'ዳርክ ዌብ' የህፃናት ጥቃት፡ በ38 አገራት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ታሰሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዓለማችን ትልቅ ከሆኑት የህፃናት የወሲብ ፊልም መሸጫ ድረ ገፆች 'ዳርክ ዌብ' ሳቢያ ከ300 በላይ ሰዎች መታሰራቸውን መርማሪዎች አስታወቁ።
ድረ ገፁ ከ200 ሺህ በላይ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን የያዘ ሲሆን ከሚሊየን ጊዜ በላይ ምስሎቹ ዳውንሎድ ተደርገዋል [ወርደዋል]።
እንግሊዝ በህፃናት ወሲብ ላይ ባደረገችው ምርመራ ድረ ገፁ የተዘጋው ባለፈው ዓመት ነበር። ባሳለፍነው ረቡዕም ከ38 የዓለማችን አገራት 337 የድረ ገፁ ተጠቃሚዎች መታሰራቸውን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት አሁን በእስር ላይ የሚገኘውንና የ23 ዓመቱን የድረ ገፁን ባለቤት ጆንግ ው ሰን ላይ ዘጠኝ ክሶችን አቅርበዋል።
የእንግሊዝ ብሔራዊ የወንጀል ምርመራ ኤጀንሲ እንዳለው ከ38 የዓለማችን አገራት መካከል በእንግሊዝ፣ አየርላንድ፣ አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጀርመን፣ ስፔን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ቼክ ሪፐብሊክና ካናዳ እስሮች ተፈፅመዋል።
'ዌል ካም ቱ ዘ ቪዲዮ' የተሰኘው ድረ ገፁ፤ ከደቡብ ኮሪያ የሚሠራጭ ሲሆን የህፃናት ጥቃትን ጨምሮ ስምንት 'ቴራ ባይት' የሚሆን ምስሎችን ይዟል። ድረ ገፁ በመቶዎች አሊያም በሺህዎች ሰዓት የሚለኩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን የመያዝ አቅም አለው።
አቃቤ ሕግ እንዳለው ድረ ገፁ በጨቅላ እድሜ ላይ ያሉት ሳይቀሩ ህፃናት የተሳተፉበት የወሲብ ፊልም የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች አስተላልፏል።
ድረ ገፁ ተጠቃሚዎች በገፁ ላይ አዋቂዎችን የተመለከተ ተንቀሳቃሽ ምስል [ቪዲዮ] እንዳይጭኑ ይጠይቃል- የወሲብ ፊልሞችን ብቻ እንዲጭኑ በማሳሰብ።
የእንግሊዝ ብሔራዊ የወንጀል ምርመራ ኤጀንሲ "በጣም የሚያሳምሙ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለሽያጭ የሚያቀርብ አንደኛው ድረ ገፅ ነው" ያለው ይህ ድረ ገፅ፤ የእንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጀርመን ተቋማትን ጨምሮ በዓለም አቀፉ የለውጥ ኃይል አማካኝነት ለሦስት ዓመታት ሥራ ላይ የነበረው ድረ ገፅ ተዘግቷል።
ድረ ገፁ የተገኘው 'በዳርክ ዌብ' የህፃናት ወሲባዊ ጥቃትን የተመለከቱ ነጥቦችና ምስሎችን በማጋራት ለ25 ዓመታት የታሰረው እንግሊዛዊው ማቴው ፋልደር ላይ ምርመራ ሲካሄድ ነበር።
በእንግሊዝ የ5 ዓመት ወንድ ህፃን ልጅን በመድፈር እና የ3 ዓመት ህፃን ልጅ ላይ ወሲባዊ ጥቃት በመፈፀም ለ22 ዓመታት ታስሮ የነበረውን ክይሌ ፎክስን ጨምሮ ሰባት ወንዶች በዚህ ምርመራ ጥፋተኛ ተብለዋል።
የወንጀል ምርመራ ቡድኑ 'ክሪፕቶከረንሲ' [ዲጂታል ከረንሲ] የገንዘብ ማስተላለፊያ ድረ ገፅ ላይ ባደረገው ክትትል ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ሊውሉ ችለዋል።
23 የሚሆኑ ህፃናትም ሊደርስባቸው ከነበረው ወሲባዊ ጥቃት መትረፍ መቻላቸውን የጥምር የለውጥ ኃይሉ በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ገልጿል።
የምርመራ ቡድኑም ሌሎች በተንቀሳቃሽ ምስሎቹ ላይ የሚታዩ ህፃናትን ማፈላለጉን ቀጥሏል።
" 'ዳርክ ዌብ' የህፃናት የወሲብ ፊልም አስተላላፊዎች ከሕግ ሊያመልጡ አይችሉም " ሲሉ የእንግሊዙ የወንጀል ምርመራ ኤጀንሲ መሪ ኒክኪ ሆላንድ ተናግረዋል።












