ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በታንዛኒያ የነዳጅ ቦቴ ፈንድቶ ቢያንስ 60 ሰዎች ሞተዋል ተባለ
ታትሟል
በታንዛኒያ የነዳጅ ቦቴ ፈንድቶ 60 ሰዎች ሲሞቱ 65 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ፖሊስ ገለፀ። በኢንተርኔት የተለቀቁ ምስሎች ላይ ሰፊ ሥፍራን በሚሸፍን ቦታ ላይ በእሳት የተያያዙ የመኪና ስብርባሪዎችና የከሰሉ የሰው አስክሬኖች ይታያል።
ፖሊስ የሞቱና የቆሰሉት ሰዎችን መንገዱ ላይ ተገልብጦ ከነበረው ቦቴ ነዳጅ ለመውሰድ ሲሞክር ነበር ብሏል።
አደጋው የደረሰው ከዳሬ ሰላም 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሞሮጎሮ ክልል ውስጥ ነው።
ሞሮጎሮ ከወደብ ከባድ ጭነቶችንና ነዳጅ ለሚያመላልሱ መተላለፊያ ስትሆን የታንዛኒያ ትልቋ የንግድ ከተማም ነች።
የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋት አለ።
ዳንኤል ንጎጎ የተባሉ የዓይን ምስክር ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት " ሁኔታው የከፋ ነው። በርካታ ሰዎች ሞተዋል። ከመኪናው ላይ ነዳጅ እየሰረቁ ያልነበሩ ሁሉ ሳይሞቱ አልቀሩም፤ ምክንያቱም በከተማዋ በርካታ ሰዎች ይኖራሉ" ብለዋል።
በአፍሪካ ከነዳጅ ጫኝ መኪኖችና ከነዳጅ ቱቦዎች ነዳጅ ለመስረቅ ሲሞክሩ በሚደርስ ፍንዳታ የሚደርስ ሞት የተለመደ ነው።
ባለፈው ወር በናይጄሪያ ከተገለበጠ የነዳጅ መኪና ላይ ነዳጅ ለመስረቅ እየሞከሩ የነበሩ 45 ሰዎች በተነሳው እሳት ምክንያት መሞታቸው ይታወሳል።