ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ በጫካ የሚያደርጉትን ጉዞ ጀመሩ
የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ 195 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን የስድስት ቀን የጫካ ውስጥ የእግር ጉዞ ጀመሩ።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ጉዞ የሚያደርጉት የቀድሞዎቹ ኢድ አሚንና ሚልቶን ኦቦቴ መውደቅን ተከትሎ እ.አ.አ. በ1986 ከወታደሮቻቸው ጋር ሆነው ስልጣን ለመያዝ ያደረጉትን ጉዞ ለማስታወስ ነው።
አንዳንድ ተቺዎች ግን ፕሬዝዳንቱ ቀጣይ ዓመት ለሚካሄደው ምርጫ ለስድስተኛ ጊዜ ለመወዳደር እንደ መቀስቀሻ ጥቅም ላይ ለማዋል የተደረገ ተራ የፖለቲካ ጨዋታ ነው ብለዋል።
የኡጋንዳው ታዋቂ ሙዚቀኛ ቦቢ ዋይንም ፕሬዝዳንቱን ከሚቃወሙት ሰዎች ቀዳሚው ነው።
ሙሴቪኒ ጉዟቸውን የሚያጠናቅቁት በምዕራባዊ የሀገሪቱ ክፍል በምትገኘው ቢሬምቦ ሲሆን ይህች ከተማ ከወቅቱ ፕሬዝዳንት ኦቦቴ ጋር ከባድና በርካቶች ህይታቸውን የገበሩበት ውጊያ ተካሂዶባታል።
የፕሬዝዳንቱ ፕሬስ ሴክረተሪ ዶን ዋንያማ ደግሞ የፕሬዝዝዳንቱን ጉዞ '' የአሁኑን ለማድነቅ የኋላውን መቃኘት ላይ ያነጣጠረ ነው'' በማለት ገልጸውታል።
ሙሴቪኒ በአፍሪካ በስልጣን ላይ ረጅም ዓመታትን ካስቆጠሩ መሪዎቹ መካከል ናቸው።
ሙዚቀኛው ቦቢ ዋይን ወይም በዋና ስሙ ሮበርት ክያጉልያኒ 'ከኤኤፍፒ' የዜና ወኪል ጋር በነበረው ቆይታ ፕሬዝዳንቱ 'ኪሳራ' ናቸው ሲል ገልጿቸዋል።
'' ከህዝቡ በታክስ የተሰበሰበ ገንዘብን ለእንደዚህ አይነት ጉዞዎች ከማዋል ይልቅ አርፎ ስልጣኑን ቢለቅ ይሻለዋል'' ብሏል።