ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በናይጀሪያ ስልሳ አምስት ኃዘንተኞች "በቦኮ ኃራም" ታጣቂዎች ተገደሉ
በናይጀሪያ ሰሜን ምስራቃዊዋ ቦርኖ ግዛት ቦኮ ኃራም ናቸው ተብለው በተጠረጠሩ ታጣቂዎች በተከፈተ ተኩስ ስልሳ አምስት ኃዘንተኞች ተገድለዋል።
የአይን እማኞች እንደተናገሩት ቅዳሜ እለት ታጣቂዎች በሞተር ሳይክሎችና በመኪኖች ተጭነው መጥተው ተኩስ እንደከፈቱ ነው።
ኃዘን ላይ የነበሩ ግለሰቦች በተተኮሱት ጥይቶች ህይወታቸው ወዲያው ያለፈ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ የሞቱት ታጣቂዎቹን ለመያዝ በመከተላቸው እንደሆነ ተዘግቧል።
በቀጠናው የፅንፈኛ ሙስሊሞች ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
የአካባቢው አስተዳደሪ ሙሀመድ ቡላማ የአሁኑ የተፈፀመው ጥቃት ከሁለት ሳምንት በፊት አስራ አንድ የቦኮ ኃራም ታጣቂዎች በአካባቢው ግለሰቦች መገደላቸው ተከትሎ ለመበቀል መሆኑን ተናግረዋል።
በአካባቢው ተገኝተው የነበሩት የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘጋቢዎች እንደተናገሩት ወዳጅ ዘመዶቻቸው የተገደሉባቸው አስከሬኖቻቸውን ሲሰበስቡና የተቃጠሉ ቤቶችን ነው።
የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ጥቃቱን አውግዘው የኃገሪቱን አየር ኃይልና ሰራዊቱን ጥቃቱን ያደረሱትን እንዲያድኑ ትእዛዝ መስጠታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
በባለፈው አስር አመት በተፈጠሩ ግጭቶች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ንፁኃን ዜጎች ህይወታቸው ተቀጥፏል፤ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎችም ተፈናቅለዋል።