ዲሞክራቶች ቦልተን ከመሰከሩ 'የትራምፕ ጉድ ይፈላል' እያሉ ነው

ቦልተን ከመሰከሩ ትራምፕ ችግር ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ቦልተን ከመሰከሩ ትራምፕ ችግር ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ
ታትሟል

በዶናልድ ትራምፕ የክስ ሂደት ላይ ዲሞክራቶች በድጋሚ "ቦልተን ይመስክሩ" ማለት ይዘዋል።

የቀድመው የብሔራዊ ደኅንነት ሹምና የዶናልድ ትራምፕ አማካሪ ጆን ቦልተን ስለ ጉዳዩ በቅርብ የሚያውቁ ሰው ስለሆኑ እርሳቸው መጥተው ካልመሰከሩማ ምኑን ፍትሕ ነገሰ ብለዋል።

ዲሞክራቶች ይህንን ጥያቄያቸውን ከዚህ ቀደምም አቅርበው የነበረ ሲሆን በሪፐብሊካን አቻዎቻቸው ገሸሽ ሲደረግባቸው ቆይቷል።

አሁን በአዲስ መልክ ይህን ጥያቄ ማቅረባቸው ከቦልተን አዲስ መጽሐፍ ረቂቅ ጋር የተያያዘ ነው።

ቦልተን በቅርብ ያሳትሙታል በሚባለው መጽሐፋቸው ረቂቅ ውስጥ የቀድሞው አለቃቸው ዶናልድ ትራምፕ ለዩክሬን ሊሰጥ የነበረው የ400 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ለጊዜው ይቆይ ያሉት ዩክሬን በጆ ባይደንና ልጃቸው ዙሪያ ምርመራ እንድትጀምር ለማስገደድ ነበር የሚል ይገኝበታል።

ትራምፕ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ዚለንስኪ ላይ ጫና በመፍጠር ባይደን ላይ ምርመራ እንዲጀምሩ አስገድደዋቸው ነበር ብለው ከመሰከሩ ቦልተን ለዲሞክራቶች ትልቅ ውለታን እንደዋሉ ይቆጠራል።

ዶናልድ ትራምፕ በባለፈው ሳምንት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ቦልተን በዚህ የክስ ሂደት ምስክር ሆኖ እንዲቆጠሩ በፍጹም እንደማይፈልጉ ተናግረው ነበር።

ትራምፕ ጠቅላላ የክስ ሂደቱን "ቧልት" ሲሉ ያፌዙበታል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ከስልጣን ለማውረድ የተጀመረው እንቅስቃሴ ይሳካ ይሆን?

ባለፈው እሑድ ዝነኛው ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ካልታተመው የጆን ቦልተን የመጽሐፍ ረቂቅ የተወሰኑ አንቀጾችን ለሕትመት አብቅቶ ነበር።

አንቀጹ ትራምፕ 391 ሚሊዮን ዶላር የዩክሬን እርዳታ ለጊዜው እንዲዘገይ ማዘዛቸውን የሚናዘዝ ነው።

ይህ ኒው ዮርክ ታይምስ ያተመው አንቀጽ እውነት ከሆነ የትራምፕ ጠበቆች እያቀረቡ ያሉትን መሠረታዊውን ጭብጥ የሚንድ ይሆናል። የጠበቆቹ መሠረታዊ ጭብጥ ትራምፕ ከዩክሬን ጋር ለግል ጥቅማቸው ሲሉ የ"እከክልኝ ልከክልህ" ዓይነት ግንኙነት ውስጥ አልገቡም የሚል ነው።

የዲሞክራቶች ክሱ መሪ የሆኑት አዳም ሺፍ በትዊተር ገጻቸው ይህን ተከትሎ "ቦልተን ቢመሰክሩ የፕሬዝዳንቱን የመቃወሚያ ክስ ይንዱታል" ሲሉ ጽፈዋል።

የታችኛው ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፒሎሲ በበኩላቸው ቦልተን እንዳይመሰክሩ ለማድረግ መሞከር ሌላ ራሱን የቻለ ክስን ይሻል ብለዋል። "አሁን ምርጫው ሁለት ነው፤ ወይ ሕገ መንግሥቱን ማክበር፣ አልያም ወንጀልን ማለባበስ" ሲሉ ጽፈዋል።

እስካሁን በቦልተን ጉዳይ ከዋይት ሃውስም ሆነ ከቦልተን ጠበቆች የተባለ ነገር የለም።

በአሁኑ ጊዜ የዓለም ሚዲያ መነጋገሪያ የሆነው ቅዳሜ 'ለት የትራምፕን ምሥልና ድምጽ የያዘው ያፈተለከ ተንቀሳቃሽ ምሥል ነው። በዚህ ተንቀሳቃሽ ምሥል ትራምፕ በዩክሬን የአሜሪካ አምባሳደርን "አሁኑኑ አባሯት፤ ጉዳዬ አይደለም፤ አሁኑኑ! አሁኑኑ አባሩልኝ" እያሉ ሲናገሩ ይደመጣል።

ያም ሆነ ይህ እየተካሄደ ባለው የክስ ሂደት ሪፐብሊካኖች ከመቶ መቀመጫ 53 ያህሉን መያዛቸው የትራምፕ ከፕሬዝዳንትነት መባረር ግመል በመርፌ ቀዳዳ የማለፍ ያህል የማይመስል ነገር ሆኗል ይላሉ ፖለቲካ አዋቂዎች።