ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢቦላ ተይዛ የነበረችው የ9 ዓመት ሕጻን ሕይወቷ አለፈ
ታትሟል
በኢቦላ ተይዛ የነበረችው የ9 ዓመቷ የኮንጎ ዜጋ ከሰዓታት በፊት በኡጋንዳ ሕይወቷ ማለፉ ተረጋገጠ።
ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ወደ ኡጋንዳ የመጣችው የ9 ዓመቷ ሕፃን በፖንድዌ ድንበር ስታቋርጥ የኢቦላ በሽታ ምልክቶች ታይተውባት ነበር።
በኋላም በኢቦላ በሽታ ተጠርጥራ የደም ናሙናዋ ለምርመራ የተላከው ይህች አዳጊ በኢቦላ ቫይረስ እንደተያዘች የተረጋገጠው ዛሬ ጠዋት ነበር።
አዳጊዋ ወዲያውኑ ከሌሎች ሰዎች ተነጥላ ወደ ኢቦላ ሕክምና ጣቢያ ተልካም ነበር።
የኡጋንዳ የጤና ጥበቃ ባለሥልጣናት አሁን የአዳጊዋ ሬሳ ወደ አገሯ በሚመለስበት ሁኔታ ዙርያ እየተነጋገሩ ይገኛሉ።
የልጅቷ እናትም ገለል ተደርገው ክትትል እየተደረገባቸው ሲሆን እርሳቸውም ወደ ኡጋንዳ እንደሚላኩ ይጠበቃል።
ኡጋንዳ ከኮንጎ በምትዋሰንበት ድንበር ከፍተኛ የኢቦላ ቁጥጥር እያደረገች ትገኛለች።
ባለፈው ሰኔ በኡጋንዳ በኢቦላ ምክንያት ሁለት ሰዎች መሞታቸው ተዘግቦ ነበር።
ባለፈው ዓመት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ወረርሽኙ አገርሽቶ 2ሺህ ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።
አንድ ኡጋንዳዊና ኮንጓዊ ሚስቱ ዘመድ ለመጠየቅ ወደ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ደርሰው ከተመለሱ በኋላ ሁለት ልጆቻቸውን በኢቦላ ማጣታቸው ይታወሳል።