ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በመኪና ኢንዱስትሪ ትልቁ ማን ነው?
የዓለማችን ትልልቅ መኪና አምራቾች የ2017 ሽያጫቸውን ይፋ አድርገዋል፤ አንደኛ ማን ነው?
በጀርመን ሃገር ያለው የቮልስዋገን ድርጅት በ2016 ቶዮታን ይበልጠው ይሆን?
ወይንስ ብዙ የመኪና አይነቶችን የሚያመርት ድርጅት ነው?
ድንገት የአሜሪካው አንጋፋ ጄኔራል ሞተርስ ተገዳድሮ ይሆን?
ምላሹ ቀላል አይደለም ምክንያቱም አምራቾቹ በአጠቃላይ ሽያጫቸው ውስጥ በሚያካትቱት የተወሰነ ነው። በተለይ ደግሞ የመኪና ስያሜ ምን ምን እንደሚያካትትም ጭምር።
አደናጋሪ
በአሁኑ ዓመት ወግ የደረሰው አዲስ ተፎካካሪ አለ። እሱም የሬኖ-ኒሳን-ሚትሱቢሺ መጣመር ነው።
ይህ የጃፓንና ፈረንሳይ ድርጅት ሚትሱቢሺን እ.አ.አ በ2016 ገዝቶ የድርጅቱን ስም ባለፈው ዓመት መስከረም ላይ ወደ አዲሱ ስያሜ ቀይሯል።
ይህ ድርጅት አስር የተለያዩ ብራንዶችን ያቀፈ ሲሆን እነሱም ዳሲያ፣ ዳትሰንን፣ ኢንፊኒቲንና ሬኖ ሳምሰንግ ሞተርስን ያካትታል። እነዚህ ሁሉ ተጠቃለውም 10.61 ሚልዮን የቤት መኪናዎችና ቀላል የሕዝብ ማመላለሻዎችን ጨምሮ እ.አ.አ በ2017 በሸጠው መሠረት በዓለም አንደኛ እንደሚያደርገው ይናገራሉ።
ይህ ግን ትንሽ አደናጋሪ ነው።
ለምን? ምክንያቱም ቮልስዋገን ባለፈው የፈረንጆች ዓመት 10.74 ሚልዮን መኪኖች መሸጡን ሲያሳውቅ ለሁለተኛ ዓመት በድጋሚ አንደኛ ደረጃ ይገባዋል የሚሉም አሉ።
ከባድ ውይይት
ለንደን የሚገኘው ቢኤምአይ የተሰኘ የጥናት ተቋም ውስጥ የመኪና ዋና ኃላፊ ሆና የምትሠራው አና-ማሪ ቤይስደን አንደኛ ደረጃ ላይ ለመመዝገብ ድርጅቱ ምን አይነት ደረጃ ላይ መሆን እንደሚፈልግ ይወስነዋል ትላለች።
አንዳንድ የሚድያ ዘገባዎች የሬኖ-ኒሳን-ሚትሱቢሺን ጥምር ድርጅት በ2017 በቀላል መኪና ሽያጭ አንደኛ ደረጃ ላይ አስቀምጠው፤ ቮልስዋገንን ሁለተኛ ደረጃ ላይ መዝግበውታል።
እነዚህ ዘገባዎች ግን ከቮልስዋገን ሽያጭ የከባድ መኪናዎችን ቁጥርን አውጥተዋል።
ከባድ መኪኖች በአጠቃላይ ከባድ መኪኖችንና አውቶቡሶችን የሚያካትት ሲሆን ቁጥራችው መውጣቱ ተገቢ ይሆናል፤ ምክንያቱም ከመኪና ምድብ ውስጥ ሊፈረጁ አይችልም።
ነገር ግን ቮልስዋገን የእነዚህን ከባድ መኪኖች ቁጥር በአጠቃላይ የሽያጭ ቁጥሮቹ ላይ ያካትታቸዋል። እናም ብዙዎች እነዚህን ቁጥሮች በቀጥታ በመጥቀስ የጀርመኑ ድርጅት በድጋሚ የአንደኝነት ቦታውን አለመልቀቁን ዘግበዋል።
ይበልጥ የሚያደናግረው ደግሞ የቀላልና ከባድ መኪና ስያሜ ከሃገር ሃገር መለያየቱ ነው።
ለምሳሌ በጣም ታዋቂ የሆነውን ኤስዩቪ የሚባለውን መኪና እንውሰድ። መኪና ነው ወይንስ ትራክ?
የዚህ ጥያቄ መልስ እንደየሃገራትና በመኪናው አይነት ላይ የተወሰነ ነው።
''ኤስዩቪዎች በጣም ተወዳጅ እየሆኑ ነው። እንደውም ብዙዎቹ እንደ ቤት መኪና እየተቆጠሩ ነው'' ይላል ዴሪን ዎንግ ካርባየር የተሰኘው መፅሄት ዋና አዘጋጅ።
''ሆኖም ግን በዩናይትድ ስቴትስ አንዳንድ ኤስዩቪዎች እንደ ቀላል ትራክ ይቆጠራሉ። በሲንጋፑር፣ ማሌዥያና ታይላንድ ቶዮታ ሃይሉክስ ፒካፕ ትራክ ሲሆን ከቶዮታ ፎረቱነሩ ጋር ቢመሳሰሉም እንኳን ይህኛው ግን ከሰው መጓጓዣ ነው የሚመደበው።''
''በአጭሩ እነዚህን ምድቦች ለመለየት በጣም አስቸጋሪ ነው'' ይላል።
ይህ ብቻ አይደለም።
ቫኖች ለምሳሌ ብዙ ጊዜ ከንግድ መኪና ይመደባሉ። ሆኖም ግን ሚኒ-ቫን የሚባሉት እንደ ቶዮታ ሲዬና አይነት ስምንት ሰው የሚይዝ መኪናን ግን አያካትትም።
እንደ ቼቭሮሌት ሲልቬራዶ አይነት ፒካፖች ለንግድም ይሁን ለግል አገልግሎት ቢሆኑ ከቀላል ትራኮች ምድብ ውስጥ ነው የሚካተቱት።
''ይህን ቀለል ለማድረግ የመኪና አምራቾቹ እራሳቸው በሚሰጡት የሰው ማመላለሻ መኪና ምድብ መሠረት ያለውን ቁጥር መውሰድ ነው። ነገር ግን ከእያንዳንዱ የመኪና ስምና የመኪና አምራች ጥምር ድርጅቶች አንፃር መሰላት ሊኖርበት ነው'' ይላል አቶ ዎንግ።
''ሆኖም ግን ሁሉም የመኪና አምራች የዓመቱን ሽያጭ ዝርዝር ይፋ አላደረገም፤ ደግሞም ሁሉም መኪና አምራች በሰውና በንግድ መኪና መካከል ያለውን አይለይም'' ብሏል።
ስለዚህ መልሱ ምንድን ነው?
በገበያ ላይ ያሉትን መኪኖች ለማነፃጸር እንዲቀል ከቁጥሩ የከባድ መኪኖችንና የአውቶቡሶችን ሽያጭ ማውጣት ይቻላል ትላለች ቤይስደን ከቢኤምአይ።
''ለተጠቃሚው ትርጉም የሚሰጠው ይህ አሠራር ነው። በዚህም አሠራር ነው የሬኖ-ኒሳን-ሚትሱቢሺ ቁጥር ጣሪያ የሚነካው'' ትላለች።
''በ2016 ሚትሱቢሺን መግዛታቸው በአሁኑ ሰዓት ያሏቸውን የመኪና ቁጥር ያለምንም ጥርጥር ይጨምረዋል። ስለዚህ የሁሉንም ምርቶች በመደመር የአንደኝነት ደረጃን ቢወስዱ የሚያስደንቅ አይሆንም።''
''የሁሉንም የመኪና አምራቾች ውጤት በሙሉ ብንደምርና የተመረቱትን የመኪና አይነቶች በሙሉ ብናካትት፤ እንደ ቮልስዋገን ያሉ ድርጅቶችን በአንደኛ ደረጃ ላይ ሊያስቀምጥ ይችላል። ምክንያቱም ቮልስዋገን ከትንሽ መኪኖች ከሃችባክ እስከ ትልልቁ ትርኮች ድረስ ያመርታል።''
ከእነዚህ አማራቾች መካከል መምረጥ ቢያቅት እንኳን ኦኢሴአ የተሰኘው የመኪና አምራቾች ዓለም አቀፍ ድርጅት ምርጥ የሆነ የሽያጭ ደረጃ ይሰጣል።
እሱም የሰው ማመላለሻ መኪኖች፣ ቀላል የንግድ መኪኖች፣ ሚኒባሶች፣ ትራኮችንና የሕዝብ ማጓጓዣ አውቶቡሶችን ያካትታሉ። የ2017 ደረጃ ምደባውን ደግሞ ይፋ አላደረገም።