ትራምፕ ሆርሙዝ እንዲከፈት የጊዜ ገደብ ሲያስቀምጡ ኢራን ደግሞ ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የኢነርጂ ጣቢያዎች ለማጥቃት ዛተች

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥን እንድትከፍት የ48 ሰዓት የጊዜ ገደብ አስቀመጡ። ኢራን በበኩሏ በኃይል ማመንጫዎቿ ላይ ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ በባሕረ ሰላጤው የሚገኙ እና ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የኢነርጂ ጣቢያዎች እንደምታጠቃ አስጠንቅቃለች።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ልጃቸው ሥልጣን በመረከባቸው ላይ ስጋት እንደነበራቸው ተነገረ

    የኢራን የቀድሞ የጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ልጃቸው እርሳቸውን ስለመተካታቸው ጥርጣሬ እንደነበራቸው የአሜሪካ ደኅንነት መረጃ እንደነበረው ምንጮች ለቢቢሲ የአሜሪካ የሚዲያ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ ተናገሩ።

    መረጃው ኻሜኒ ልጃቸው ሞጅታባ ኻሜኒ “ብቃት እንደሌለው” እና ለመሪነት “ብሩህ አይደለም” ተብሎ ስለሚታሰብ ሥልጣን መረከቡ ላይ ስጋት ነበራቸው ተብሏል።

    በተጨማሪም ሟቹ የበላይ መሪ ልጃቸው "በግል ሕይወቱ ውስጥ ችግሮች እንዳሉበት" እንደሚያውቁ ተጠቅሷል።

    ሲቢኤስ እንደዘገበው መረጃው አስቀድሞ ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና "በዙሪያቸው ላሉ ጥቂት ሰዎች” ደርሷል።

    የ56 ዓመቱ አያቶላህ ሞጅታባ ኻሜኒ ከአንድ ሳምንት በፊት የኢራን የበላይ መሪ እንዲሆኑ መመረጣቸው ይታወሳል።

  2. እስራኤል በኢራን በሺህዎች የሚቆጠሩ ዒላማዎች እንደሚቀሯት ስትናገር ትራምፕ ከስታርመር ጋር ስለ ሆርሙዝ መከሩ

    የእስራኤል ጦር በኢራን ውስጥ “በሺህዎች” የሚቆጠሩ ዒላማዎችን ገና መደብደብ እንደሚቀረው የአገሪቱ ጦር ቃል አቀባይ ኤፊ ደርፊን ተናገሩ።

    ቃል አቀባዩ በቴሌቪዥን በተላለፈው መግለጫቸው ላይ “በየዕለቱ አዳዲስ ዒላማዎችነ እየለየን ነው” ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

    ሮይተርስ አክሎም የእስራኤል ጦር “ኢራን እና ሔዝቦላህ ላይ የሚፈጽማቸውን ጥቃቶች ስጋቱ እስኪወገድ እና የዘመቻው ዓላማዎች እስኪሳኩ ድረስ ይቀጥላል” ማለታቸውን ዘገቧል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር እና የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመካለኛው ምሥራቅ ስላለው ሁኔታ እና የሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥን ማስከፈት አሰፈላጊነት ላይ መወያየታቸውን የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

    ሁለቱ መሪዎች ያደረጉት የስልክ ውይይት ለ15 ደቂቃ የዘለቀ ነው የተባለ ሲሆን፣ ከሆርሙዝ ወሽመጥ በተጨማሪ ስታርመር “በጦርነቱ ሕይወታቸውን ላጡ አሜሪካውያን ሞት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል” ተብሏል።

    የካናዳው ጠቅላይ ሚኒሲትር ካርኒ እንዲሁ ከስታርመር ጋር "እየተካሄደ ባለው ጦርነት ዙሪያ “ለመነጋገር መስማማታቸው ተገልጿል።