ማይክል ጃክሰን ፈፅሞታል ለተባለው ጥቃት ድርጅቶቹ እንዲከሰሱ ፍርድ ቤት ወሰነ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በእውቁ አሜሪካዊ አቀንቃኝ፣ የዘፈን ግጥም ፀሐፊ እና ዳንሰኛ ማይክል ጃክሰን ወሲባዊ ጥቃት ደርሶብናል ላሉ ሁለት ግለሰቦች፤ እሱ በሕይወት ባይኖርም ያሉትን ሁለት ድርጅቶች መክሰስ እንደሚችሉ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ።
ዋዴ ሮብሰን እና ጀምስ ሴፍቻንክ በ80ዎቹ እና በ90ዎቹ መጀመሪያ በአቀንቃኙ መኖሪያ ቤት 'ኔቨርላንድ' በቆዩበት ወቅት ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።
ሮብሰን እና ሴፍቸንክ በጊዜው ከሰባት እስከ አስር ዓመት የእድሜ ክልል ላይ ይገኙ እንደነበር ገልፀዋል።
በአውሮፓዊያኑ 2009 ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው የማይክል ጃክሰን ቤተሰቦች ግን ክሱን ተቃውመውታል።
በአውሮፓዊያኑ 2019 በእንግሊዝ ፊልም ሰሪ የተዘጋጀውን እና በአቀንቃኙ ጥቃት ተፈፅሞብናል ባሉት ሁለቱ ግለሰቦች ታሪክ ላይ የሚያጠነጥነውን ዘጋቢ ፍልም 'ሊቪንግ ኔቨርላንድ'ንም "የጅምላ ፍርድ" ነው ሲሉ ገልፀውታል።
በካሊፎርኒያ በፀደቀው ሕግ መሠረት በልጅነት ወቅት የወሲብ ጥቃት የደረሰበት አንድ ግለሰብ ክስ ማቅረብ የሚችለው 26 ዓመት ሳይሆነው/ናት በፊት ነው በሚለው ሕግ መሠረት፤ 2014 ላይ በሁለቱ ግለሰቦች የቀረበውን ክስ ፍርድ ቤት ውድቅ አድርጎት ነበር።
በወቅቱ ክሱ ወድቅ ቢደረግም እንኳን፤ በጥር ወር ተግባራዊ የተደረገው አዲሱ ሕግ ግለሰቦች እስከ 40 ዓመታቸው ድረስ በልጅነታቸው ለደረሰባቸው ጥቃት ክስ መመስረት እንደሚችሉ ፈቅዷል።
የሁለቱ ግለሰቦች ጠበቃ ቪንስ ፊንላንዲ፤ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ "ፍርድ ቤቱ ጥቃት ለደረሰባቸው ተጎጂዎች ፍትሕ ለመስጠት በካሊፎርኒያ ሕግ ላይ የተቀመጠውን የዕድሜ ወሰን ከግምት በማስገባቱ በጣም ደስተኞች ነን" ብለዋል።
የማይክል ጃክሰን ድርጅቶች ጠበቃ ሆዋርድ ዌትዝማን በበኩላቸው "ፍርድ ቤቱ በማይክል ጃክሰን ድርጅቶች ላይ ክስ እንዲመሠረት የሰጠው ትዕዛዝ፤ የማይክል ጃክሰን ድርጅት ሠራተኞችን ባልተፈፀመ ጥቃት ተጠያቂ የሚያደርግ ነው" ሲሉ ተቃውመውታል።















