የእስራኤል ጦር ከሐማስ ጋር ከባድ ውጊያ ማድረጉን እና በርካታ ታጣቂዎች መገደላቸውን አስታወቀ
የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት በጋዛ ሰርጥ ከሐማስ ጋር ከባድ ውጊያ ማድረጉን እና በርካታ ታጣቂዎች መገደላቸውን አስታወቀ።
እግረኛ ጦሩም በአየር እና ባህር ጥቃቶች በመታገዝ በሰሜናዊ ጋዛ የሚገኘውን የሐማስ መከላከያ ግንባር መስበራቸውንም የእስራኤል ወታደራዊ ቃለ አቀባይ ገልጸዋል።
እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ በምታደርገው የማያባራ የአየር ጥቃት እና ከባድ መሳሪያ ድብደባ ከ8 ሺህ 700 በላይ ሰዎች ሲገደሉ በርካቶቹ ህጻናት መሆናቸውን ከጋዛ ጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
በትናንትናው ምሽት አል ቁድስ ሆስፒታል አቅራቢያን ጨምሮ ከፍተኛ ፍንዳታዎች እና የከባድ መሳሪያ ድብደባ ተኩሶች እየተሰሙ እንደነበር አለም አቀፉ የቀይ ጨረቃ ድርጅት አስታውቋል።
የእስራኤል ባለስልጣናት ህሙማንና የጤና ባለሙያዎች ሆስፒታሉን ለቀው እንዲወጡ ያስጠነቀቁ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት በበኩሉ በህሙማን ላይ የሞት አደጋ መፈረጅ ነው ብሎታል።
የመከላከያ ኃይሉ ሐማስ ጸረ ታንክ ሚሳኤሎችን መተኮሱን፣ ፈንጂዎችን እና የእጅ ቦምቦችን በእስራኤል ወታደሮችን ላይ መወርወራቸውን አስረድቷል። ጦ
ሩም በምላሹ በከባድ መሳሪያ፣ በታንክ እንዲሁም በአየር እና ከባህር በተወነጨፈ የሚሳኤል ጥቃት አድርሻለሁ ብሏል። እግረኛ ጦሩም ከሐማስ ታጣቂዎች ጋር ፊት ለፊት መዋጋታቸውንም አክሎ ገልጿል።