የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣን በጋዛ ‘ደኅንነቱ የተጠበቀ’ ቦታ የለም አሉ

የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣን በጋዛ ‘ደኅንነቱ የተጠበቀ’ ቦታ የለም አሉ። ይህ የተባለው የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ከሐማስ ጋር አየተደረገ ባለው ግጭት ጊዜያዊ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እየቀረቡ ያሉትን ጥሪዎች ውድቀ ማድረጋቸው ከተሰማ በኋላ ነው።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ጋዛ ውስጥ ከባድ “የዘር ማጥፋት” አደጋ መደቀኑን የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሙያዎች ገለጹ

  2. በእስራኤል ይሠሩ የነበሩ ጋዛ ነዋሪዎችን ወደመጡበት መለሰች

    በእስራኤል እና በዌስት ባንክ የሚገኙ በሺህዎች የሚቆጠሩ የጋዛ ነዋሪ የሆኑ ሠራተኞችን እና ላብ አደሮችን ወደ ጋዛ መመለሳቸውን ዘገባዎች ገለጹ።

    የእስራኤል መንግሥት ከጋዛ የሚመጡ ፍልስጤማውያን ሠራተኞች በግዛቱ እንደማይኖሩ ቀደም ብሎ አስታውቋል።

    የሐማስ ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከጋዛ ውጭ እንዲሠሩ ከእስራኤል ባለስልጣናት ፈቃድ አግኝተዋል።

    የዓይን እማኞች ለሮይተርስ እንደተናገሩት አንዳንድ የጋዛ ሠራተኞች የንግድ ዕቃዎች ማቋረጫ በሆነው እና በደቡባዊ ጋዛ ከእስራኤል ጋር በሚያገናኘው በኬረም ሻሎም መሻገሪያ በኩል ተመልሰዋል።

  3. ብሊንከን እና ኔታኒያሁ በቴል አቪቭ ተገናኙ

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በቴል አቪቭ ተገናኙ።

    የኔታኒያሁ ጽ/ቤት ሁለቱ መሪዎች ሲገናኙ የሚያሳይ ምስል አጋርቷል።

    ብሊንከን በቴል አቪቭ ቆይታቸው ከእስራኤል የጦርነት ካቢኔ አባላት ጋርም እንደሚገናኙ ተገልጿል።

    ብሊንከን ሐማስ መስከረም 26 እስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከሰነዘረ ወዲህ ወደ ቀጠናው ጉዞ ሲያደርጉ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

    ብሊንከን ከእስራኤል ባለስልጣናት ጋር በሚኖራቸው ንግግር በጋዛ ባሉ ሲቪሎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት የሚቀንስበት ሁኔታ ዋነኛ አጀንዳቸው እንደሚያደርጉ ቀድመው ገልጸው ነበር።

    ባይደን ከእስራኤል ጉብኝታቸው በኋላ ወደ ጆርዳን እንደሚያቀኑ ይጠበቃል።

    በጆርዳን ጉዟቸው ሐማስ በዚህ ጦርነት የሚሸነፍ ከሆነ የጋዛ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል እንዲሁም ግጭቱ በቀጠናው ወዳሉ አገራት እንዳይስፋፋ መግታት ስለሚቻልበት ሁኔታ እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል።

  4. እስራኤል ድብደባ እንድታቆም ዮርዳኖስ አሜሪካንን ልትጠይቅ ነው

    የዮርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከአሜሪካው አቻቸው ጋር ሲገናኙ እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ድብደባ በአስቸኳይ እንድታቆም እንደሚጠይቁ ተገለጸ።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ቅዳሜ ወደ ዮርዳኖስ ተጉዘው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አይማን ሳፋዲ ጋር ይነጋገራሉ።

    በሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ውይይት ላይ አይማን ሳፋዲ የእስራኤል እርምጃን አጥብቀው እንደሚያወግዙ ይጠበቃል።

    የዮርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ሚኒስትሩ ከብሊንከን ጋር ሲገናኙ እስራኤል ሰላማዊ ሰዎችን በቦምብ በመደብደብ እና ከበባ ውስጥ በመክተት የጦር ወንጀል እየፈጸመች እንደሆነ በመግለጽ የአገራቸውን ጠንካራ አቋም ያንጸባርቃሉ።

    ብሊንከን ከሐማስ ጥቃት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ በቀጠናው የሚገኙ መሪዎችን ለማነጋገር ዛሬ ረፋድ ቴል አቪቭ ደርሰዋል።

    ይህ የብሊንከን የጉዞ ዋነኛ ትኩረት ሐማስ በዚህ ጦርነት የሚሸነፍ ከሆነ የጋዛ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል እንዲሁም ግጭቱ በቀጠናው ወዳሉ አገራት እንዳይስፋፋ መግታት ስለሚቻልበት ሁኔታ ለመምከር ነው።

  5. ሐማስ ከዋሻዎች እየወጣ ጥቃት ሰንዝሮ እየሸሸ ነው ስትል እስራኤል ገለጸች

  6. የሄዝቦላ መሪ ሐሰን ናስራላህ የቡድኑን ቀጣይ እርምጃን የሚጠቁም ንግግራቸው ዛሬ ሊያደርጉ ነው

  7. የእስራኤል-ሐማስ ግጭት ወደ አካባቢው አገራት ሊስፋፋ እንደሚችል አረብ ኤምሬትስ ገለጸች

    የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚንስትር የእስራኤል-ሐማስ ግጭት ወደ አካባቢው አገራት ሊስፋፋ እንደሚችል ስጋታቸውን ገለጹ።

    ሚንስትሩ አካባቢው ሁኔታ “ሊፈነዳ ከጫፍ ደርሷል” ብለዋል።

    “ግጭቱ በቀጠናው የመቀጣጠሉ እና የመስፋፋቱ ነገር እሙን ነው። አክራሪ ቡድኖችም አጋጣሚውን በመጠቀም ርዮተ ዓለም ከማስፋፋት ባለፈ ወደ ግጭት ዑደት ውስጥ ሊከቱን ይችላሉ” ሲሉ ኑራ አል-ካቢ በአቡ ዳቢ በተካሄደ የፖሊሲ ኮንፈረንስ ላይ ተናግረዋል።

    በአሜሪካ አሸማጋይነት ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያው ግንኘቷን በ2020 የጀመረችው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፤ የሰብዓዊ ተኩስ አቁም እንዲደረገ “ያለመታከት” እየሠራች መሆኗን አል-ካቢ ገልጸዋል።

    “ጥረቶች ሁሉ ሲቪሎችን መጠበቅ እና ግጭቱን በፍጥነት ማስቆም ላይ ያተኩራሉ” ብለዋል።

  8. አንቶኒ ብሊንከን እስራኤል ገቡ

    ከእስራኤል ባለስልጣናት ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ የሚጠበቁት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንክን ቴል አቪቭ ገብተዋል።

    ብሊንከን በሲቪሎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት በሚቀንስበት ሁኔታ ላይ ትኩረት አድርገው ይመክራሉ ተብሏል።

    ሐማስ መስከረም 26 ጥቃት ከሰነዘረ በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ወደ እስራኤል ሲያቀኑ የአሁነኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

    በሲቪሎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እስራኤል “ጠንካራ እርምጃ” የምትወስድበትን መንገድ እንደሚያፈላልጉ ከአሜሪካ ከመነሳታቸው በፊት አሳውቀዋል።

    ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚሆን ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ጥሪ አቅርበዋል።

    ብሊንከን ወደ ጆርዳን እንደሚያቀኑ ይጠበቃል።

    እስራኤል የጋዛ ከተማን ሙሉ በሙሉ መክበቧን እና ከሐማስ ታጣቂዎች ጋር ፊት ለፊት እየተዋጋች መሆኗን አሳውቃለች።

  9. ታይላንድ በሐማስ የተያዙ 23 ዜጎቿን ለማስፈታት ከኢራን ጋር እየተነጋገረች ነው

    ታይላንድ ዜጎቿን ለማስፈታት ኢራንን ጨምሮ ከሌሎች ከሐማስ ጋር ግንኙነት መፍጠር ከሚችሉ መንግስታት ጋር እየተነጋገረች መሆኗን አስታወቀች።

    ሐማስ መስከረም 26 በእስራኤል ላይ ጥቃት ሰንዝሮ አግቶ ከወሰዳቸው ከ240 በላይ ሰዎች መካከል ቢያንስ 23ቱ የታይላንድ ዜጎች ናቸው።

    የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፓርንፕሬይ ባሂዳ-ኑካራ ለሐማስ ቅርበት ያላት ኢራን በድርድሩ ላይ እገዛ ለማድረግ ቃል ገብታለች ብለዋል።

    ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት ወደ 30 ሺህ የሚጠጉ ታይላንዳውያን በእስራኤል እርሻዎች ላይ ይሠሩ ነበር ተብሏል። በሐማስ ጥቃት በርካታ የታይላንድ ዜጎች ተገድለዋል።

  10. አሜሪካ ታጋቾችን ለመፈለግ በጋዛ ድሮን ማብረሯ ተገለጸ

    ሐማስ መስከረም 26 እስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሰንዝሮ ሰዎችን አግቶ ወደ ጋዛ ከወሰደ በኋላ አሜሪካ ታጋቾችን ፍለጋ በጋዛ በሰው አልባ አውሮፕላን የታገዘ ቅኝት ስታደርግ መቆየቷ ተዘገበ።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል ሁለት የአሜሪካ ባለስልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው አሜሪካ የታጋቾችን ቦታ ለመለየት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የቅኝት ድሮኖችን በጋዛ ስታበር ቆይታለች።

    ስሜ አይጠቀስ ያሉት የአገሪቱ ባለስልጣን አሜሪካ ከአንድ ሳምንት በላይ ድሮኖቹን ስታበር ቆይታለች።

    ሐማስ ከእስራኤል ካገታቸው መካከል 10 የሚሆኑት አሜሪካውያን መሆናቸው ተገልጿል።

  11. “በ24 ዓመቴ በፍጹም መሞት አልፈልግም”፡ ከራፋህ ድንበር መሻገር ያልቻለችው ወጣት

  12. ሐማስ ከዋሻዎች እየወጣ ጥቃት ሰንዝሮ እየሸሸ ነው ስትል እስራኤል ገለጸች

    የእስራኤል ጦር የሐማስ ጠንካራ ይዞታ የሆነውን የጋዛ ከተማን መክበቡን ገልጾ የሐማስ ተዋጊዎች ከዋሻዎች እየወጡ ጥቃት እየከፈቱ ነው ብሏል።

    ጦሩ ከሐማስ ተዋጊዎች ጋር በቅርብ ርቀት ጦርነት መግጠሙንና የሐማስ ተዋጊዎች ከዋሻዎች በመውጣት ጥቃት ሰንዝረው እየሸሹ መሆኑን ጠቁሟል።

  13. በምስል፡ በመላው ዓለም ሰልፎች ተካሂዱ

    በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የእስራኤል-ሐማስ ጦርነትን በተመለከተ ሰልፎች ተካሄዱ።

    ሰልፎቹ በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ የሚጠይቁ አልያም ለእስራኤል አጋርነትን የሚገልጹ ናቸው።

    በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰልፈኞች ለፍልስጤማውያን አጋርነታቸውን ለመግለጽ አደባባይ ወጥተዋል።

    በደቡብ ኮሪያ ሶል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ የሚጠይቅ ሰልፍ ተካሂዷል።

    በሮማኒያ እና በስዊትዘርላንድ ደግሞ ለእስራኤል አጋርነትን የሚገልጹ ሰልፎች ተካሂደዋል።

  14. የእስራኤል ጦር ጋዛ ከተማን ሙሉ በሙሉ መክበቡን አስታወቀ

    የእስራኤል ጦር ጋዛ ከተማን ሙሉ በሙሉ መክበቡን እና በከተማዋ ሐማስ ወታደራዊ ቅኝት የሚያደርግባቸውን መመልከቻዎች፣ ማዘዣ ጣቢያዎች እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን እያጠቃ እንደሆነ አስታወቀ።

    ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ጦራቸው ወደ ጋዛ ከተማ የሚያደርገውን ግስጋሴ ማጠናከሩን ገልጸው ነበር።

    ጠቅላይ ሚንሰትሩ “አስደናቂ ስኬት አስመዝግበን የጋዛ ከተማ ዙሪያን አልፈን ወደፊት እየገሰገስን ነው” ብለዋል።

  15. ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ጦራቸው ወደ ጋዛ ከተማ እየገሰገሰ መሆኑን ገለጹ

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ጦራቸው ወደ ጋዛ ከተማ የሚያደርገውን ግስጋሴ ማጠናከሩን ገለጹ።

    ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት የወጣው መግለጫ ጋዛ ውስጥ በሚካሄደው “ጦርነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ነን” ብሏል።

    ኔታኒያሁ ዝርዝር ከመረጃ ከመስጠት በተቆጠቡበት መግለጫ “አስደናቂ ስኬት አስመዝግበን የጋዛ ከተማ ዙሪያን አልፈን ወደፊት እየገሰገስን ነው” ብለዋል።

    ቀደም ሲል ሲወጡ የነበሩ ሪፖርቶች በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በጋዛ ከተማ ዙሪያ ጠንካራ ውጊያ እየተደረገ መሆኑ ተዘግቦ ነበር።

    ጋዛ ውስጥ ያለው የቢቢሲ ሪፖርተርም ሁለቱ ኃይሎች በሰሜናዊ የጋዛ ሰርጥ ቢያንስ በአምስት አካባቢዎች ውጊያ እያደረጉ ነው ሲል ዘግቦ ነበር።

  16. በሐማስ የታገቱ ሰዎች ቁጥር 242 መድረሱን እስራኤል አስታወቀች

    እስራኤል በሐማስ የታገቱ ሰዎች ቁጥር 242 መድረሱን አስታወቀች።

    ሐማስ እስራኤል ላይ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ድንገተኛ ጥቃት ሰንዝሮ በውል ያልታወቁ ሰዎችን አፍኖ መውሰዱ ይታወሳል።

    እስራኤል አድራሻቸው የጠፋ ሰዎችን ጉዳይ ስትመርምር የቆየች ሲሆን፣ አሁን ላይ በሐማስ እጅ የገቡ ሰዎች ቁጥር 242 መሆኑን አረጋግጫለሁ ያለች ሲሆን ከታጋቾቹ መካከል ሕጻናት እና አዛውንቶች ይገኙበታል ተብሏል።

    ሐማስ ከእስራኤል ያገታቸውን የተለያዩ ዜግነት ያላቸውን ሰዎች በጋዛ በተለያዩ ስፍራዎች እንደደበቀ የገለጸ ሲሆን፣ ቩድኑ እስራኤል በፈጸመችው የአየር ድብደባ እስካሁን ድረስ 57 የሚሆኑ ታጋቾች ተገድለዋል ብሏል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የታይላንድ መንግሥት በሐማስ ታግተው የሚገኙ ዜጎቹን ለማስለቀቅ ከቡድኑ ጋር ድርድር እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቋል።

    የታይላንድ መንግሥት እንዳለው ከሆነ “በትክክለኛው ጊዜ” ዜጎቹ እንደሚለቀቁ ከሐማስ ማረጋገጫ አግኝቷል።

  17. ባህሬን በእስራኤል ያሉትን አምባሳደሯን ጠራች

    በቅርቡ ከእስራኤል ጋር ወዳጅነቷን ያደሰችው ባህሬን እስራኤል በጋዛ ውስጥ እያካሄደችው ካለው ዘመቻ ጋር በተያያዘ በቴል አቪቭ የሚገኙትን አምባሳደሯን ጠርታለች።

    ከዚህ በተጨማሪም የባህሬን ፓርላማ እስራኤል በጋዛ እየፈጸመች ባለችው ጥቃት ምክንያት ከአገሪቱ ጋር ያላትን ምጣኔ ሃብታዊ ግንኙነትም እንዲቋረጥ ትዕዛዝ አሳልፏል።

    በባህሬን የነበሩት የእስራኤል አምባሳደርም ወደ አገራቸው ስለመመላሳቸው ተገልጿል።

    ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአሜሪካ አሸማጋይነት ባህሬን፣ ሞሮኮ፣ ሱዳን እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ከእስራኤል ጋር ግንኙነታቸውን በማደስ የንግድ እና ወታደራዊ ትብብር ስምምነት መፈጸማቸው ይታወሳል።

  18. አስካሁን ከ9 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ

    አንድ ወር ሊሞላው በተቃረበው የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት በጋዛ ላይ ያለማቋረጥ በተካሄደው የእስራኤል የአየር ድብደባ የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ9,000 በመብለጡን በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

    መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ በጋዛ ሰርጥ ላይ እየተፈጸመ ባለው ጥቃት የተገደሉ ሰዎች አሃዝ ከዕለት ዕለት እያሻቀበ ሲሆን፣ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በወጣው አዲስ ቁጥር መሠረት 9,061 ሰዎች ተገድለዋል።

    ከተገደሉት ውስጥም ከአንድ ሦስተኛው የሚልቁት ወይም 3,760ዎቹ ሕጻናት መሆናቸውን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አመልክቶ፣ ከ32,000 የሚልቁ የጋዛ ነዋሪዎች ደግሞ የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

    ለዚህ ጦርነት መቀስቀስ ምክንያት በሆነው የሐማስ ጥቃት 1,400 በላይ እስራኤላውያን የተገደሉ ሲሆን፣ 242 የሚሆኑት ደግሞ በቡድኑ ታግተው ወደ ጋዛ መወሰዳቸውን የእስራኤል መንግሥት አስታውቋል።

  19. በጋዛ - እስራኤል የተከሰቱ ዋና ዋና ጉዳዮች

    እስራኤል በጋዛ ሰርጥ የምታደርገውን ጥቃት በአየር፣ በመሬት እና በባህር በተቀናጀ መልኩ አጠናክራ መቀጠሏን ገልጻለች።

    ትናንት ምሽትም ከሐማስ ጋር ከባድ ውጊያ እንደተካሄደም የእስራኤል ጦር አስታውቋል።

    በቅርቡ የተከሰቱ ጉዳዮችን እንዳስ፦

    • የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እያካሄዱት በነበረው የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ላይ አንዲት ሴት የፕሬዚዳንቱን ንግግር አቋርጣ በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ተደጋጋሚ ጥሪ አቅርባለች። ይህንንም ተከትሎ ፕሬዚዳንቱ ታጋቾችን ለማስለቀቅ በጊዜያዊነት እንዲቆም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። "በእኔ አስተሳሰብ በጊዜያዊነት መቆም አለበት። መገታት ማለት እስረኞቹን ለማስወጣት ጊዜ መስጠት ማለት" ነው ሲሉም ተናግረዋል። ፕሬዚዳንቱ ጥሪ ያደረጉት ሰብዓዊ እርዳታ እንዲገባ እና በሐማስ የተወሰዱት 240 ታጋቾች እንዲፈቱ ነው ሲል ዋይት ሐውስ ማብራሪያ ሰጥቷል።
    • ከ400 በላይ የውጭ አገራት ዜጎች እና የተጎዱ ፍልስጤማውያን ከሶስት ሳምንታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጋዛን ለቀው እንዲወጡ ተፈቅዶላቸዋል። ከነዚህም መካከል የእንግሊዝ እና የአሜሪካ ዜጎች ይገኙበታል።
    • በግብጽ በኩል ያለው የራፋህ ድንበር ማቋረጫ ተዘግቶ የቆየ ሲሆን ለጋዛ እርዳታ ለማስገባትም ተከፍቶ ነበር።
    • የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት በጃባሊያ የስደተኞች መጠለያ ላይ ያደረሰውን ጥቃት አስመልክቶ ተዋጊ ጄቶች በጃባሊያ የሚገኘውን የሐማስ ማዘዣ እና መቆጣጠሪያ ህንጻ ላይ ጥቃት ማድረሱን ጠቅሶ "በጥቃቱ ሁለት የሐማስ አሸባሪዎች ተወግደዋል" ሲልም ለቢቢሲ ተናግሯል።
    • በጃባሊያ ላይ እስራኤል ላለፉት ሁለት ቀናት ተከታታይ የአየር ጥቃት ፈጽማለች። እስራኤል በስደተኞች ማቆያው ከፈጸመችው ጥቀት በኋላ 1,000ሰዎች መገደላቸው፣ መጎዳታቸው ወይም የት እንዳሉ እንዳልታወቀ የጋዛ ጤና ሚኒስቴር ገልጿል።
    • የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጽህፈት ቤት እስራኤል በጃባሊያ የስደተኞች መጠለያ ላይ የፈጸመቻቸውን የአየር ጥቃቶች አውግዞ፣ የሞቱ ሰላማዊ ሰዎችም አኃዝም በእስራኤል የተፈጸመ "የጦርነት ወንጀል" ሊሆን እንደሚችልም ጠቅሷል።
    • የእስራኤል መከላከያ 162ኛ ዲቪዥን አዛዥ ጄነራል ኢትዚክ ኮኸን ጦሩ ወደ ጋዛ በጥልቀት እየገባ እንደሆነ ተናግረዋል።
  20. በጃባሊያ የስደተኞች ጣቢያ የተገደሉ ፍልስጥኤማውያን ቁጥር መጨመሩ ተገለጸ

    የስደተኞች መጠለያ በሆነው ጃባሊያ ሰሜናዊ ክፍል እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ ተገለጸ።

    በጋዛ የሚገኘውና በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር የሟቾች ቁጥር መጨመሩን ገልጿል።

    በጃባሊያ ላይ እስራኤል ላለፉት ሁለት ቀናት ተከታታይ የአየር ጥቃት ፈጽማለች።

    እስራኤል በስደተኞች ማቆያው ከፈጸመችው ጥቀት በኋላ 1,000ሰዎች መገደላቸው፣ መጎዳታቸው ወይም የት እንዳሉ እንዳልታወቀ ተገልጿል።

    ምን ያህሉ ሰዎች እንደሞቱ፣ እንደተጎዱና እንደጠፉ ባይገለጽም ከዚህ ቀደም የሟቾች ቁጥር 195 እንደደረሰ ተገልጿል።

    ያሳለፍነው ማክሰኞ እና ረቡዕ በደረሱት ጥቃቶች ብዙ ሕንጻዎች ተጎድተዋል።

    የእስራኤል መከላከያ በበኩሉ የሐማስ ኮማንደርን ዒላማ እንዳደረገና ብዙ ተዋጊዎችን እንደገደለ አስታውቋል።