ሰሜን ኮሪያ ከሰርጓጅ መርከቧ ሚሳዔል ሳትተኩስ አልቀረችም ተባለ

ታትሟል

ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር በኒውክለር ፕሮግራሟ ላይ ያቋረጠችውን ውይይት ለመቀጠል እንደምትፈልግ በተሰማ በሰዓታት ውስጥ ከሰርጓጅ መርከቧ ላይ ሚሳዔል ሳትተኩስ እንዳልቀረች ተነግሯል።

የደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣናት እንዳሉት ሚሳዔሉ የተተኮሰው ከዎንሳን ወደብ አቅራቢያ ሲሆን በጃፓን ባህር ላይ ከማረፉ በፊት በ910 ኪሎ ሜትር ከፍታ ሲምዘገዘግ ነበር።

ይህ የደቡብ ኮሪያ መረጃ እውነት መሆኑ ከተረጋገጠ ከግንቦት ወር ወዲህ ከተደረጉ የአጭር ርቀት ሚሳዔል ሙከራዎች በኋላ የተደረገ "ጠብ አጫሪ" ሙከራ ነው ተብሏል።

ዜናው እንደተሰማ ወዲያው ከተለያዩ አካላት ውግዘት ተሰንዝሯል።

የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዝዋ አቤ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ሰሜን ኮሪያ የባሌስቲክ ሚሳዔልን ቴክኖሎጂን እንዳትጠቀም ያስቀመጠውን ደንብ መተላለፍ ነው ሲሉ ድርጊቱን አውግዘውታል።

የደቡብ ኮሪያ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤትም ሙከራውን በጠንካራ ቃላት አውግዟል።

ሚሳዔል መተኮሱ ከመሰማቱ ከሰዓታት በፊት ፒዮንግያንግ ከዋሺንግተን ጋር አቋርጣው የነበረው የኒውክለር ፕሮግራሞቿን የተመለከተ ውይይት በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ እንደምትቀጥል አስታውቃ ነበር።

ባለፈው የካቲት ከተካሄደውና ያለውጤት ከተጠናቀቀው የሐኖይ ጉባኤ በኋላ ድርድሩ ተቋርጦ ቆይቷል።

ዜናው እንደተሰማ ሰሜን ኮሪያ ሁለት ሚሳዔሎችን ማስወንጨፏ የተገለፀ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አንዱ የጃፓን ውሃ ክልል ላይ ማረፉ ተነግሮ ነበር።

በኋላ ላይ የጃፓን ካቢኔ የበላይ ኃላፊ የሆኑት ዮሺዳ ሱጋ፣ አንድ ባለስቲክ ሚሳዔል ተተኩሶ የውሃ አካሉ ላይ ከማረፉ በፊት ለሁለት ተከፍሎ ሊሆን ይችላል ሲሉ ገልፀዋል።

ይሀ ሰሜን ኮሪያ ያደረገችው የሚሳኤል ተኩስ ለ11ኛ ጊዜ ቢሆንም የደቡብ ኮሪያና የጃፓን ባለሥልጣናት ግን በይበልጥ የተተኮሰው ሚሳዔል መምዘግዘግ የሚችለው ርቀት ላይ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ሰሜን ኮሪያ የረዥም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳዔሎችን ከማቋረጧ ቀደም ብሎ ከሰርጓጅ መርከቦች የሚተኮሱ ባሌስቲክ ሚሳዔሎች ቴክኖሎጂን ለተወሰነ ጊዜ አቋርጣ ነበር።

ሰሜን ኮሪያ ለመጨረሻ ጊዜ ከሰርጓጅ መርከቦቿ ላይ ሚሳዔል ያስወነጨፈችው እኤአ በ2016 ነበር።