ዴሞክራቲክ ኮንጎ፡ የቀድሞው የጤና ሚኒስትር ከኢቦላ ፈንድ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ዋሉ

ኦሊ ኢሉንጋ

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

ታትሟል

በዴሞክራቲክ ኮንጎ ለኢቦላ ወረርሽን መቆጣጠሪያና መከላከያ ተብሎ የተመደበ ገንዘብ ያለአግባብ ተጠቅመዋል የተባሉት ቀድሞው የሃገሪቱ የጤና ሚኒስትር በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።

ኦሊ ኢሉንጋ ባሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ ከኢቦላ ጋር የተያያዘ ሃላፊነታቸውን እንደተነጠቁ ሲሰሙ ነበር ከሚኒስተርነት እራሳቸውን ያገለሉት።

ፖሊስ የቀድሞው ሚኒስትር በህግ የተላለፈውን ውሳኔ በመጋፋት በሚስጥር ከሃገር ሊወጡ ሲሉ ነው በቁጥጥር ስር ያዋልኳቸው ቢልም እርሳቸው ግን ምንም የሰራሁት ጥፋት የለም በማለት እየተከራከሩ ነው።

''ስራዬን የለቀቅኩትም ኢቦላን ለመከላከል ፍቃድ ያላገኘ የክትባት መድሃኒት የዓለም የጤና ድርጅት መጠቀሙን በመቃወም ነው'' ብለዋል የቀድሞው ሚኒስትር።

በወቅቱ የኢቦላ መድሃኒት እጥረት አጋጥሞ ስለነበረና ሌላ አማራጭ ስለሌለን ፍቃድ ያለገኘውን ክትባት ለመጠቀም ተገደን ነበር ብለው የሚከራከራከሩ የጤና ባለሙያዎችም አልጠፉም ነበር በወቅቱ።

የቀድሞው ሚኒስትር ዶክተር ኢሉንጋ እንደሚሉት ከዚህ በፊት አገልግሎት ላይ ይውል የነበረው መድሃኒት ውጤታማነቱ የተረጋገጠ ሲሆን በኋላ ላይ የመጣው ክትባት ግን አስተማማኝ አይደለም።

የተለያዩ ምግባረ ሰናይ ድርጅቶችና ሃገራት ለኢቦላ ወረርሽኝ መከላከያ የሚውል ከ150 ሚሊየን ዶላር በለይ ለግሰው ነበር። እስካሁን ከበሽታው ጋር በተያያዘ ከ2000 በላይ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።