አውስትራሊያዊቷ ድምፃዊት ሲያ በከባድ ሕመም እየተሰቃየች ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አውስትሪያላዊቷ ድምፃዊት ሲያ በከባድ በመገጣጠሚያ ሕመም እየተሰቃየች መሆኑን ገለፀች። ሲያ ለአድናቂዎቿ በቲዊተር ገጿ ላይ በከፍተኛ ሕመም ውስጥ እየተሰቃየች መሆኑን ተናግራለች።
ድምፃዊቷ እያሰቃያት ያለው በሽታ ኢዲኤስ የሚባል መሆኑን ለተከታዮቿ ይፋ አድርጋለች። ኢዲኤስ (Ehlers-Danlos Syndrome) በጣም ጥቂት ሰዎችን ብቻ የሚያጠቃ በሽታ ሲሆን ከባድ የመገጣጠሚያ ሕመምና፣ የሚያዝል ድካምን ያስከትላል።
የ43 ዓመቷ ሲያ ስለግል ሕይወቷ ብዙም መናገር የማትወድ ስትሆን በምታቀነቅንበት ወቅትም ፊቷን በረዥም ዊግ በመሸፈን ትታወቃለች።
ድምፃዊቷ በአድናቂዎቿ የተወደዱላት በርካታ ሥራዎች አሏት። ከእነዚህም መካከል ሻንድሊር፣ ኢላስቲክ ሀርት፣ ኔቨር ጊቭ አፕ እና ቺፕ ትሪልስ የሚባሉ ሥራዎቿ ዝናን አጎናፅፋዋታል።
ከዚህም ባሻገር ለሪሃና፣ ቢዮንሴ፣ ኬቲ ፔሪና አዴል እንዲሁም ላየን፣ ፊፍቲ ሼድስ ዳርከር፣ ፋይንዲንግ ዶሪ እንዲሁም የሌሎች ፊልሞችም ማጀቢያ ሙዚቃ ደርሳለች።።
"ማለት የምፈልገው በአካላዊም ሆነ በስሜት፣ ሕመም ለሚሰቃዩ እወዳችኋለሁ ነው፤ ተስፋ አትቁረጡ" በማለት በቲውተር ገጿ ላይ ያሰፈረችው ሲያ "ሕመም ሞራልን ያላሽቃል፤ እናም ብቻችሁን አይደላችሁም" ብላለች።
እንደ ዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና አገልግሎት ጥናት ከሆነ 13 ዓይነት የኢዲኤስ ሕመሞች ያሉ ሲሆን፣ በሽታው በአካል ውስጥ ያሉ የመገጣጠሚያ ስሮችን ያጠቃል።
ይህ በሽታ አንዳንዱ ለክፉ የማይሰጥ ሲሆን አንዳንዱ ደግሞ መንቀሳቀስን አዳጋች ሊያደርግ ይችላል።
ሲያ ከዚህ በፊት ስላለባት የመጠጥ ሱስ ለአድናቂዎቿ ተናግራ የነበረ ሲሆን፤ ባለፈው ዓመት ከመጠጥ ከራቀች ስምንት ዓመት እንደሆናት በትዊተር ገጿ ላይ አስፍራ ነበር።












