የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የሙስና ክስ ይጠብቃቸዋል

ታትሟል

የእስራኤል ጠቅላይ አቃቢ ሕግ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን በሙስና እንደሚከስ አስታውቋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ በስርቆት፣ በማጭበርበርና በክህደት ሦስት ክስ ቀርቦባቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከባለጸጋ የቢዝነስ ሰዎች ስጦታዎችን ተቀብለዋል፣ ሃሳባቸውን ለመሸጥም የሚዲያ ሽፋን አመቻችተዋል ተብለዋል።

ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው "በካርድ የተሰራ ቤት ፈረሰ እንደማለት ነው" በማለት ክሱን አጣጥለውታል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ "በቀጣይ ሚያዝያ በሚካሄደው ምርጫ ተቃዋሚዎቼ እንደማያሸንፉኝ ሲገባቸው ከወዲሁ ሌላ የሥልጣን መወጣጫ መንገድ እየፈለጉ ነው፤ ሆኖም ግን አይሳካላቸውም" ብለዋል።

ክስ አቅራቢዎቹ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ ትውልደ እስራኤላዊ ከሆነው የሆሊውድ ፊልም ፕሮዲውሰር አርኖን ሚልካንና ከአውስትራሊያዊው ባለጸጋ ጄምስ ፓከር 264,100 የአሜሪካን ዶላር የሚያወጡ ውድ ስጦታዎችን ተቀብለዋል ይላሉ።

በክሱ፣ ቤንያሚን ኔታንያሁ ስጦታዎች ከተቀበሉ በኋላ የአሜሪካ ቪዛ እንዲያገኙና የታክስ ቅናሽ እንዲደረግላቸው አመቻችተዋል ተብሏል። በተጨማሪም የሳቸውን ስብዕና የሚያጎላ የሚዲያ ሽፋን በማመቻቸት ሁለት ክሶች ቀርበውባቸዋል።

ይህን ተከትሎ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁኑኑ ስልጣን ሊለቁ ይገባል በማለት ጠይቀዋል።

የሀገሪቱ ጠቅላይ አቃቢ ሕግ አቪካይ ማንደልብሊት በተጠቀሱት ወንጀሎች ዙሪያ መደበኛ ክስ እንደሚመሰርት ተናግረዋል። ነገር ግን ሥልጣን መልቀቅና አለመልቀቃቸውን የሚወስነው የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሆኑን ጠቅላይ አቃቢ ሕግ ተናግሯል።

ክሱ እንደሚቀጥል እና እንደማይቀጥል የፊታችን ሚያዝያ ከሚካሄደው ምርጫ በኋላ ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አሁን ባለው ሁኔታ ሁለት ታሪክ ሊሠሩ ይችላሉ። አንዱ የሚቀጥለውን ምርጫ አሸንፈው በእስራኤል ታሪክ ለረዥም ጊዜ ሥልጣን ላይ የቆዩ መሪ መሆን ነው።

ሁለተኛው ደግሞ ስልጣን ላይ እያሉ የተከሰሱ የመጀመርያው ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን።