ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጀርመን ከፍተኛ የናዚ ኃላፊ የነበረ ግለሰብ መቃብር ተከፍቶ ተገኘ
በጀርመን መዲና በርሊን የናዚ ከፍተኛ አመራር የነበረው ሬይንሃርድ ሄድሪክ መቃብር ተከፍቶ መገኘቱን ፖሊስ አስታወቀ።
ፖሊስ በቼኮስሎቫኪያ ሰላይ እአአ 1942 የተገደለው ሬይንሃርድ ሄድሪክ፤ ስለ ማንነቱ ምንም ያልተፃፈበት መቃብሩ ተከፍቶ ተገኝቷል ብሏል።
የመቃብር ስፍራው ሰራተኛ ነበር ባሳለፍነው ሐሙስ ጠዋት መቃብሩ ተከፍቶ የተመለከተው።
ፖሊስ መቃብሩን የከፈተውን ግለሰብ እየፈለገ እንደሆነ ያስታወቀ ሲሆን፤ የሟች አጥንት ግን አለመነካቱን አስታውቋል።
በናዚ በአውሮፓ የሚገኙ የአይሁዶችን ግድያ ካቀነባበሩ ኃላፊዎች መካከል ሄድሪክ ተጠቃሹ ነው።
እአአ 1942 ላይ 'ዋንሴ' ተብሎ በሚታወቀው ኮንፍረንስ የሂትለር የጅምላ ግድያ እቅድ የወጣበትን ስብሰባ የመራው ሄድሪክ ነበር።
የመቃብር ስፍራን ጸጥታ ማደፍረስ ወይም መቃብርን ማፈራረስ እና መቆፈር በጀርመን በሕግ ያስጠይቃል።
የናዚ ደጋፊ ወይም አድናቂ የሆኑ ሰዎች የናዚ የመቃብር ስፍራዎችን የአምልኮ ቦታ እንዳያደርጉት ወይም የናዚ ጥላቻ ያላቸው ሰዎች መቃብሮቹን እንዳያወድሟቸው በማሰብ የናዚ አባላት የመቃብር ስፍራ ምንም ምልክት አይደረግባቸውም። ስምም ሌላም መረጃ ጭምር።
የሄድሪክን መቃብር የከፈተው ግለሰብ ግን መቃብሩ የማን እንደሆነ ያውቅ ነበር ተብሏል።
"ጨካኙ ገዳይ" ተብሎ የሚታወቀው ሄድሪክ፤ ከናዚ ጦር አዛዥ ሄኔሪክ ሂምለር ሥር ሆኖ ለአጠቃላይ የናዚ አስተዳደር የደህንነት ኦፊሰር ሆኖ ሰርቷል። አዶልፍ ሂትለር ሄድሪክን "ባለ ብረት ልቡ ሰው" እያለ ይጠራው ነበር።
ሁለት የቼክ ሪፓብሊክ ግዛቶቸን ያስተዳደረው ሄድሪክ፤ እግሊዞች ያሰለጠኑት የቼኮስላቫኪያ ሰላይ ሄድሪክ መኪናው ውስጥ እያለ ጥቃት ከሰነዘረበት በኋላ ባጋጠመው ጉዳት ህይወቱ አልፏል።
በአጸፋውም ናዚዎች ሊዲስ ተብላ በምትጠራ መንደር ውስጥ የሚገኙ እድሜያቸው ከ15 ዓመት በላይ የሆኑ ወንዶችን በሙሉ የገደሉ ሲሆን ሴቶች እና ህጻናትን ደግሞ የጅምላ ግድያ ወደሚፈጸምባቸው ማጎሪያ ስፍራ ወስደዋል።