''ጠጥታችሁ አታሽከርክሩ" ያሉት ፖለቲከኛ ጠጥተው ሲያሸከረክሩ ተጋጩ

ሪፐብሊካኑ ብራይንል ኮለበ

የፎቶው ባለመብት, Ontario County Sheriff's Office

የምስሉ መግለጫ, ሪፐብሊካኑ ብራይንል ኮለበ
ታትሟል

አሜሪካዊው ፖለቲከኛ አምደኛ በሆኑበት ጋዜጣ ላይ ሰዎች ጠጥተው እንዳያሽከረክሩ ከጻፉ በኋላ፤ ጠጥተው ሲያሽከርክሩ ተይዘዋል።

ብራይንል ኮለበ የተባሉት ሪፐብሊካን በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ ኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ ጠጥተው ሲያሽከረክሩ ተጋጭተዋል ብሏል ፖሊስ።

ይህ ከመሆኑ ከአንድ ሳምንት በፊት ፖለቲከኛው ብራይን፤ በጋዜጣ ላይ ባሳተሙት ጽሁፍ ሰዎች በምንም አይነት ጠጥተው ማሽከርከር እንደሌለባቸው ጽፈው ነበር። ከአንድ ሳምንት በኋላ እርሳቸው ጠጥተው ሲያሸከረክሩ ከግዑዝ ነገር ጋር ተጋጭተው በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

የ67 ዓመቱ ፖለቲከኛ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ በሰጡት ቃል "እጅግ በጣም ይቅርታ'' ብለዋል።

"ማክሰኞ ምሽት ለተፈጸመው ነገር ምንም አይነት ማስተባበያ እና ምክንያት ላቀርብ አልችልም። የወሰደኩት እርምጃ ስህተት ነው። ለዚህም በጣም ተጸጽቻለሁ" ብለዋል ፖለቲከኛው።

ፖሊስ እንዳለው ፖለቲከኛው መንግሥት የሰጣቸውን መኪና ከውሃ ማስወገጃ ቱቦ ጋር አጋጭተዋል።

ፖለቲከኛው አደጋው በደረሰበት ወቅት እና ፖሊስ ጣቢያ ከደረሱ በኋላ የተደረገላቸውን የአልኮል ምርመራ ማለፍ አልቻሉም።

ብራይን ኮለብ ሪፐብሊካኖችን ወክለው ከሚያደርጉትን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ራሳቸውን እንዲያገሉ በተለያዩ አካላት እየተጠየቁ ነው።