የፓርላማ አባሉ የምሽት ክበብ ሙዚቃ አጫዋቹን በጥይት መቱ

የኬንያ ፖሊስ ባቡ ኦዊኖ የተባሉ የሕዝብ እንደራሴ በምሽት መዝናኛ ክበብ ውስጥ ሙዚቃ አጫዋቹን በጥይት ከመቱ በኋላ በቁጥጥር ሥር እንዳዋላቸው አስታወቀ።
ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ ባይሰጥም በቦቢ አዊኖ የፌስቡክ ገጽ ላይ የሰፈረው ጽሑፍ የሕዝብ እንደራሴው በግለሰቦች ከተከበቡ በኋላ ራሳቸውን ለመከላከል ለመተኮስ ተገደዋል ይላል።
የገዢው መንግሥት ተቀናቃኝ የሆነው የኦሬንጅ ፓርቲ አባል የሆኑት ባቡ አዊኖ፤ "ተቀናቃኞቼ የግድያ ዛቻ እና ሙከራ እያዳረሱብኝ እንደሆነ ለፖሊስ በተደጋጋሚ ሪፖርት አድርጌያለሁ፤ አሁንም የተፈጠረው ከዚሁ ጋር የተገናኘ ነው። ብዛት ያላቸው የተቆጡ ወጣቶች ከበቡኝ። ከዚያም የተኩስ ልውውጥ ተደረገ" ይላል በሕዝብ እንደራሴው ተሰጥቷል የተባለው እና በፌስቡክ ገጻቸው ላይ የሰፈረው ጽሁፍ።
ባቡ አዊኖ ይህን ይበሉ እንጂ በምሽት መዝናኛ ክበብ ውስጥ የተቀረጸው የሲሲቲቪ ካሜራ ምስል ያሳየው የተለየ ነበር። ኬ24 የተባለው ቴሌቪዥን ያወጣው ተንቀሳቃሽ ምስል፤ የሕዝብ እንደራሴው በክበቡ ውስጥ ከጥቂት ሰዎች ጋር ሆነው ሺሻ እያጨሱ እየተዝናኑ ሳለ አንድ ወጣት ይጠጋቸዋል። ከዚያም ከቅርብ ርቀት በሽጉጥ መትተው ይጥሉታል።
ከሌላ ሲሲቲቪ ካሜራ የተገኘው ምስል ደግሞ፤ በጥይተ ተመትቷል የተባለውን ወጣት ሁለት ሰዎች እጅ እና እግሩን ይዘው ሲያወጡት ኬ24 አሳይቷል።
በጥይት የተመታው ወጣት ወደ ሆስፒታል ተወስዶ ህክምና እየተደረገለት የሚገኝ ሲሆን የደረሰበት የጉዳት መጠን ግን አልታወቀም።









