የዕጽ አዘዋዋሪ ቡድን እንደሆነ የምትናገርለት 'ሲናሎዋ' የተባለው ቡድን በአካባቢው እንደሚንቀሳቀስ ይነገራል።

የዚህ ቡድን መስራችና የረጅም ጊዜ መሪ ኤል ቻፖ ተብሎ የሚታወቀው ዮአኪን ጉዝማን አሜሪካ ውስጥ የእድሜ ልክ እስር ተፈርዶበት ዘብጥያ ይገኛል።

ስለመተላለፊያ ዋሻው መገኘት ይፋ የተደረገው አሁን ይሁን እንጂ፤ ዋሻው መጀመሪያ የተገኘው ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ሲሆን የሜክሲኮ ባለስልጣናት መግቢያውን ሲያገኙ የአሜሪካ መርማሪዎች ደግሞ መስመሩን ለይተው ደርሰውበታል።

መተላለፊያው ከመሬት በታች 21 ሜትር አማካይ ጥልቀት እንዳለው የአሜሪካ ጉምሩክና የድንበር ጥበቃ ተቋም የገለጸ ሲሆን ለመገንባት ምን ያህል ጊዜ እንደፈጀ የታወቀ ነገር የለም።

"የዚህ መተላላፊያ ዋሻ ዘመናዊነትና ርዝመት ድንበር ተሻጋሪ የወንጀል ቡድኖች ለተግባራቸው የሚያገለግል ማንኛውንም ነገር ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት ያሳያል" ሲሉ የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደህንነት ባለስልጣን የሆኑት ካርዴል ሞራንት ተናግረዋል።

ፕሬዝዳናት ዶናልድ ትራምፕ ሕገ ወጥ ስደተኞችንና የዕጽ አዘዋዋሪዎችን ለመግታት በሜክሲኮ ድንበር ላይ አጥር መገንባት ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ እንደሆነ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።

ነገር ግን ባለስልጣናት እንደሚሉት ወደ አሜሪካ የሚገባው አብዛኛው ዕጽ በግል ተሽከርካሪዎችና በጭነት መኪኖች ከሌሎች ነገሮች ጋር ተደባልቀው በሕጋዊ የመግቢያ በሮች በኩል ነው።

መርማሪዎች በዋሻው ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, CBP/REUTERS