በቦይንግ ሌላ አውሮፕላን ላይ ችግር መታየቱ ተገለጸ

የቦይንግ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በሥራ ላይ ባሉ በአንዳንድ ቦይንግ 737 ኤንጂ በተባሉት የቦይንግ ስሪት አውሮፕላኖች ላይ የመሰንጠቅ ምልክቶች መታየታቸው ተነገረ።

ይህንንም ተከትሎ የአሜሪካ የአየር ትራንስፖርት ደህንንት ተቆጣጣሪዎች በአውሮፕላኖቹ ላይ አስቸኳይ ምርመራ እንዲደረግ አዘዋል።

የአሜሪካ ፌደራል የአየር በረራ የበላይ ተቆጣጣሪ የሆነው ኤፍኤኤ እንዳለው ቦይንግ "ለረጅም ጊዜ ጥቅም ላይ በዋሉ አውሮፕላኖች ላይ ማሻሻያዎችን በሚያደርግበት ጊዜ የመሰንጠቅ ምልክቶች" ማግኘቱን ገልጿል።

ተቋሙ ጨምሮ እንደገለጸው ተመሳሳይ መሰንጠቆች አነስ ያለ ቁጥር ባላቸው ሌሎች አውሮፕላኖች ላይ መገኘቱንም አመልክቷል።

ነገር ግን ሁለት የመከስከስ አደጋ ገጥሞት ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ከበረራ ውጪ እንዲሆን የተደረገው ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ላይ የተባለው ችግር እንዳልታየ ተጠቅሷል።

የቦይንግ ኩባንያ እንዳለው የ737 ኤንጂ ምርቶችን ከሚጠቀሙ ተቋማት ስለአውሮፕላኖቹ አስተያየት መቀበሉን ገልጾ ምንም አይነት ችግር እንዳላጋጠማቸው አረጋግጫለሁ ብሏል።

የአሜሪካው አውሮፕላን አምራች ቦይንግ በምን ያህል ምርቶቹ ላይ ምርመራውን እንደሚያካሂድ ያለው ነግር የለም።

"በቀጣዮቹ ቀናት አውሮፕላኑ ካላቸው ደንበኞቻችን ጋር በቅርበት በመስራት የሚጠበቀውን የምርመራ ሥራ በተወሰኑ አውሮፕላኖች ላይ እናካሂዳለን" ሲል ለቢቢሲ ገልጿል።

አክሎም ይህ ያጋጠመው ችግር ከበረራ ውጪ በሆኑት 737 ማክስ አውሮፕላኖችም ሆነ በሌሎች ላይ እንዳላጋጠመ ገልጿል።

ቢቢሲ በአውሮፕላኖቹ ላይ የተገኙት ስንጥቃቶች በየትኛው ክፍል ላይ እንደሆነ ለማወቅ ተጨማሪ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት ለቦይንግ ጥያቄ ቢያቀርብም እስካሁን ምላሽ አላገኘም።

737 ኤንጂ የተባለው ይህ የቦይንግ ስሪት አውሮፕላን 737-700፣ 737-800 እና 737-900 የተሰኙ ምርቶች ያሉት ሲሆን፤ የተለያዩ አየር መንገዶች እንደሚጠቀሙበት ቦይንግ በድረ ገጹ ላይ አስፍሯል።

የአሜሪካ የአየር ትራንስፖርት ተቆጣጣሪ ባወጣው መግለጫ "አውሮፕላኑን የሚጠቀሙ ተቋማት ተለይቶ የሚታወቅ ምርመራ እንዲያደርጉ፣ ከዚያም አስፈላጊውን ጥገና በማካሄድ በአስቸኳይ የምርመራቸውን ውጤት እንዲያሳውቁ" ማዘዙን ገልጿል።

ቦይንግ 737 ማክስ በሚባሉት አውሮፕላኖቹ ላይ ሁለት አሰቃቂ አደጋዎች ባለፈው ዓመት ከደረሱ በኋላ ከበረራ ውጪ መሆናቸው የሚታወስ ነው።

መጋቢት 01/2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን 157 መንገደኞችን ይዞ ለመብረር ከተነሳ ከደቂቃዎች በኋላ ተከስክሶ ሁሉም ተሳፋሪዎች ከሞቱ በበሏ 737 ማክስ ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆን ተደርጓል።

ይህ አደጋ የተከሰተው ከአራት ወራት ቀደም ብሎ ኅዳር ወር ላይ የኢንዶኔዢያው ላየን ኤር አየር መንገድ ንብረት የሆነው ተመሳሳይ አውሮፕላን ተከስክሶ 189 ሰዎች ካለቁ በኋላ ነበር።