ናይጄሪያ፡ የፕሬዝዳንቱ ሚስት ስለማህበራዊ ሚዲያዎች የሰነዘሩት ሃሳብ አነጋጋሪ ሆነ

ታትሟል

የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት አቡባከር ቡሐሪ ባለቤት ቀዳማዊ እመቤት አይሳ ቡሐሪ ማህበራዊ ሚዲያዎች ቁጥጥር እንዲደረግባቸው ጥሪ ማቅረባቸው ቁጣን ቀሰቀሰ።

በዚህም ሳቢያ በርካታ ናይጄሪያዊያን በተለያዩ የኢንተርኔት መድረኮች ላይ ቀዳማዊት እመቤቷ የሰነዘሩትን ሃሳብ በመቃወም ቁጣቸውን እየገለጹ ነው።

ቀዳማዊት እመቤት አይሻ ባለፈው ሳምንት ማብቆያ ላይ በተሳተፉበት የናይጄሪያ እስላማዊ ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትና በብሔራዊው ሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር የማህበራዊ ሚዲያዎች ከቁጥጥር ውጪ ከመሆናቸው በፊት የሚገዛቸው ደንብ ሊበጅላቸው ይገባል ብለዋል።

ቀዳማዊት እመቤቷ ናይጄሪያን በሕዝብ ብዛት በከፍተኛ ደረጃ ከምትበልጣት ቻይና ጋር በማነጻጸር፤ አገራቸው ማህበራዊ ሚዲያዎችን መቆጣጠር መቻል አለባት ሲሉ ተናግረዋል።

"ከማህበራዊ ሚዲያዎች አንጻር ቻይና 1.3 ቢሊየን ሕዝቧን መቆጣጠር ችላለች። ስለዚህ 180 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ናይጄሪያ ቁጥጥር ለማድረግ የማያስችላት ምክንያት የለም።"

ቀዳማዊት እመቤቷ አክለውም "ቀበቷችንን ጠበቅ አድርገን አስፈላጊ የሆነውን ነገር ለማድረግ መነሳት ካልቻልን ይህንን ባለማድረጋችን በቅርቡ ጸጸት ይጠብቀናል" ብለዋል።

ቀዳማዊት እመቤት አይሻ ይህንን ንግግር ያደረጉት ማህበራዊ ሚዲያዎችን በተመለከተ ለናይጄሪያ ምክር ቤት ረቂቅ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ባለበት ወቅት ነው።

የማህበራዊ መገናኛ ብዙኀንን የሚጠቀሙ ናይጄሪያዊያን ግን ቀዳማዊት እመቤቷ አገራቸውን ከቻይና ጋር በማነጻጸር ያቀረቡትን ሃሳብ በጽኑ ተቃውመውታል።