በኒጀር ታጣቂዎች 73 ወታደሮችን ገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ታትሟል
በኒጀር ታጣቂዎች በአንድ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ በፈጸሙት ጥቃት ቢያንስ 73 ወታደሮች መገደላቸውን ባለስልጣናት አስታወቁ።
ጥቃቱ የተፈጸመበት ካምፕ ለማሊ ድንበር ቅርበ ሲሆን የትኛውም ቡድን ከጥቃቱ ጀርባ ስለመሆኑ አላስታወቀም። ነገር ግን በናይጄሪያ መሰረቱን ያደረገው የቦኮ ሃራም ኢስላማዊ ቡድን ተዋጊዎች በአካባቢው ስለሚንቀሳቀሱ ጥቃቱን የፈጸሙት እነሱ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተገምቷል።
የዚህ ጥቃት ዜና የሀገሪቱ መንግስት ታውጆ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሶስት ወራት ለማራዘም ሃሳብ ካቀረበ በኋላ ነው። በኒጀር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታወጀው ከሁለት ዓመታት በፊት መሆኑ ይታወሳል።
የኒጀር የጸጥታ ኃይሎች በሃገሪቱ በብዛት የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ቡድኖችን መቆጣጠር ተስኖታል።
በሀገሪቱ የሚገኙ የደህንነት ባለሙያዎች እንደገለጹት እንደዚህ አይነት ጥቃቶች በኒጀር እየተበራከቱና አሳሳቢ በሚባል ደረጃ ላይ ደርሰዋል።
በቅርብ ሳምንታት ከማሊ ድንበር የሚነሱ የቦኮ ሀራም ታጣቂዎች በተለያዩ የኒጀር ክፍሎች በነጻነት ሲንቀሳቀሱና ለበርካታ ሰዎች ህይወት ማለፍ ምክንያት የሆኑ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ተስተውሏል።
ኒጀር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገር ውስጥ ግጭቶች ስትታመስ የቆየች ሲሆን ይህም ሰርገው በገቡ የእስላማዊ ቡድኖች ቆስቋሽነት መሆኑ ይነገራል።













