የቴክሳስ ፖሊስ ጥቁር እስረኛን በፈረስ ላይ ሆነው በገመድ በማሰራቸው ይቅርታ ጠየቁ

ሁለት ፖሊሶች በፈረስ ላእ ሆነው እስረኛው በእግሩ እየሄደ

የፎቶው ባለመብት, Anonymous

ታትሟል

የቴክሳስ ፖሊስ በደንብ መተላለፍ ይዤዋለሁ ያለውን ዶናልድ ኔሊን በቁጥጥር ስር ያውላል። የጋልቬስተን ፖሊስ እንደሚለው ከሆነ እስረኛውን ለማጓጓዝ መኪና በወቅቱ በቶሎ አልመጣም። እናም ፈረሰኘኛ ፖሊሶቹ እስረኛውን እነርሱ በፈረስ በገመድ አስረው እርሱ በእግሩ ሆኖ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወስደውታል።

ፖሊስ ጣቢያ ከመድረሱ በፊት ግን አንድ ማንነቱ እንዳይገለፅ የፈለገ ግለሰብ ይህንን ድርጊት በምስል አስቀርቶ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ አጋራው።

በተለይ ጉዳዩን ከባርነት ዘመን ጋር ያገናኙት ግለሰቦች ድርጊቱን ኮነኑ፤ አወገዙ።

የቴክሳስ ፖሊስም የፖሊስ ባልደረቦቻችን እንዲህ ማድረግ አልነበረባቸውም በማለት ይቅርታ ጠይቋል።

የጋልቬስተን ፖሊስ ኃላፊ ቨርነን ሐሌ እስረኛን በፈረሰኛ ፖሊሶች በዚህ መልኩ ይዘው መሄድ በአንዳንድ ሁኔታዎች ተቀባይነት ያለው አሰራር ሆኖ መቆየቱን ጠቅሰው ነገር ግን "ፖሊሶቻችን ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ደካማ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል" ብለዋል።

አክለውም ምንም ዓይነት "ድብቅ ዓላማ " የለውም በማለት ይህንን አይነት እስረኛን የማጓጓዝ ተግባር እንዲቀር መወሰናቸውን ተናግረዋል።

እንደ ጋልቬስተን ፖሊስ ከሆነ በፈረስ ላይ የተቀመጡት ፖሊሶች ብሮሽ እና ስሚዝ ሲሆኑ ዶናልድ ኔሊን በቁጥጥር ስር ያዋሉት በሕግ መተላለፍ ነው።

የፖሊስ ጣቢያው በሰጠው መግለጫ ላይ እንደገለፀው " የዚህ ዓይነት እስረኛ አያያዝ ያለውን አሉታዊ ትርጉም እንረዳለን፤ ስለዚህም ይህንን የእስረኛ አያያዝ እንዲቆም ወስነናል" ብለዋል።

የፖሊስ ኃላፊው ሐሌ፣ እስረኛው ኔሊ በዚህ በሚያሸማቅቅ መንገድ በቁጥጥር ስር በመዋሉ ይቅርታ ጠይቀውታል።

በተጨማሪም በቁጥጥር ስር የዋለበት ድረስ ሌላ መጓጓዣ እስኪመጣ ድረስ መጠበቅ ነበረባቸው ሲሉ ተናግረዋል።

ሚስተር ኔሊ የዋስ መብቱ ተጠብቆለት የወጣ ቢሆንም በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ሊገኝ አልቻለም።

የጋልቬስተን ካውንቲ ጥምረት ለፍትህ ዳይሬክተር ሊዮን ፊሊፕስ ለቢቢሲ እንዳሉት ከሆነ በዚህ አካባቢ እንደሚኖር ግለሰብ ክስተቱን "ለማውራት የሚከብድ" ሲሉ ገልፀውታል።

" ይህ ቀሽም ስህተት ነው" በማለትም "ነጭ ቢሆን ኖሮ እንዲህ አያደርጉም ነበር" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ሚስተር ኔሊ የአእምሮ ሕመምተኛ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ምንም ያህል ጊዜ ቢፈጅ መኪና እስኪመጣላቸው ድረስ መጠበቅ ነበረባቸው ሲሉ ሀሳባቸውን ያጠናክራሉ።

"የፖሊስ ኃላፊው ምንም ዓይነት ፖሊሲ አልተላለፉም ብለዋል እስረኛን ከቦታ ቦታ የማጓጓዝ ፖሊሲ ማለት ምን ማለት ነው? "

" ያ ፖሊሲስ በ1875 አለመጻፉን በምን እርግጠኛ መሆን እችላለሁ? በርካታ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ" ሲሉ ሀሳባቸውን ያጠናቅቃሉ።