ብሪጊድ ኮስጌ በፓውላ ራድክሊፍ ተይዞ የነበረውን የሴቶች ማራቶን ሪከርድ ሰበረች

አትሌት ብሪጊድ ኮስጌ የሴቶች ማራቶን አዲስ ሪከርድ አስመዘገበች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ትናንት በቺካጎ በተካሄደው የሩጫ ውድድር ኬንያዊቷ ብሪጊድ ኮስጌ በእንግሊዛዊቷ ፓውላ ራድክሊፍ ተይዞ የነበረውን የዓለም የሴቶች ማራቶን ሪከርድ ሰበረች።

የ25 ዓመቷ አትሌት 2፡14፡04 ሰከንድ ውድድሯን በማጠናቀቅ ነበር ሪከርድ የግሏ ያደረገችው።

በአውሮፓዊያኑ 2003 በለንድን በተካሄደው ውድድር እንግሊዛዊቷ ፓውላ 2፡ 15፡ 25 በማጠናቀቅ ለዓመታት ሪከርዱን ይዛ ቆይታለች።

ብሪጊድ በዚህ ዓመት በለንደን በተካሄደው ውድድር ላይም 2፡ 18፡ 20 ሰኮንዶች በማጠናቀቅ በውድድሩ ወጣቷ አሸናፊ መሆን ችላ ነበር።

በችካጎው ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አባበል የሻነህ ስድስት ደቂቃ ከ47 ሰኮንድ ዘግይታ በመግባት ውድድሩን በሁለተኛነት አጠናቃለች።

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ገለቴ ቡርቃም በ2፡20፡51 ሰከንድ በመግባት ሦስተኛ ደረጃነትን ይዛለች።

ባለፈው ዓመት 2፡18፡35 በማጠናቀቅ ያሸነፈችው ብሪጊድ "ጥሩ ስሜት ነው ያለኝ፤ ደስም ብሎኛል፤ ምክንያቱም በዚህ መልኩ ውድድሬን አጠናቅቃለሁ ብዬ አልጠበቅኩም ነበር" ብላለች።

በወንዶች ውድድር በብሪጊድ ሰዓት ፈጥነው ወድድራቸውን ያጠናቀቁት 22 ሯጮች ብቻ ሲሆኑ እርሷ ያስመዘገበችው ሰዓት በጎርጎሳውያኑ 1964 በወንዶች ተይዞ የነበረ ሪከርድ ነበር።

በዚሁ በችካጎ በተደረገው ውድድር የቀድሞዋ የዓለም ሻምፒዮና ፓውላ፤ የአትሌቷን አጨራረስ ለመመልከት በመጨረሻ መሙ ላይ የነበረች ሲሆን 'እንኳን ደስ አለሽ' ለማለትም የመጀመሪያዋ ሆናለች።

"በመጀመሪያዎቹ ግማሽ ሰዓታት እንዴት በፍጥነት እንደምትሮጥ ስመለከታት፤ ሪከርዱን መስበር እንደምትችል አወቅኩ" ብላለች ፓውላ።