ኔታንያሁ ሐማስ የለቀቀውን የታጋቾች ቪድዮ “ጭካኔ የተሞላ የሥነ ልቦና ፕሮፓጋንዳ” አሉት
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ በሐማስ የተለቀቀው ታጋቾችን የሚያሳይ ቪድዮ “ጭካኔ የተሞላበት ሥነ ልቦና ላይ ያነጣጠረ ፕሮፓጋንዳ ነው” በማለት አወገዙ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቁጣቸውን የገለጹት ጋዛ ውስጥ ተይዘው የሚገኙ ሦስት ታጋቾችን የሚያሳይ ቪድዮ በሐማስ መለቀቁን ተከትሎ ነው።
ኔታኒያሁ የታጋቾቹን ስም በመጥራትም መልዕክት አስተላልፈዋል። “የጦር ወንጀል በሚፈጽመው ሐማስ የታገታችሁት ኤሌና ትሩፓኖቭ፣ ዳንኤል አሎኒ እና ሪሞን ኪርሽት አቅፌያችኋለሁ” ብለዋል።
ከአንድ ደቂቃ ትንሽ በሚረዝመው እና ቢቢሲ በማያጋራው ቪድዮ ላይ፣ ሦስቱ ታጋቾች ግድግዳ ጥግ ተቀምጠው ወደ ካሜራ እያዩ ሲናገሩ ይታያል።
ሐማስ ከሦስት ሳምንት በፊት በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት በፈጸመበት ጊዜ ከ230 በላይ ሰዎችን አግቶ ወደ ጋዛ መውሰዱን የእስራኤል መንግሥት አስታውቋል።
ባለፈው ሳምንት የተወሰኑ ሰዎችን በቀይ መስቀል በኩል የለቀቀ ሲሆን፣ የቀሩትን ለመልቀቅ እስራኤል በጋዛ ላይ የምታካሂደውን ዘመቻ እንድታቆም ጠይቋል።