የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣን በጋዛ ‘ደኅንነቱ የተጠበቀ’ ቦታ የለም አሉ

የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣን በጋዛ ‘ደኅንነቱ የተጠበቀ’ ቦታ የለም አሉ። ይህ የተባለው የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ከሐማስ ጋር አየተደረገ ባለው ግጭት ጊዜያዊ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እየቀረቡ ያሉትን ጥሪዎች ውድቀ ማድረጋቸው ከተሰማ በኋላ ነው።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ቦሊቪያ ከእስራኤል ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋረጠች

    ቦሊቪያ በጋዛ ደረሰ ባለችው “አስከፊ እና ተመጣጣኝ ያልሆነ” ጥቃት ምክንያት ከእስራኤል ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙት ማቋረጧን አስታወቀች።

    ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍሬዲ ማማኒ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "የእስራኤል ጦር በጋዛ ሰርጥ ላይ እየደረሰ ያለውን አጸያፊ እና ተመጣጣኝ ያልሆነ ጥቃት ለመቃወም እና ለማውገዝ " አገራቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማቋረጥ ምክንያት እንደሆናት ተናግረዋል።

    በሌላ መረጃ ደግሞ ኮሎምቢያ እና ቺሊ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ በእስራኤል የሚገኙ አምባሳደሮቻቸውን ጠርተዋል።

    የቺሊው ፕሬዝዳንት ጋብርኤል ቦሪስ ፎንትስ በኤክስ ላይ እንዳሰፈሩት አገራቸው የእስራኤልን "ተቀባይነት የሌለውን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ህግ ጥሰቶችን" ታወግዛለች።

    የኮሎምቢያው ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔትሮም በተመሳሳይ በኤክስ ላይ “እስራኤል በፍልስጤም ላይ የምታደርሰውን እልቂት ካላቆመች ግንኙነት ሊኖረን አይችልም” ሲሉ ጽፈዋል።

  2. ሳዑዲ በጃባሊያ የስደተኞች ጣቢያ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አወገዘች

    ሳዑዲ አረቢያ በጃባሊያ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ላይ እስራኤል የፈጸመችውን “ኢሰብዓዊ” ጥቃት አወገዘች።

    የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የእስራኤል የአየር ጥቃት ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው "ሰላማዊ ሰዎች ሞት እና ጉዳት ምክንያት ሆኗል" ብሏል።

    እስራኤል በስደተኞች መጠለያ ጣቢያው ላይ ጥቃቱን ማድረሷን ያረጋገጠች ሲሆን በጥቃቱ ከፍተኛ የሐማስ አመራር እና የቡድኑን መሠረተ ልማት አውድሚያለሁ ብላለች።

    በዚህ ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ120 በላይ እንደሆነ አንድ በስፍራው ያሉ ሐኪም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

  3. እስራኤል በጃባሊያ መጠለያ ጣቢያ ባደረስኩት ጥቃት የሐማስ መሪን ገደልኩ አለች

    የእስራኤል ጦር ጃባሊያ በተሰኘው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጦ በጥቃቱ ከፍተኛ የሐማስ አመራርን ገድያለሁ አለ።

    ጦሩ ኢብራሂም ቢአሪ የተባለ የሐማስ ተዋጊዎች ከፍተኛ አመራርን መግደሉን እና ከመሬት በታች የተቆፈሩ የሐማስ መሠረተ ልማቶችን ማውደሙን አስታውቋል።

    እስራኤል በዚህ መጠለያ ጣቢያ ላይ ጥቃት መፈጸሟ ብዙ እያስተቻት ይገኛል።

    በጋዛ ከሚገኙ ግዙፍ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት ከ50 ያላሱ ሰዎች መገደላቸው የጤና ተቋማት አስታውቋል። በጋዛ ያሉ አንድ ሐኪም ደግሞ 120 አስክሬን ሆስፒታላቸው መቀበሉን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    ይሁን እንጂ ከደረሰው ጉዳት አንጻር የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ከፍ ሊል ይችላል።

    ከስፍራው እየወጡ ያሉ ምስሎች ሕንጻዎች ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረው አሳይተዋል። እንዲሁም ፍንዳታው የደረሰበት ቦታ ትልቅ ጉድጓድ ፈጥሯል።

  4. አንቶኒ ብሊንከን አርብ ወደ እስራኤል ሊያቀኑ ነው

    የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን አርብ ወደ እስራኤል ሊያቀኑ መሆኑ ተገለጸ።

    ከእስራኤል ባለስልጣናነት በተጨማሪ በቀጠናው ከሚገኙ መሪዎች ጋር እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል።

    በጉዟቸው ከፍልስጤም ባለስልጣናት ጋር ስለመነጋገራቸው የተባለ ነገር የለም።

    ባለፉት ሦስት ሳምንታት ውስጥ ብሊንከን ወደ እስራኤል ሲያቀኑ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ይሆናል።

  5. በጋዛ የስደተኞች መጠለያ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ከ50 ያላነሱ ሰዎች ተገደሉ

    ጃባሊያ ተብሎ በሚጠራው የስደተኞች መጠያ ጣቢያ ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት ከ50 ያላሱ ሰዎች መገደላቸው የጤና ተቋማት አስታወቁ።

    በሰሜን ጋዛ በሚገኘው መጠለያ ጣቢያ ላይ የደረሰውን ከፍተኛ ውድመት የሚያሳዩ ምስሎች እየወጡ ነው።

    የሮይተርስ ጋዜጠኛ ባጋረው ምስል ሰዎች ወደ ፍርስራሽነት በተቀየሩት ሕንጻዎች ስር በሕይወት የተረፉ ሰዎችን እና አስክሬኖችን ሲያወጡ አሳይቷል።

    በሐማስ የሚተዳደረው ጤና ሚኒስቴር እንዲሁም ከመጠለያ ጣቢያው በቅርብ ርቀት የሚገኝ የኢንዶኔዢያ ሆስፒታል ዳይሬክተር በጥቃቱ ከ50 ያላነሱ ሰዎች መገደላቸውን ገልጸዋል።

    ጃባሊያ መጠለያ ጣቢያ በጋዛ ከሚገኙት 8 መጠለያ ጣቢያዎች በርካታ ሰዎችን በመያዝ ቀዳሚው ሲሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት ሐምሌ 2015 ዓ.ም. ላይ በመጠለያ ጣቢያው የተጠለሉ 116ሺህ ፍልስጤማውያን መዝግቦ ነበር።

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል ጥቃቱን በተመለከተ እስካሁን ያለው ነገር የለም።

  6. በእስራኤል ላይ የምንፈጽመው ጥቃት ይቀጥላል፡ የየመን ሁቲ ታጣቂዎች

    የየመን ሁቲ አማጺያን “በርካታ ቁጥር ያለው” ተወንጫፊ ባሊስቲክ ሚሳኤል እና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ወደ እስራኤል ማስፈንጨፋቸውን አስታወቁ።

    የሁቲ አማጺያን ዛሬ ማክሰኞ ከደቡብ-ምሥራቅ እስራኤል በመቶ ኪሎ ሜትሮች ርቃ ከምትገኘው የመን ከዒላማቸው ጋር እየተላተሙ ጉዳት የሚያደርሱ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ማስወንጨፋቸውን አስታውቀው ነበር።

    ቀደም ሲል እስራኤል ኤላት የተሰኘችውን የጎብኚዎች መዳረሻ የሆነችውን ከተማዋን ዒላማ ያደረጉ ድሮኖችን ቀይ ባሕር ላይ መትታ መጣሏን አስታውቃለች።

    በኤላት የአየር ጥቃት ስጋት መኖሩን ተከትሎ የማስጠንቀቂያ ድምጾች በተከማዋ ተስተጋብተው ነበር።

    የሁቲ ጦር ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ በቴሌቪዥን በተሰራጨ መግለጫ፣ እራኤልን ዒላማ ያደረገው ይህ ጥቃት ሦስተኛው መሆኑን እና ተጨማሪ ጥቃቶች እንደሚሰነሩ ጨምረው ተናግረዋል።

    የሁቲ ኃይል “የእስራኤል ጥቃት እስኪቆም ድረስ ልዩ የሆኑ ዘመቻዎችን ማካሄዳቸውን ይቀጥላሉ” ብለዋል ቃል አቀባዩ።

    በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አማጺያን የየመን መዲና ሰነዓን ጨምሮ በርካታ የአገሪቱ አካባቢዎችን የሚቆጣጠሩ ሲሆን፣ አስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከሳዑዲ መራሹ ኃይል ጋር ጦርነት ውስጥ መቆየታቸው ይታወሳል።

    ባለፈው ሳምንት በሁለት የግብፅ ከተሞች ውስጥ ላጋጠሙ ፍንዳታዎች እስራኤል ይህን ቡድን ተጠያቂ አድርጋ ነበር።

    ለእስራኤል ተብለው የሁቲ አማጺያን የተተኮሱት ኢራን ሰራሽ ድሮኖች በሁለቱ የግብፅ ከተሞች ላይ ፍንዳታ መፍጠራቸውን እስራኤል ገልጻለች።

  7. እስራኤል በጋዛ ባካሄድኩት ዘመቻ “በርካታ አሸባሪዎችን ገደልኩ” አለች

    የእስራኤል ጦር በጋዛ ባካሄደው ዘመቻ በርካታ የሐማስ ተዋጊዎችን መግደሉን አስታወቀ።

    ጦሩ ባለፉት ጥቂት ሰዓታት ባወጣው ሪፖርት “በሰሜናዊ ጋዛ ሰርጥ የአሸባሪው ሐማስ ወታደራዊ የቅኝት ጣቢያን” መምታቱን አስታውቋል።

    የእስራኤል እግረኛ ጦር ባካሄደው ዘመቻ “በርካታ አሸባሪዎችን” መግደሉን፣ ፀረ ታንክ ሚሳኤል የሚያስወነጭፉ ቡድኖችን መደምሰሱን፣ ሚሳኤል ማስወንጨፊያ እና የወታደራዊ ቅኝት ጣቢያዎችን ማውደሙን እንዲሁም በርካታ መሳሪዎች እና ቦምቦችን መማረኩን አስታውቋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ ሐማስ በበኩሉ በጋዛ በተደረገ ውጊያ አንድ የእስራኤል ወታደር መግደሉን እና ታንክ ማጋየቱን አስታውቋል።

    ሐማስ በሰሜን ምዕራብ ጋዛ ዘልቀው ለመግባት የሞከሩ ሁለት የእስራኤል ጦር ተሸከርካሪዎችን ማውደሙን ጨምሮ ገልጿል።

  8. የእስራኤል አየር መንገድ ከኢራን አየር ክልል ለመራቅ የበረራ አቅጣጫውን ቀየረ

    የእስራኤል አየር መንገድ የሆነው ኤል ኤአይ ሐማስን በመደገፍ ከምትታወቀው ኢራን የአየር ክልል ለመራቅ ሲል የበረራ አቅጣጫውን ቀየረ።

    አሶሺዬትድ ፕሬስ እንደዘገበው የአየር መንገዱ የመንገደኞች አውሮፕላን ወደ ታይላንድ በነበረው በረራ የተለመወደውን የበረራ አቅጣጫውን በመቀየሩ የበረራ ጊዜው በሰዓታት ተራዝሟል።

    አየር መንገዱ ከዚህ ቀደም እንደሚያደርገው ከኢራን በቅርብ ርቀት በምትገኘው በኦማን የአየር ክልል አድርጎ ነበር ወደ መዳረሻው ይበር የነበረው።

    ይሁን እንጂ አውሮፕላኑ በቅድሚያ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ከበረራ በኋላ፣ በቀይ ባሕር በኩል አድርጎ ወደ አፍሪካ ቀንድ ከዚያም ወደ ሕንድ ውቅያኖስ ፊቱን አዙሮ ወደ መዳረሻው አቅንቷል።

  9. በጋዛ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከ8 ሺህ በላይ ሆነ

    በእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት ምክንያት በጋዛ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከ8ሺህ በላይ ማለፉ ተገለጸ።

    በሐማስ የሚተዳደረው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር ከመስከረም 26 ጀምሮ በጋዛ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 8525 ደርሷል ብሏል።

    እንደ ጤና ሚኒስቴሩ ከሆነ ከሟቾቹ መካከል 3542 ያህሉ ሕጻናት ሲሆኑ፣ 2187 ሴቶች ናቸው ብሏል። 130 የሚሆኑት ደግሞ የጤና ባለሙያዎች መሆናቸው ተገልጿል።

    ሐማስ ከጥቂት ቀናት በፊት በእስራኤል የአየር፣ የምድር እና የባሕር ላይ ጥቃቶች የተገደሉ ናቸው ያላቸው የ7ሺህ ሰዎች ስም ዝርዝር ይፋ አድርጎ ነበር።

  10. ሐማስ “ከፍልስጤማውያን ጀርባር ተደብቋል” ስትል እስራኤል ከሰሰች

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ “ሐማስ ከፍልስጤማውያን ጀርባ ተደብቋል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናገሩ።

    ቃል አቀባዩ ፒተር ለርነር እንዳሉት ሐማስ ሰላማዊ ሰዎች በሚኖሩበት አካባቢ መሽጓል።

    “የሚፈነዱ ሰው አልባ አውሮፕላኖቹን ጨምር በሰዎች መኖሪያ ቤት ጣሪያ ላይ አከማችቷል። . . . ሮኬቶችን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት እያስወነጨፈ ነው” በማለት ቃል አቀባዩ ቡድኑን ወቅሰዋል።

    በሁለቱም በኩል በግጭቱ ምክንያት ጉዳዩ የማይመለከታቸው ሰላማዊ ሰዎች እየተጎዱ መሆኑን የገለጹት ፒተር ለርነር፤ ሐማስ መወገድ ካለበት ምክንያቶች መካከል አንዱ በሰላማዊ ሰዎች ስር መሸሸጉ አንዱ ነው ብለዋል።

    ቃል አቀባዩ ጨምረውም ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከሰነዘረ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከ7ሺህ በላይ ሮኬቶችን ከጋዛ ማስወንጨፉን ተናግረዋል።

    ይህ ቃል አቀባይ ከዚህ ቀደም ሐማስ በጋዛ የሚገኙ ሆስፒታሎችን እንደ ጦር ማዘዣ ጣቢያ እና የመሰባሰቢያ ቀጠና አድርጎ እየተጠቀመ ነው ብለው ነበር።

  11. የተባበሩት መንግሥታት 64 ሰራተኞቹ በጋዛ እንደተገደሉበት አስታወቀ

    የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጥኤም ስደተኞች ኤጀንሲ 64 ሰራተኞቹ በጋዛ እንደተገደሉበት አስታወቀ።

    በትናንትናው ዕለትም አንድ የተመድ ሰራተኛ ከስምንት ልጆቹ እና ከባለቤቱ ጋር በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ እያሉ መገደላቸውን ቃለ አቀባይዋ ጁሊየት ቶውማ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    በጋዛ ሰርጥ የተባበሩት መንግሥታት የሚያስተዳድራቸው 450 መጠለያዎች ያሉ ሲሆን እነዚህም መጨናነቃቸውን ቃለ አቀባይዋ ተናግረዋል።

    እነዚህ መጠለያዎች 670 ሺህ ፍልስጥኤማውያንን እያስተናገደ ነው ተብሏል።

    “እንደ እከክ እና ተቅማጥ የመሳሰሉ በሽታዎች እየተዛመቱ መሆናቸውንም ሪፖርቶች ደርሰውናል” ብለዋል።

    “የሰብዓዊ ተኩስ አቁም መደረግ አለበት። ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገቡ አብያተ ክርስቲያናት፣ መስጂዶች እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት ተመትተዋል። የትኛውም የጋዛ ስፍራ ደህንነቱ የተጠበቀ አይደለም። ጋዛ በፍጥነት ወደ ገሐነም ተቀይራለች” በማለትም ተናግረዋል።

    እስራኤል ሐማስ ላደረሰው መብረቃዊ ጥቃት ምላሽ ነው በሚል በጋዛ ላይ የማያባራ የአየር እና የመሬት ጥቃት እየፈጸመች ትገኛለች።

    ሐማስ ባደረሰው ጥቃት 1 ሺህ 400 ሰዎች ተገድለዋል እንዲሁም ከ200 በላይ ሰዎች ታግተዋል። በእስራኤል ጥቃት ከ8 ሺህ በላይ ፍልስጥኤማውያን የተገደሉ ሲሆን፣ ከእነዚህም አብዛኛዎቹ ሕጻናት እና ሴቶች መሆናቸውን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

    እስራኤል ጋዛን በሙሉ ከበባ ውስጥ ያስገባቻት ሲሆን በዚህም የነዳጅ፣ የመብራት እና የውሃ አቅርቦት እንዲቋረጥ አድርጋለች።

  12. አሜሪካ የጋዛ የተኩስ አቁም ጥሪን ውድቅ አደረገች

  13. የእስራኤል መከላከያ የጋዛ ሰርጥ ላይ ከሁሉም አቅጣጫ ጥቃት እያደረስኩ ነው አለ

    እስራኤል ለሶስት ሳምንታት ከቀጠለችው የማያባራ የአየር ጥቃት በተጨማሪ እግረኛ ጦሯ ከፍተኛ ጥቃት እያደረሰ መሆኑን አስታውቃለች።

    በትናንትናው ዕለትም 300 የሚጠጉ ኢላማዎችን በአየር ጥቃት እና በእግረኛ ጦሯ መምታቱን የእስራኤል መከላከያ ኃይል ገልጿል።

    የእስራኤል ጦር ሁሉንም የጋዛ ሰርጥ አካባቢዎችን እየመታ መሆኑንም የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት ቃለ አቀባይ ሌተናል ኮሎኔል ጆናታን ተናግረዋል።

    "ዋናው ትኩረታችን ሰሜናዊው ጋዛ ሐማስ ማዕከል ያደረገው ስፍራ ነው። ነገር ግን ሌሎች የጋዛ አካባቢዎችን መምታታችንን እንቀጥላለን።

    አዛዦቻቸውንን እያደንን ነው። መሰረተ ልማቶቻቸውን እያጠቃን ነው፤ አስፈላጊ ዒላማ ሲገኝ እንመታዋለን" ሲሉም ነው የተናገሩት።

    እስራኤል የንጹሐን ዜጎችን ግድያ ለማስቀረት የተቻላትን ሁሉ እያደረገች እንደሆነ የገለጹት ቃለ አቀባዩ ሐማስ የጋዛ ዋና ሆስፒታል አል ሺፋን ሽፋ "የአሸባሪዎች መደበቂያ" አድርጎታል ሲሉም ከሰዋል።

    እስራኤል በሰሜናዊ ጋዛ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማውያንን ከዋዲ ጋዛ ወንዝ በስተደቡበ በኩል እንዲሸሹ ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች።

    ሆኖም እስራኤል በሰሜን ጋዛ ብቻ ሳይሆን ደቡብ ጋዛም ላይ የማያባራ የአየር ጥቃት መፈጸሟን በመቀጠሏ የተባበሩት መንግሥታት በጋዛ "ደህንነቱ የተጠበቀ ቦታ የለም" ብሏል።

    ሰኞ ዕለት የእስራኤል መከላከያ ኃይል ሰሜን ጋዛን የወረሩ ሲሆን በስፍራውም ከ600 ሺህ በላይ ፍልስጥኤማውያን ይኖራሉ ተብሏል።

    የእስራኤል መከላከያ ታንኮች ወደ ሰሜን ጋዛም ሲገባ የደቡብ መተላለፊያውን መንገድ ለአጭር ጊዜ ቆርጠውት እንደነበር የዓይን እማኞች ተናግረዋል።

  14. ሌሊቱን ጋዛ ውስጥ ከሐማስ ኃይሎች ጋር ‘ከፍተኛ’ ውጊያ ሲካሄድ እንደነበር እስራኤል ገለጸች

    ከቀናት በፊት ወደ ጋዛ የገባው የእስራኤል እግረኛ ጦር ጋዛ ውስጥ በሐማስ ይዞታዎች ላይ የሚያካሂደውን ጥቃት ሌሊቱን አጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ ‘ትላልቅ’ ውጊያዎች መካሄዳቸው አመልክቷል።

    እስራኤል እንዳለችው ጋዛ ውስጥ ከሐማስ ተዋጊዎች ጋር “የጎላ የተኩስ ልውውጥ” መካሄዱን እና ወታደሮቿ በሰሜን ጋዛ ውስጥ የሚያካሂዱትን ዘመቻ “በዝግታ እና ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ” እያሰፉ ናቸው።

    ፒተር ለርነር የተባሉ የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ጋዛ ውስጥ “ከፍተኛ መጠን ያለው የተኩስ ልውውጥ” በእስራኤል እና በሐማስ ኃይሎች መካከል ሌሊቱን ተካሂዷል።

    ሌላኛው የሠራዊቱ ቃል አቀባይ ሌተናል ኮሎኔል ጆናታን ኮንሪከስ የእስራኤል ኃይሎች በአየር እና በምድር ዘመቻውን እያካሄዱ ያሉት በከፍተኛ የተኩስ ኃይል እና በመረጃ ተደግፈው መሆኑን ገልጸዋል።

    ቃል አቀባዩ አክለውም ጦሩ ጥቃቱን “የሐማስ ዋነኛ ማዕከል ነው” ባሉት ሰሜናዊ የጋዛ ሰርጥ ላይ በማተኮር “በሁሉም የጋዛ ሰርጥ ክፍሎች ላይ እየፈጸመ ነው” ብለዋል።

    ሌሊቱን የእስራኤል ወታደሮች ከሐማስ ኃይሎች ጋር ጋዛ ውስጥ መዋጋታቸውን እና በሐማስ የፀረ ታንክ ሚሳኤል እና የመትረየስ ጥቃት ተሰንዝሮበት እንደነበር ሠራዊቱ ገልጿል።

    በተመሳሳይ የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ አል-ቃሳም ብርጌድ በቴሌግራም ላይ ተመሳሳይ መረጃ አጋርቷል። በዚህም የቡድኑ ተዋጊዎች ሰሜናዊ ጋዛ ውስጥ ሦስት የእስራኤል የጦር ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጿል።

    መረጃው አክሎም ተሽከርካሪዎቹ ወደ ጋዛ ዘልቀው ለመግባት አል-ታዋም በተባለው አካባቢ ሲንቀሳቀሱ ፀረ ታንክ ሚሳኤል ተተኩሶባቸዋል ብሏል።

    ቀደም ብሎ ባጋራው መረጃ በደቡባዊ ጋዛ ኬሬም መተላለፊያ አቅራቢያ በእስራኤል እግረኛ ጦር ላይ የሞርታር ጥቃት እንደፈጸመ ሐማስ ገልጾ ነበር።

  15. ፑቲን በአገራቸው ለተፈጠረው ጸረ-አይሁድ እንቅስቃሴ ምዕራባዊያንን ተጠያቂ አደረጉ

  16. የፍልስጥኤም ደጋፊዎች የካናዳ መንግሥታዊ ቢሮዎችን ያዙ

    በመላው ካናዳ ያሉ ሰብዓዊ ተሟጋቾች በጋዛ የተኩስ አቁም ጥሪ እንዲደረግ ለመጠየቅ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት የሆኑ ቢሮዎችን ይዘዋል።

    የፓርላማ አባላቱ የተኩስ አቁም ጥሪ እንዲያቀርቡ ጫና ለማድረግም ነው ተሟጋቾቹ በነዚህ የመንግሥት ባለስልጣናት ቢሮዎች የተቀመጡት።

    ተሟጋቾቹ ሰኞ እለት ከያዟቸው ቢሮዎች መካከል የመከላከያ ሚኒስትሩ ቢል ብሌየር እና የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ክሪስቲያ ፍሪላንድ ይገኙበታል።

    ተቃውሞው የተካሄደው በመላ ሃገሪቱ ባሉ 12 ከተሞች በሚገኙ 17 የመንግሥት መስሪያ ቤቶች መሆኑንም የሞንትሪያል ጋዜጣ ዘግቧል።

    "የካናዳ መንግሥት በጋዛ ላይ የተኩስ አቁም ጥሪ እንዲያደርግ እንዲሁም በጋዛ ሰርጥ ላይ ለ16 ዓመታት የቀጠለው እገዳ እና ከበባ እንዲቆም እንዲሁም ካናዳ ለእስራኤል የምታሳየውን አጋርነት እንድታቆም ለመጠየቅ ነው" ሲሉም አንድ ተቃዋሚ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

    ተቃዋሚዎቹ በጋዛ ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ጭፍጨፋ እንዲቆም እና ነጻ ፍልስጥኤምን የሚጠይቁ መፈክሮችን ይዘዋል።

  17. የዩኬ ባለሥልጣን ‘በጋዛ ተኩስ አቁም ይደረግ’ በማለታቸው ከሥራ ተባረሩ

  18. በጦርነቱ ከተገደሉት 31 ጋዜጠኞች መካከል 26ቱ ፍልስጥኤማውያን ናቸው

    በእስራኤል- ጋዛ የተፈጠረውን ቀውስ በመዘገብ ላይ የነበሩ 31 ጋዜጠኞች የተገደሉ ሲሆን ከነዚህም ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው የፍልስጥኤማውያን መሆኑን የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪው ሲፒጄ መረጃ ያሳያል።

    26 ፍልስጥኤማውያን፣ 4 እስራኤላውያን እና 1 የሊባኖስ ዜጋ የዘገባ ስራቸውን በማከናወን ላይ እያሉ መገደላቸውን ነው ተቋሙ ያስታወቀው።

    ተጨማሪ ስምንት ጋዜጠኞች የቆሰሉ ሲሆን ዘጠኝ ደግሞ እንደጠፉ ወይም ታስረው ሊሆን እንደሚችል ነው ሲፒጄ በመግለጫው አስፍሯል።

    በተለይም በጋዛ የሚዘግቡ ጋዜጠኞች በከፍተኛ ፈተናው ውስጥ እንደሆኑም አስፍሯል።

    "እስራኤል በመሬት ላይ እየፈጸመች ያለችውን ከባድ ጥቃት፣ አውዳሚ የአየር ድብደባዎች፣ እንዲሁም የመገናኛ ዘዴዎች እና የኤሌክትሪክ አቅርቦት በሚቆራረጥበት ሁኔታ እየዘገቡ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ አደጋም ተደቅኖባቸዋል" ብሏል።

    ከተገደሉት መካከል ታዋቂው ፍልስጥኤማዊ ፊልም ሰሪ ሮሽዲ ሳራጅ፣ በቤይሩት የሮይተርስ የቪዲዮ ባለሙያ ኢሳም አብዳላህ ይገኙበታል ።

    እስራኤል በሊባኖስ ላይ በፈጸመችው የከባድ መሳሪያ ጥቃትም በቤይሩት የነበረው የሮይተርስ ጋዜጠኛ እንደተገደለ ሲፒጄ አትቷል።

    የእስራኤል መከላከያ ጉዳዩን እየመረመርኩ ነው ብሏል። የእስራኤል መከላከያ በጋዛ ሰርጥ ውስጥ ለሚሰሩ ጋዜጠኞቻቸው ደህንነት ዋስትና እንደማይሰጥም ለሮይተርስ እና አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግሯል።

    መከላከያው ይህንን የተናገረው ሰራተኞቻቸው በእስራኤል ጥቃት ጉዳት እንዳማይደርስባቸው የዜና ወኪሎቹ መጠየቃቸውን ተከትሎም እንደሆነ ሮይተርስ ዘግቧል።

  19. እግረኛ ጦሯን ወደ ጋዛ ያሰማራችው እስራኤል የምትፈልገውን ግብ ማሳካት ትችላለች?

  20. እስራኤል በሐማስ ታግታ የነበረች ወታደሯን ነጻ ማውጣቷን አስታወቀች

    እስራኤል በሐማስ ታግታ ተወስዳ የነበረች ሴት ወታደሯን ማስለቀቅ መቻሏን ዛሬ ሰኞ ምሽት በተሰጠ መግለጫ አስታወቀች።

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል እና የእስራኤል ደኅንነት ባለሥልጣን በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይ ነው በሐማስ ቁጥጥር ስር የነበረችውን ወታደር ነጻ መውጣት መቻሉን ያስታወቁት።

    ኦሪ ሜጊዲሽ የተባለችው ወታደር መስከረም ወር መጨረሻ ላይ ሐማስ ከፈጸመው ጥቃት ጋር በተያያዘ ከታገቱ ሰዎች መካከል አንዷ ስትሆን፣ የእስራኤል እግረኛ ጦር ትናንት ሌሊት ባካሄደው ዘመቻ ነው ነጻ ሊያወጣት የቻለው ተብሏል።

    የወታደሯን ነጻ መውጣት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ በኤክስ (ትዊተር) ላይ "እንኳን ወደ ቤትሽ ተመለስሽ" በማለት የቪዲዮ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    የወታደሯ መለቀቅም ታጋቾችን ለማስለቀቅ የአገራቸውን ቁርጠኝነት በመግለጽ፣ ሐማስ ላይም እስራኤል የቡድኑን አባላቱ ዒላማ ማድጓን እንደምትቀጥል ዝተዋል።

    “የወታደሯ ጤና በደህና ሁኔታ ላይ ነው ያለው፣ ከቤተሰቦቿ ጋርም ተገናኝታለች። ጦሩ እና የደኅንነት ተቋሙ ሁሉንም ታጋቾች ለማስለቀቅ የሚያስፍልጉ ሁሉንም ነገሮች ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ” ብሏል በጋራ የወጣው መግለጫ።