ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የናይጀሪያ ፖሊስ ሴቶችና ህጻናትን "ከህጻናት ፋብሪካ" ነጻ አወጣ
የናይጄሪያ ፖሊስ በደቡብ ምዕራብ ናይጄሪያ ከሌጎስ ግዛት ወጣ ብሎ በሚገኝ ሕገ ወጥ ቤት ውስጥ ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ 19 ሴቶችንና ሁለት ጨቅላ ህጻናትን ጨምሮ አራት ልጆችን ነጻ ማውጣቱን አስታወቀ።
"የሕጻናት ፋብሪካ" ተብለው ከሚጠሩት የእናቶችና የሴቶች ማቆያ ቤቶች መካከል እንደሆነ በተነገረው በዚህ ቤት ውስጥ የተገኙት እናቶች እድሜያቸው ከ15 እስከ 28 ሲሆን፤ ቤቱን ያስተዳድራሉ ተብለው የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች በናይጄሪያ የሰዎች ሕገ ወጥ ዝውውርን ለሚከታተለው ብሔራዊ ተቋም ተሰጥተዋል።
ፖሊስ ለቢቢሲ እንዳረጋገጠው በቤቱ ውስጥ የተገኙት ሴቶች አቅመ ደካሞች ሲሆኑ፤ የሚወልዷቸው ልጆች ሴት ከሆኑ ከ800 በላይ እንዲሁም ወንድ ከሆኑ ከ1 ሺህ በላይ ዶላር እንደሚከፈላቸው ተነግሯቸው የሄዱ ናቸው።
በቤቱ ውስጥ ከተገኙት ሴቶች መካከል አንዷ፤ ካለፈቃዷ መያዟንና የወለደችው ልጅ ሊሸጥ እንደሆነ ስታውቅ ከቤቱ እንዳትወጣ መከልከሏን ለቢቢሲ ትናገራለች።
ሌላኛዋ ደግሞ የሞባይል ስልኳና ገንዘቧ እንደተወሰደባት እንዲሁም ምንም እንኳን ህመም ቢያጋጥማትም ህክምና ለማግኘት ከቤቱ እንዳትወጣ መከልከሏን ገልጻለች።
ሴቶቹን ከሚጠብቁትና በወንጀሉ ተጠርጥረው ከተያዙት መካከል አንዷ ቤቱ "የህጻናት ፋብሪካ" መሆኑን ያወቀችው ሥራውን ከጀመረች በኋላ መሆኑን ጠቅሳ ለፖሊስ ሄዳ ለመጠቆምም ፍርሃት እንዳደረባት ተናግራለች።
የናይጄሪያ ፖሊስና ብሔራዊው ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን የሚቆጣጠረው አካል ህጻናትን የሚያዘዋውሩ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ሲያውሉ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።
በጉዳዩ ላይ ተሳታፊ የሆኑ ተጠርጣሪዎች በሙሉ ለፍርድ እስከሚቀርቡ ድረስ ክትትልና ምርመራው እንደሚቀጥል ተገልጿል።
የፖሊስ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሴቶቹ ይጠለፉና ይደፈራሉ። የተደፈሩት ሴቶች በደፋሪዎቹ ቁጥጥር ሥር ሆነው እንዲያረግዙ ይደረጋል። በዚህ መልኩ የሚወለዱ ልጆች ግን ለእናቶቻቸው አይሰጡም፤ ዋጋ እየተተመነላቸው ለሽያጭ ይቀርባሉ።
ህጻናቱ የተሸጡበት ገንዘብም ለወላጆቻቸው (ለእናቶቻቸው) የሚሰጥ ሳይሆን የፋብሪካው ("የህጻናት ፋብሪካው") ጌቶች እንደፈለጉ የሚያደርጉት ነው። ሴቶቹም ብቸኛ ሥራቸው በማያውቋቸው ሰዎች እየተደፈሩ ልጅ መውለድ ብቻ ነው።
የዚህ ወንጀል ተጠቂ የሆኑት ሴቶች ታዲያ ሥራ እናስይዛችኋለን በሚል መደለያ ከተለያዩ የአሪቱ ክፍል የተሰባሰቡ ናቸው።