ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአንድ ቀን ልጇን በሞት የተነጠቀችው እና ሌላ የወለደችው እናት
በኢሉ አባ ቦራ ዞን ዲዱ ወረዳ ነዋሪ የሆነችው ኢንዲያ ሱሌይማን ታህሳስ 29 በገና በዓል ማግስት ምናልባትም በሕይወት ዘመኗ የማትረሳው ቀን ሊሆን ይችላል።
በዕለተ ረቡዕ ታህሳስ 29፣ 2012 ዓ.ም. የሁለት ዓመት ተኩል ልጇን በድንገተኛ ህመም በሞት የተነጠቀችበት እና ሌላ አዲስ ልጅ የወለደችበት ቀን ሆኖ አልፏል።
"ልጄ ከቀኑ ስምንት ሰዓት አካባቢ ድንገት ታሞብኝ ሃኪም ቤት ይዘነው ሄድን። ከአንድ ሰዓት በኋላ ሞተ። ወደ ቤት ከመለሱኝ በኋላ ምጥ አጣድፎኝ ምሽት ላይ ወለድኩኝ" ትላለች ኢንዲያ ሱሌይማን።
የመውለጃ ጊዜዋ መቃረቡን እንደምታውቅ የተናገረችው ኢንዲያ፤ "ከባድ ሃዘን ላይ ስለነበርኩ፤ ምጥ መጥቶብኝ ህመም ሲሰማኝ ኩላሊቴን ያመመኝ ነበር የመሰለኝ" ትላለች።
"በልጄ ሞት በጣም በሃዘን ስብሰለሰል ነበር" የምትለው ኢንዲያ፤ በዕለቱ ቤተሰብ እና ጎረቤት ሁኔታዋን ተመልክተው ወደ ህክምና ቦታ ሊወስዷት ቢጎተጉቷትም እርሷ ግን ኩላሊቷን እንዳመማት እንጂ ምጥ እንዳልሆነ ስትነግራቸው እንደነበረ ታስታውሳለች።
"ከዛ በቃ ምጤ መጣ፤ ወዲያው ቤት ወለድኩኝ" ትላለች ኢንዲያ።
"በሃዘኔ ቀን መውለዴ በጣም ግራ የሚያጋባ ስሜት ፈጥሮብኛል" በማለት የተሰማትን ትገልፃለች።
ሊጎበኟት ወደቤቷ የሚመጡ ሰዎችም የሞተውን ነብስ ይማር እንደሚሉ፤ የተወለደውን ደግሞ መርቀው እንደሚሄዱ ኢንዲያ ትናገራለች።
እሷ ግን "ምናልባት ይሄን ልጅ በማግኘቴ ወደፊት እደሰት ይሆናል እንጂ አሁን ለሞተው ልጄ ነው በጣም እያዘንኩ ያለሁት" ትላለች።
"ፈጣሪ አንዱን ነብስ በሌላ እንደተካ ነው ያመንኩት" ትላለች በድንገት የሞተባት ልጇ ሳይቀበር ሌላ ልጅ የመውለዷ ነገር የፈጠረባትን ስሜት ስትገልጽ።
የኢንዲያ እህት የሆነችው ለይላ ሱሌይማን ደግሞ "እኛ ቤተሰብ ውስጥ የፈጣሪን አስደናቂ ሥራ ተመልክተናል" ትላለች።
"በሞት ያጣነው ልጅ በሌላ ስለተካልን ለፈጣሪ ምስጋና እናቀርባለን። ሃዘን እና ደስታችን በአንድ ቀን መሆኑ ግን አሳዝኖናል። ምንም ነገር ጎደለ ወይም ተሟልቷል ብለን አንደሰትም ወይም አንከፋም የፈጣሪ ሥራን ብቻ እናደንቃለን" ብላለች።
ለይላ እንደምትለው ከሆነ፤ ጎረቤቶቻቸው ፈጣሪ ሌላ ልጅ ስለሰጣቸው ደስ ሊሰኙ እንጂ ሊያዝኑ እንደማይገባ እንደሚነግሯቸው ታስረዳለች።
ከኢንዲያ ቤተሰቦች እንደሰማነው ይህ ሲፈጠር የኢንዲያ ባለቤት በሥራ ምክንያት በአካባቢው አልነበሩም።