ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሊቢያ መንግስትና አማጺያን በሩሲያ ድርድር ጀመሩ
በሊቢያው የእርስ በርስ ጦርነት ለሁለት ተከፍለው እየተዋጉ የሚገኙት መንግስትና አማጺያን ከወራት ውጊያ በኋላ በሩሲያዋ ዋና ከተማ ሞስኮ ለድርድር ተቀምጠዋል።
በተባበሩት መንግስታት የሚደግፈው መንግስትና ለጀነራል ካሊፋ ሃፍታር ታማኝ የሆኑት ወታደሮች በዚሁ ድርድር የተኩስ አቁም ስምምነት እንደሚፈራረሙ ይጠበቃል።
ድርድሩ ባለፈው ሳምንት የሩሲያና የቱርክ መሪዎች በኢስታንቡል ያስጀመሩት ውይይት አካል መሆኑ ታውቋል።
የመጀመሪያው ዙር ስምምነት እሁድ የተጀመረ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች አንደኛው ሌላኛውን ስምምነቱን በመጣስ ተወነጃጅለዋል።
የድርድሩ መጀመር ምናልባትም በሊቢያ ጉዳይ ሩሲያና ቱርክ የአንበሳውን ድርሻ ለመውሰድ የሚያደርጉት እሽቅድድም ማሳያ ሊሆን እንደሚችል አንዳንድ ተንታኞች ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በሳምንቱ መጨረሻ የጀርመኗ መራሄ መንግስት አንጌላ መርክል የሩሲያና የቱርክን ጥረት ለመደገፍ በያዝነው ወር ላይ በሊቢያ ዙሪያ ውይይቶች እንደሚደረጉ ገልጸዋል።
ሩሲያ እስካሁን ባለው ሂደት ጀነራል ሃፍታር እና ወታደሮቻቸው ዋና ከተማዋ ትሪፖሊን ለመያዝ የሚያደርጉትን ጥረት የምትደግፍ ሲሆን ቱርክ ግን በዓለማቀፍ ደረጃ እውቅና ያለውን መንግስት ትደግፋለች።
ፕሬዚዳናት ሬሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን ፓርላማው ያሳላፈውን ውሳኔ ተከትሎ የቱርክ ወታደሮች ወደ ሊቢያ ማቅናት መጀመራቸውን ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው።
ወደ ሊቢያ ማቅናት የጀመሩት ወታደሮች ተልዕኮ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚደገፈውን የትሪፖሊ መንግስት አስተዳደር በመደገፍ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ነውም ብለዋል።
ከሩሲያ በተጨማሪ ጄኔራል ሃፍታርና ወታደሮቻቸው በግብፅ፣ ሳኡዲ አረቢያና እና በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የሚደገፉ ሲሆን በተባበሩት መንግስታት የሚደገፈው አስተዳደር ደግሞ በቱርክ እና ኳታር ይደገፋል።
ትሪፖሊን የሚያስተዳድረው መንግሥት የጀነራል ሃፍታር ወታደሮች ትሪፖሊን እንዳይቆጣጠሩ የመከላከል እርምጃዎችን ሲወስድ የቆየ ሲሆን በተለይ በደቡባዊ ወደ ትሪፖሊ በሚወስዱ አቅጣጫዎች ላይ የጀነራሉ ወታደሮች ብዙ ሽንፈቶችን ተከናንበዋል።