ስፔን ውስጥ የሚወለዱ ሕፃናት 'እንደ ተኩላ' ፊታቸው ላይ ፀጉር እየታየባቸው መሆኑ ታውቋል

ስፔን ውስጥ የሚወለዱ ሕፃናት 'እንደ ድኩላ' ፊታቸው ላይ ፀጉር ታይቶባቸዋል

የፎቶው ባለመብት, Science Photo Library

ታትሟል

ስፔን ውስጥ በቅርቡ ከተወለዱ ሕፃናት መካከል የተወሰኑቱ ፊታቸው ላይ ፀጉር እንደበቀለባቸው እና ምክንያቱ ደግሞ የተሳሳተ መድኃኒት እንደሆነ እየተነገረ ነው።

ቫሌንሲያ፣ ካንታብሪያ እና ግራናዳ በተባሉ የስፔን ከተሞች የተወለዱ 17 ሕፃናት ይህ ክስተት እንዳጋጠማቸው ታውቋል።

የሕክምና ሰዎች ሕፃናቱ ፈታቸው ላይ ፀጉር በቅሎባቸው ሊወለዱ የቻሉት እናቶች በእርግዝና ወቅት እና በኋላ በወሰዱት መድኃኒት ሳቢያ ነው ይላሉ።

«የልጄ ግንባር፣ ጉንጭ፣ እጆቹና እግሮቹ ሁሉ በፀጉር ተሸፍነው ነበር። በጣም ነው የሚያስፈራው» ስትል ነው አንዲት እናት ሁኔታውን የገለጠችው።

የስፔን ጤና ቁጥጥር ሰዎች ባደረጉት ማጣራት እናቶች ነብሰ-ጡር ሳሉ ከጨጓራ ጋር የተያያዘ በሽታን ለማስታገስ ሲሉ የወሰዱት መድኃኒት ነው ጨቅላዎቹ ለየት ያለ ፀጉር ይዘው እንዲበቅሉ ያደረገው ብለዋል።

'ኦሜፕራዞል' የተሰኘው ክኒን በውስጡ 'ሚኖክሲዲል' የተሰኘ ንጥረ-ነገር ይዟል፤ ይህ ደግሞ የፀጉር እድገትን የሚያፋጥን ነው ይላሉ ባለሙያዎች።

አሁን መድኃኒቱ ከገበያ ውጭ እንዲሆን መደረጉም ታውቋል፤ ክኒናውን አከፋፍሏል የተባለው ድርጅትም ተዘግቶ ምርመራ እየተደረገበት ነው።

አል-ሙንዶ ለተሰኘው ጋዜጣ ድምጿን የሰጠች አንድ እናት የ22 ወራት ዕድሜ ያላት ሴት ልጇ ፊት ላይ ፀጉር መብቀል ሲጀምር እጅግ ተደናግጣ እንደነበር ትናገራለች።

እናቶች በእርግዝና ወቅት ከሚወስዱት መድኃኒት በተጨማሪ ለሕፃናት የሚዘጋጀው 'ኦሜፕራዞል' በውስጡ ፀጉር አሳዳጊ ንጥር እንደያዘ ሊታወቅ ችሏል።

'ዌርውልፍ ሲንድረም' በመባል የሚታወቀው ይህ በሽታ ሕፃናት ያለዕድሜያቸው እና ባለተለመዱ ቦታዎች ላይ 'እንደ ተኩላ' ፀጉር እንዲያበቅሉ የሚያደርግ ነው።

የስፔን ጤና ጥበቃ ሰዎች መድኃኒቱን ከያለበት እየሰበሰቡ ምርመራ ማድረግ ላይ መሆናቸውን አክለው አሳውቀዋል፤ ሌሎች ወላጆች እንዳይጠቀሙትም መክረዋል።