የተባበሩት መንግሥታት ከእስራኤል 'ህገወጥ' ሰፈራ ጋር የተያያዙ ኩባንያዎችን ይፋ አደረገ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ድርጅት እስራኤል በኃይል የያዘቻቸው ዌስት ባንክ ግዛትና ምሥራቅ እየሩሳሌም ላይ ከምታደርገው ሰፈራ ጋር ንክኪ አላቸው ያላቸውን ኩባንያዎችን በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
ለረዥም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው ይህ ሪፖርት እስራኤል በምታደርገው ሰፈራ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳትፈዋል ያላቸው 112 ኩባንያዎችን ዝርዝር አውጥቷል።
ከነዚህም መካከል ኤይርቢኤንቢ፣ ቡኪንግ ዶት ኮም፣ ኤክስፒዲያ ግሩፕና ሞቶሮላ ሶሉሽንስ ይገኙበታል።
ሪፖርቱ ፍልስጤማውያንን "ለዓለም አቀፍ ህግ ድል ነው" በሚል ያስፈነደቀ ሲሆን እስራኤል በበኩሏ አሳፋሪ ብላዋለች።
እስራኤል በጎርጎሮሳውያኑ 1967 ምሥራቅ ኢየሩሳሌምና ዌስት ባንክ ግዛቶችን በኃይል ከተቆጣጠረች በኋላ 600 ሺህ የሚሆኑ እስራኤላውያንን በገነባቻቻቸው 140 በሚሆኑ የሰፈራ ቦታዎች አስፍራለች።
እነዚህ ሰፈራዎች በዓለም አቀፉ ህግ ዘንድ ሕገወጥ ቢባሉም እስራኤል ይህንን አትስማማበትም።
ፍልስጤማውያን በእነዚህ ግዛቶች ያሉ ሰፈራዎች እንዲቆሙም ቦታዎቹም እንዲነሱ የህልውና ጥያቄ በማንሳት ይከራከራሉ። በኃይል በተያዙት ቦታዎች ላይ ነፃ የፍልስጤም አገር ለመመስረትም መሰናክል ሆኗል ይላሉ።
ባለፈው ወር ዶናልድ ትራምፕ ለእስራኤልና ለፍልስጤም ቀውስ እልባት የሚያስገኝ ነው ባሉት እቅዳቸው የእየሩሳሌምን ባለቤትነት ለእስራኤል ከመስጠት በተጨማሪ በነዚህ ቦታዎች ላይ ያሉ ሰፈራዎችን የሚያበረታታ ነው ተብሏል።
በዚህ ሳምንትም የፍልስጤም ፕሬዚዳንት መሐሙድ አባስ የትራምፕን እቅድ ውድቅ ማድረጋቸውንና፣ ትራምፕ በእቅዱ ላይ ያካተቷት የወደፊቷ ፍልስጤምን ቀልድ እንደሆነችና ተጨምቃ የምትገባ ነው የምትመስለው በማለት በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጉባኤ ላይ ተናግረዋል።
የእስራኤሉ አቻቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው በመካከለኛው ምሥራቅ ላይ ከቀረቡ እቅዶች ምርጡ ነው ብለው ያሟካሹት ሲሆን፤ ለእስራኤልም ሆነ ለፍልስጤም መልካም ነገር ነው ብለዋል።
የሪፖርቱ ጭብጥ
በጎርጎሳውያኑ 2016 የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ መብት ጉባኤ የሰብዓዊ መብት ዋና ኮሚሽነርን እስራኤል ከምታደርጋቸው ሰፈራዎች ጋር ማንኛውም አይነት ንክኪ ያላቸውን ኩባንያዎችን ዝርዝር ጉዳዮች እንዲያቀርብ አዟል። ይህንንም ተከትሎ ሪፖርቱ ሊያጣራው ይገባል ብሎ ካዘዛቸው መካከል፦
- እስራኤል በያዘችው የዌስት ባንክ ግዛት ውስጥ ለሰፈራው ቦታ የሚሆን የግንባታ ቁሳቁሶችን ያቀረቡ
- በዚሁ ግዛት ውስጥ የነበሩ ቤቶችን፣ የእርሻ ቦታዎችን፣ አዝርዕቶችን እስራኤል ስታወድም ቁሳቁሶችን ያቀረቡ
- ለሰፈራው የሚውሉ መሰረተ ልማቶች ላይ የተሳተፉ፣ አሁንም የሚሳተፉ እንዲሁም ሰዎችን በማጓጓዝ የትራንስፖርት አገልግሎት የሰጡ እንዲሁም በመስጠት የቀጠሉ
- የባንክ አገልግሎቶችን የሚሰጡ በተለይም ሰፈራ ቦታዎች ላይ ለሚገነቡ ቤቶች ብድር ያመቻቹ
የሚሉ ሲሆን በኮሚሽኑም ግምገማ መሰረት 112 ኩባንያዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መሳተፋቸውን ይፋ አድርጓል።
በዝርዝሩ ከተካተቱት ውስጥ 94ቱ በእስራኤል ተቀማጭነታቸውን ያደረጉ ሲሆን አስራ ስምንቱ ደግሞ በአሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ሆላንድ፣ ሉክሰምበርግ፣ ታይላንድና እና እንግሊዝ የሚገኙ ናቸው።

"ምንም እንኳን በዓለም አቀፉ ሕግ መሰረት እነዚህ ሰፈራዎች ሕገወጥ ቢሆኑም ሪፖርቱ የእነዚህን ኩባንያዎች ተሳትፎ ሕገወጥ ነው በሚል አላስቀመጠውም፤ እንዲሁም ለግምገማው ሕጋዊ ማዕቀፍ አልተጠቀመም" በማለት ከኮሚሽኑ የወጣው መግለጫ ያስረዳል።
ከዚህ በመቀጠል ያለው ሂደት የሰብዓዊ መብት ጉባኤው አባላት የሆኑ አገራት ሥራ ነው ብሏል።
"ይህ ጉዳይ በከፍተኛ ደረጃ ሊያወዛግብ እንደሚችል እረዳለሁ" በማለት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሚሸል ባቸሌት ተናግረዋል።
የሪፖርቱ ምላሽ
የፍልስጤም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪያድ አል ማሊኪ "ከነዚህ ሰፈራዎች ጋር ንክኪ ያላቸው ኩባንያዎች በዝርዝሩ ውስጥ መካተት ለዓለም አቀፉ ሕግ ድል ነው" ብለዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም የሰብዓዊ መብት ጉባኤ አባላት ቀጣዩን እርምጃ እንዲያስቀምጡና የኩባንያዎቹም ፈቃድ እንዲሰረዝ ጠይቀዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኔታንያሁ በበኩላቸው ለሪፖርቱ መረር ባለ ቃል ምላሽ የሰጡ ሲሆን፤ በትዊተር ገፃቸውም "እግድ የጣለብን፤ ይታገዳል" በማለት "ይህንን ወራዳ ሥራ አንቀበለውም" ብለዋል።
አይሁዳውያንን የሚያሰፍረው የሻ ጉባኤ በበኩሉ ሪፖርቱን "ፀረ ሴማዊ" ነው ያሉት ሲሆን አክለውም "እነዚህ ኩባንያዎች የሃገሪቱን ኢኮኖሚን ለማጠናከር ሲሰሩ የነበሩ፤ እንዲሁም በአካባቢው ሰላም ለማስፈን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ ናቸው። በሰላም ላይ ያላቸው ተግባር የተባበሩት መንግሥታት ከሰራው በላይ ነው" ብለዋል።
ሂውማን ራይትስ ዋች በበኩሉ "ሕገወጥ ሰፈራ ላይ መሰማራት የጦር ወንጀሎችን ከማገዝ ጋር ስለሚያያዝ እነዚህ ኩባንያዎች ማስጠንቀቂያ ይገባቸዋል" ብሏል።
በዝርዝሩ ውስጥ የተካተቱት ኩባንያዎች አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።












