በሱዳን የጦር አውሮፕላን ተከስክሶ ቢያንስ 18 ሰዎች ሞቱ

ታትሟል

የሱዳን የጦር አውሮፕላን ምዕራብ ዳርፉር ባጋጠመው የመከስከስ አደጋ ቢያንስ የ18 ሰዎች ሕይወት አለፈ። ከእነዚህ መካከል አራቱ ሕፃናት ናቸው።

አንቶኖቭ 12 የተሰኘው የጦር አውሮፕላኑ፤ በምዕራብ ዳርፉር ግዛት ዋና ከተማ ኤል ጀኔይና አየር ማረፊያ ከተነሳ ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ነበር የተከሰከሰው።

የጦር አውሮፕላኑ በቅርቡ በአካባቢው የሰዎች ሕይወት ያለፈበትን የብሔር ግጭት ተከትሎ የእርዳታ ቁሳቁሶችን ለማድረስ ነበር ጉዞ የጀመረው።

የጦሩ ቃል አቀባይ አመር መሀመድ አል ሃሰን ለኤ ኤፍ ፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት፤ ሰባት የበረራ ቡድን አባላት፣ ሦስት ዳኞች እና ስምንት መንገደኞች በአደጋው ሕይወታቸው አልፏል። ከመንገደኞቹ መካከልም አራቱ ህፃናት ናቸው።

የአደጋው መንስኤ አለመታወቁን እና ምክንያቱን ለማጣራት ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ቃል አቀባዩ አክለዋል።

በዚህ ሳምንት በሱዳን ምዕራብ ዳርፉር በተቀሰቀሰ ግጭት ቢያንስ 48 ሰዎች ሲገደሉ 241 የሚሆኑት ጉዳት እንዳጋጠማቸው የሱዳን ቀይ ጨረቃ የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት አስታውቋል።

በምዕራብ ዳርፉር ዋና መዲና ኤል ጀኔይና ባለፈው እሁድ በአረቦችና በአፍሪካዊያን ቡድኖች መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት እስከ ሁለተኛው ቀን ድረስ የዘለቀ ነበር።