በታንዛኒያ እስር ቤቶች በተደረገ አሰሳ 743 ኢትዮጵያውያን ተገኙ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የኢትዮጵያ ኤምባሲ በታንዛኒያ በሚገኙ ስምንት ክልሎች በሚገኙ እስር ቤቶች ባደረገው አሰሳ 743 ኢትዮጵያውያን እስረኞች መገኘታቸውን በታንዛኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሚኒስትር ካውንስለር አቶ ቴዎድሮስ ግርማ ለቢቢሲ ተናገሩ።

በታንዛኒያ ወደ 21 ክልሎች አሉ ያሉት አቶ ቴዎድሮስ ከማክሰኞ ጀምሮ በቀሪዎቹ 13 ክልሎች አሰሳ እንደሚያካሂዱ ተናግረው የእስረኞቹ ቁጥር ከዚህም ሊጨምር እንደሚችል ያላቸውን ግምት ገልጸዋል።

በታንዛኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተከፍቶ በይፋ ሥራ ከጀመረ አምስት ወር ገደማ እንደሚሞላው ያስታወሱት አቶ ቴዎድሮስ እስካሁን ድረስ 1ሺህ 50 ሰዎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉን ተናግረዋል።

ኤምባሲው በታንዛኒያ የተለያዩ እስር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ቁጥር በትክክል ለማወቅ ባደረጉት አሰሳም እስካሁን ድረስ 743 ገደማ እስረኞችን በስምንት እስር ቤቶች ማግኘታቸውን ጨምረው አስረድተዋል።

ከእስረኞቹ መካከል አንድ ሴት ብቻ እንደምትገኝ የገለፁት አቶ ቴዎድሮስ ዕድሜያቸው ከ18 በታች የሆኑ አዳጊዎች፣ ወጣቶች እና የሰባት ልጆች አባት እንደሚገኙበት ገልፀዋል።

አቶ ቴዎድሮስ እንደሚሉት የእነዚህ እስረኞች ቤተሰቦች ልጆቻቸው የት እንዳሉ፣ እንዲሁም በሕይወት ስለመኖራቸውም ስለማያውቁ ስም ዝርዝራቸውን በኤምባሲው የፌስቡክ ገጽ ላይ በየወቅቱ እንደሚለጥፉ ተናግረዋል።

ከዚህ በታች ባለው የኢምባሲው የፌስ ቡክ አድራሻ በመግባት የእስረኞቹን ስም ዝርዝር ማግኘት ይቻላል ብለዋል።

እነዚህ ኢትዮጵያውያን ሦስት ዓመት እና ከዚያ በታች በእስር ላይ የቆዩ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ቴዎድሮስ አንዳንዶቹ እስራቸውን ጨርሰው ከማረሚያ ቤቶች ያልወጡ እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

የታንዛኒያ መንግሥት እስረኞቹ የእስር ጊዜያቸውን እንደጨረሱ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ቢፈልግም ከሚገኙበት እስር ቤት ወደ ዳሬሰላም ወይንም ኪሊማንጀሮ አየር ማረፊያ ለማምጣትና የአየር ትኬት ወጪያቸውን ለመሸፈን አዳጋች በመሆኑ በዛው ባሉበት እስር ቤት እንዲቆዩ መገደዳቸውን ይጠቅሳሉ።

ሁሉም ኢትዮጵያውያን ፍርድ ቤት ቀርበው በሕገወጥ መልኩ የታንዛኒያን ድንበር በማቋረጥ ተከስሰው የተፈረደባቸው ናቸው ያሉት አቶ ቴዎድሮስ ከእስረኞቹ መካከል አንዳንዶቹ በቋንቋ ችግር ምክንያት ምርመራቸው ሳይጠናቀቅ የቀረ ቢኖርም አብዛኞቹ ግን ፍርድ ቤት ቀርበው እስር የተፈረደባቸው መሆናቸውን አስረድተዋል።

አቶ ቴዎድሮስ እንደሚሉት እነዚህ የፍርድ ጊዜያቸውን የጨረሱ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ ከሚኖሩበት እስር ቤት ወደ ዳሬሰላም ማጓጓዝ፣ አንዳንድ ጉዳዮችን እስኪያልቅላቸው ያሉ ወጪዎችንና የአየር ትኬት ወጪ እንደሚያስፈልግ አስታውሰው ከዚህ ቀደም ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም) የ288 እስረኞችን ወጪ መሸፈኑን አስታውሰው ከዚያ ውጪ ያለውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የወጪውን ግማሽ በመቻል የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ ቀሪውን በመሸፈን ስደተኞቹ ወደ ሀገራቸው እነዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል።

ለአንድ ግለሰብ የአየር ቲኬት ወጪው 402 ዶላር ነው ያሉት አቶ ቴዎድሮስ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያውያኑን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ በኤምባሲ ደረጃ የወጣው ወጪ ለትራንስፖርት ብቻ ከ188ሺህ ዶላር በላይ መሆኑን ይናገራሉ።

እነዚህን እስረኞች በአንድነት ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ከአይ ኦ ኤም፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ እና ሌሎች ደጋፊ አካላት ለመነጋገር እየሠሩ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።

አቶ ቴዎድሮስ ኢምባሲው በተለያዩ እስር ቤቶችን ለመመለስ ጥረት እያደረገ ባለበት ሰዓት እንኳ አስራ ሁለት ኢትዮጵያውያን በሕገወጥ መልኩ የታንዛኒያን ድንበር ሲያቋርጡ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው እንደተነገራቸው በማስረዳት "የስደት አዙሪት" ያሉትን ጉዳይ አሳሳቢነት ይናገራሉ።