ዴቪድ ኢስትማን፡ ለ19 ዓመታት በስህተት የታሰሩት አውስትራሊያዊ ነፃ ወጡ

የፎቶው ባለመብት, AAP
አውስትራሊያዊው የፖሊስ ኃላፊን በመግደል ተወንጅለው በስህተት ለ19 ዓመታት በእስር ያሳለፉት ግለሰብ የ4.8 ሚሊየን ዶላር [7 ሚሊየን የአውስትራሊያ ዶላር] ካሳ ተከፈላቸው።
ግለሰቡ ዴቪድ ኢስትማን ኮሊን ዊንቸስተር የተባሉ የአውስትራሊያ ፌደራል ፖሊስ ረዳት ኮሚሽነርን በመግደል ተወንጅለው እድሜ ይፍታህ የተፈረደባቸው በጎርጎሳውያኑ 1995 ነበር።
ፍርድ ቤቱ ባለፈው ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ በዋለው ችሎት ግለሰቡ ላይ የተላለፈው ውሳኔ 'ፍትሃዊ አይደለም' ሲል በነፃ እንዲወጡ ትዕዛዝ ካስተላለፈ በኋላ ከእስር ተለቀዋል።
የ74 ዓመቱ ዴቪድ ቀደም ሲል ከአውስትራሊያ ካፒታል ቴሪተሪ (ACT) መንግሥት 3.8 ሚሊየን የአውስትራሊያ ዶላር ካሳ የቀረበላቸው ሲሆን አልቀበልም ብለው ነበር።
ቀደም ባለው ጊዜ ኤ ሲ ቲ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት ዴቪድ ለእስር በመዳረጋቸው ምክንያት ቤተሰብ መመስረት እና ሥራ የማግኘት እድል እንዳጡ አስረድተዋል። በእስር ላይ በነበሩበት ጊዜም እናታቸውንና ታናናሽ እህት ወንድሞቻቸውን በሞት እንዳጡ ተናግረዋል።
ጠበቃቸው ሳም ቲርኒይ ከችሎቱ በኋላ "የሕይወታቸውን መሠረት ነው ያጡት" ሲሉ ተናግረዋል።
የኮሚሽነሩ ኮሊን ግድያ በአውስትራሊያ ያለውን የሕግና የፖለቲካ ሁኔታ ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ሲሆን፤ በአገሪቷ ከተደረጉ ከፍተኛ የወንጀል ምርመራዎች አንዱ ነበር። ግድያው ግን አሁንም እንቆቅልሽ እንደሆነ ነው።
ረዳት ኮሚሽነሩ ኮሊን፤ በአገሪቷ መዲና በካንቤራ በቤተሰቦቻቸው መኖሪያ ቤት አቅራቢያ ሁለት ጊዜ ጭንቅላታቸው ላይ ተመትተው ነበር ሕይወታቸው ያለፈው። በአውስትራሊያ ውስጥ ከተፈፀሙ ግድያዎች ከፍተኛ የፖሊስ ኃላፊ ላይ ሲፈፀም የመጀመሪያው ነውም ተብሏል።
ዴቪድ በግድያው የተጠረጠሩት ቀደም ብሎ የተፈፀመ የግድያ ምርመራን በተመለከተ በተደጋጋሚ ለፖሊስ የሚያስፈራራ መልዕክት ይልኩ ስለነበር ነው።
ለእስር ከተዳረጉ በኋላም ድርጊቱን እንዳልፈፀሙ ሲከራከሩ 19 ዓመታት ነጎዱ፤ በተለያዩ ዓመታት ለአምስት ጊዜ ያህል ይግባኝ ቢጠይቁም ሰሚ ሳያገኙ ቆይተዋል።
ባለፈው ዓመት 100 የዐይን ምስክሮችን ባካተተ መልኩ ለሁለተኛ ጊዜ በዋለው ችሎት ነፃ ሊወጡ ችለዋል። ግለሰቡ በነፃ መለቀቃቸውን ተከትሎ ወዲያውኑ ስለ ካሳ ክፍያቸው ያላቸውን ቅሬታ አሰምተዋል።















