ትራምፕ ሆርሙዝ እንዲከፈት የጊዜ ገደብ ሲያስቀምጡ ኢራን ደግሞ ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የኢነርጂ ጣቢያዎች ለማጥቃት ዛተች

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥን እንድትከፍት የ48 ሰዓት የጊዜ ገደብ አስቀመጡ። ኢራን በበኩሏ በኃይል ማመንጫዎቿ ላይ ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ በባሕረ ሰላጤው የሚገኙ እና ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የኢነርጂ ጣቢያዎች እንደምታጠቃ አስጠንቅቃለች።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በኢራን የሟቾች ቁጥር 3100 ማለፉን የሰብዓዊ መብቶች ኤጀንሲ አስተወቀ

    መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የሰብዓዊ መብቶች አክቲቪስቶች የዜና ኤጀንሲ (ሂርና) በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነቱ ከጀመረበት ከየካቲት 21 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በኢራን የሞቱ ሰዎች ቁጥር 3186 መድረሱን አስታውቋል።

    ከእነዚህ መካከል 1394 ሰላማዊ ሰዎች መሆናቸውን የገለጸ ሲሆን 210 ደግሞ ሕጻናት እንደሆኑ ሂርና ይፋ አድርጓል።

    በአሜሪካ እና እስራኤል ዒላማ ከተደረጉት መካከል 1153 ወታደራዊ ተቋማት መሆናቸው የገለጸው የዜና ወኪሉ እስካሁን ድረስ የ639 ሰዎች ሞት አልተመዘገበም ብሏል።

  2. ትራምፕ እግረኛ ወታደሮችን ወደ ኢራን እንደማያሰማሩ እና ጦርነቱ “ከታቀደለት ጊዜ ፈጥኖ እየተካሄደ ነው” አሉ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመካለኛው ምሥራቅ የትኛውም ቦታ የእግረኛ ጦራቸውን እንደማያሰማሩ ተናገሩ።

    ትራምፕ ሦስት ሳምንት ሊሞላው የተቃረበው በኢራን ላይ የሚካሄደው ጦርነት “ከታቀደለት ጊዜ ፈጥኖ እየተካሄደ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

    ፕሬዝዳንቱ የአሜሪካ ወታሮች ይሰማሩ እንደሆነ ጥያቄውን ላቀረቡላቸው ጋዜጠኞች በሰጡት ምላሽ "ብናቅድ እንኳ አልነግርህም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

    ትራምፕ ይህንን ያሉት ከጃፓኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳናኤ ታካኢቺ ጋር በዋይት ሐውስ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው።

    የጃፓኗ ጠቅላይ ሚኒስትር በዓለም ላይ ሰላምን ሊያሳኩ የሚችሉት ትራምፕ “ብቻ ናቸው” ሲሉ ተደምጠዋል።

    አክለውም ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንድታበለጽግ “በጭራሽ ሊፈቀድላት አይገባም” ብለዋል።

    ታካኢቺ የጃፓን ባለሥልጣናት ኢራን በኢነርጂ መሠረተ ልማቶች ላይ የምትፈጽማቸውን ጥቃቶች እንድታቆም በቀጥታ መጠየቃቸውን ተናግረዋል።

  3. የነዳጅ ማምረቻዎችን ዒላማ እያደረጉ ያሉት ጥቃቶች

    በባሕረ ሰላጤው የሚካሄደው ጦርነት ሦስተኛ ሳምንቱን ሊደፍን በተቃረበበት ጊዜ ተፋላሚዎቹ ወገኖች የነዳጅ ምርት ማዕከላትን ዒላማ እያደረጉ ነው።

    ጦርነቱ ሲጀመር በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚተላለፉ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች አደጋ ላይ ይወድቃሉ የሚል ስጋት የነበራቸው ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ መርከቦች ወደ አካባቢው ለመንቀሳቀስ ሳይችሉ ቀርተዋል።

    የዓለም 20 በመቶ የነዳጅ ምርት በሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ በተፈጠረው መስተጓጎል የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ ነው።

    አሁን ደግሞ ከፍተኛ ነዳጅ በሚመረትባቸው የፋርስ ባሕረ ሰላጤ አገራት የነዳጅ ማምረቻዎች ላይ አሜሪካ፣ እስራኤል እና ኢራን ጥቃት መፈጸም በመጀመራቸው ዓለምን ስጋት ላይ ጥለዋል።

    ይህ ቪዲዮ ከአንድ የሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ማጣሪያ አቅራቢያ የተከሰተ ፍንዳታን ያሳያል።

  4. አሜሪካ በኢራን ነዳጅ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ለማንሳት እያሰበች መሆኑ ተገለጸ

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሴንት አሜሪካ የነዳጅ ዋጋን ለማረጋጋት በኢራን ነዳጅ ላይ የጣለችወን ማዕቀብ ልታነሳ እንደምትችል ተናገሩ።

    ባለሥልጣኑ ለፎክስ ቢዝነስ በሰጡት ቃለ ምልልስ ወቅት ይህ እርምጃ በመርከብ ላይ ተጭኖ ያለ 140 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅን ተጠቃሚ ሊያደርግ እንደሚችል ተናግረዋል።

    የዓለም ሕዝብ በቀን 100 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ይጠቀማል ተብሎ ይገመታል።

    ቤሴንት የነዳጅ ዘይት አቅርቦትን ለማሻሻል በሩሲያ ነዳጅ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ለማንሳት እንዲሁም ከመጠባበቂያ ክምችት 172 ሚሊዮን በርሜል ለዓለም ገበያ ለመልቀቅ በመፍትሄነት መቀመጣቸውን ተናግረዋል።

    ቤሴንት ቀደም ሲል ጦርነት እየተካሄደ ቢሆንም አሜሪካ የኢራን ነዳጅ ጫኝ መርከቦች እንዲያልፍ እንደምትፈቅድ ተናግረው ነበር።

    ይህ የአሜሪካ እርምጃ በዓለም የነዳጅ ዋጋ ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንድሚኖረው ግልጽ አይደለም።

    ቤሴንት አሜሪካ ይህ እርምጃዋ ጠላቷን በገንዘብ ይደግፋል የሚል ስጋት የላትም ወይ ተብለው ሲጠየቁ አሜሪካ በሚቀጥሉት 10 እና 14 ቀናት የነዳጅ ዋጋን በመቀነስ “የኢራንን ነዳጅ ከኢራን በተቃራኒ እንዲቆም” ታደርጋለች ብለዋል።

  5. የዩኬ መከላከያ ሚኒስትር ኢራን በባሕረ ሰላጤው የኢነርጂ ተቋማት ላይ የፈጸመችው ጥቃት ግጭቱን "የበለጠ የሚያባብስ" ነው አሉ

    ኢራን በአካባቢው የሚገኙ የነዳጅ ማምረቻ ጣቢያዎችን ካጠቃች በኋላ ብሪታንያ ለባሕረ ሰላጤው አገራት የመከላከያ ድጋፏን "እያጠናከረች" ነው ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትሩ ጆን ሂሌይ ተናገሩ።

    ቴህራን ሌሊቱን የፈጸመችው ጥቃት "ቀጣናውን የበለጠ ለማወክ" የሚያሰጋ እና ግጭቱን "የበለጠ የሚያባብስ" እንደሆነ ጨምረው ተናግረዋል።

    "እዚህ በኑሮ ውድነት እና በነዳጅ ዋጋ ላይ ያለውን ተጽእኖ ማየት እንችላለን፤ ስለዚህ ወሽመጡን እንደገና ለመክፈት በሚደረገው ጥረት ውስጥ መሳተፍ ከሚፈልጉ ሌሎች ብዙ አገራት ጋር የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አስፈላጊ ነው" ሲል ሄሊይ ለፔንስልቬንያ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

    በዓለም የነዳጅ ዋጋ ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስ በጣም ጥሩው መንገድ "ግጭቱን ማርገብ እና ማቆም" እንደሆነ ተናግረዋል።

  6. ምዕራባውያን የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመጠበቅ ፈቃደኝነታቸውን ገለጹ

    ዩናይትድ ኪንግደም እና አምስት አገራት በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ ላይ የሚደረግ የነዳጅ መርከቦች ጉዞን ደኅንነት ለመጠበቅ "ተገቢ ጥረቶችን" ለማድረግ "ዝግጁ" መሆናቸውን ገለጹ።

    ዩናይትድ ኪንግደም እና አጋሮቿ በጋራ ባወጡት መግለጫ ኢራን በሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ የምታደርሰውን ጥቃት አውግዘዋል።

    በተጨማሪም በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ ላይ የሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ የምትፈጥረውን ስጋት እንድታቆም ጥሪ አቅርበዋል።

    "በባሕር ላይ የመቅዘፍ ነፃነት የዓለም አቀፍ ሕግ መሠረታዊ መርኅ ነው" ሲሉ የዩኬ፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የጣልያን፣ የኔዘርላንድስ እና የጃፓን መሪዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይ ጠቅሰዋል።

    “የኢራን ድርጊት ውጤት በሁሉም የዓለም ክፍሎች በተለይም በጣም ተጋላጭ የሆኑት እንዲሰማቸው ያደርጋል።”

    ቡድኑ በተጨማሪም የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ መተላለፊያ በሆነው የባሕር ወሽመጥ ላይ ደኅንነቱ እንዲጠበቅ ለማድረግ "ተገቢ ጥረቶችን" ለማድረግ "ዝግጁነቱን" ገልጿል።

    አገራቱ አክለውም "በዝግጅት ዕቅድ ላይ የተሳተፉ አገራት ያላቸውን ቁርጠኝነት በደስታ እንቀበላለን" ብለዋል።

    ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን መዝጋቷን ተከትሎ የዓለም አቀፍ የነዳጅ እና ጋዝ ዋጋ ጭማሪ አሳይቷል።

    በእስራኤል እና በአሜሪካ ለሚፈጸምባት ጥቃት አጸፋ ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የነዳጅ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት እየፈጸመች ነው።

    ይህንንም ተከትሎ ዋና ዋና አገራት በኢራን ላይ የሚካሄደው ጦርነት ያስከተለውን ተጽእኖ ለመግታት በሚል ለድንገተኛ ጊዜ ካስቀመጡት ክምችታቸው ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ ለመልቀቅ ተስማምተዋል።

    ቀደም ሲል የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በሆርሙዝ ሰርጥ ላይ የሚደረግ ጉዞን ለመጠበቅ አገራት የባሕር ኃይላቸውን እንዲያዋጡ ጥሪ አቅርበው ነበር።

  7. የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር በኢራን ላይ እየተካሄደ ስላለው ጦርነት ምን አሉ?

    የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት ከአገሪቱ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ዳን ኬይን ጋር በመሆን አገራቸው በኢራን ላይ ከእስራኤል ጋር በመሆን እያካሄደች ስላለው ጦርነት መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫው ላይ የተነሱት ዋና ዋና ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?

    • የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር አገሪቱ በጦርነቱ ላይ “በዕቅዷ” እና “በዒላማዋ” ላይ መሆኗን ተናግረዋል። ነገር ግን ጦርነቱ መቼ ሊያበቃ እንደሚችል የጊዜ ገደብ ሳያስቀምጡ ቀርተዋል። ግልጽ ለመሆን በማለትም “ቁርጥ ያለ የጊዜ ገደብ ማስቀመጥ አንፈልግም” ብለዋል።
    • አሜሪካ በቴህራን ላይ እያካሄደች ያለው ጦርነት ዓላማዎችም ዳግመኛ ሲናገሩ ሚሳዔሎቿን እና የባሕር ኃይሏን ማውደም እንዲሁም “ኢራን ዳግም የኒውክሌር ጦር መሣሪያ አለማግኘቷን ማረጋገጥ” መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
    • አሜሪካ እስከ ዛሬ ድረስ 7000 የኢራን ዒላማዎችን አጥቅታለች ያሉ ሲሆን፣ “ምን እንደምናጠቃ እና ለምን እንደምናጠቃ ግልጽ ነው” ብለዋል።
    • ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ዳን ኬይን ለጋዜጠኞች የአሜሪካ ጦር በኢራን የአየር ክልል ምሥራቃዊ አካባቢ ዘልቆ በመግባት እና ኤኤች 64 አፓቼ ሂሊኮፕተሮችን በመጠቀም አጥፍቶ ጠፊ ድሮኖችን “የማደን እና የማውደም” ሥራ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
    • ኬይን አክለውም ኢራን “ወደዚህ ጦርነት የገባችው በርካታ ጦር መሣሪያዎችን ታጥቃ ነው” ካሉ በኋላ፤ አሜሪካ የምትፈጽማቸው ጥቃቶች በተቻለ መጠን “ተከታታይ እና ጫን ያለ” የሆኑት ለዚያ ነው ብለዋል። በተጨማሪም ኢራን አሁንም “የተወሰነ” ወታደራዊ አቅም አንዳላት ገልጸዋል።
    • በስተመጨረሻም ሄግሴት ፔንታጎን በኢራን ለሚካሄደው ጦርነት የ200 ቢለዮን ተጨማሪ በጀት ኮንግረሱ እንዲያጸድቅለት ስለመጠየቁ ሲናገሩ “ሊጨምር ይቸላል” ካሉ በኋላ “መጥፎ ሰዎችን ለመግደል ገንዘብ ይጠይቃል" ብለዋል።
  8. ኢራን እና እስራኤል የኢነርጂ ጣቢያዎችን ማጥቃታቸውን ተከትሎ የጋዝ ዋጋ ጭማሪ አሳይቷል፤ እስካሁን ምን እናውቃለን?

    • የጋዝ ዋጋ ጭማሪ፡- ሐሙስ ዕለት በነበረው የኢነርጂ ግብይት የጋዝ ዋጋ ከ25 በመቶ በላይ ከፍ ብሏል። አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ ወዲህ በአውሮፓ የነዳጅ ዋጋ በፊት ከነበረው በእጥፍ ጭማሪ አሳይቷል።
    • በኢነርጂ ጣቢያዎች ላይ የተፈፀሙ ጥቃቶች፡- ኢራን በኳታር የሚገኘውን የራስ ላፋን የጋዝ ማመንጫ ጣቢያ መትታ "ሰፊ ጉዳት" አድርሳለች። ቴህራን ጥቃት የፈፀመችው እስራኤል በኢራን እና በኳታር መካከል በሚገኘው የደቡብ ፓርስ የነዳጅ ማደያ ጣቢያ ላይ ለፈጸመችው ድብደባ ምላሽ ለመስጠት ነው። የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሃብሻን የነዳጅ ማመንጫ ጣቢያ እና የጋዝ ማምረቻዎች ኢራን የበቀል እርምጃ ከወሰደች በኋላ ለመዝጋት ተገድዳለች። ሳውዲ አረቢያ ደግሞ በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል እና በዋና ከተማዋ ሪያድ የተፈጸሙ ጥቃቶችን ማክሸፏ ተዘግቧል።
    • አሜሪካ "ምንም እንደማታውቅ" ናገራለች፡- ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል በደቡብ ፓርስ ላይ ስለፈጸመችው ጥቃት እንደማታውቅ ተናግረዋል። በተጨማሪም ኢራን በኳታር ላይ ተጨማሪ ጥቃቶችን እንዳትፈጽም አስጠንቅቀዋል።
    • የኢራን እና እስራኤል የሚሳዔል ተኩሶች፡- በመካከለኛው ምሥራቅ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ቀጥለዋል፤ የእስራኤል ጦር ቀደም ሲል ከኢራን የተወነጨፉ ሚሳዔሎች መኖራቸውን አስታውቋል። የአገሪቱ የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ስለደረሰ ጉዳት ምንም ያለው ነገር የለም። ይህ የሆነው የእስራኤል ጦር ረቡዕ ዕለት በሰሜን ኢራን ለመጀመሪያ ጊዜ በዒላማዎች ላይ የአየር ድብደባ መጀመሩን ከተናገረ በኋላ ነው።
    • የሆርሙዝ ወሽመጥ፦ የኢራን ፓርላማ አባላት በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦች የአገልግሎት ክፍያ እና ታክስ እንዲከፍሉ የሚያስገድድ ሕግ ላይ መወያየታቸው ተዘግቧል። 20 በመቶ የሚሆነው የዓለም ነዳጅ የሚተላለፈው በወሽመጡ በኩል ቢሆንም ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ኢራን ለማለፍ የሚሞክሩ መርከቦችን “በእሳት እለኩሳቸዋለሁ” ማለቷን ተከትሎ እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ ቆመዋል።
  9. ኢራን የነዳጅ ተቋማቷ ዳግም ከተጠቁ የባሕረ ሰላጤውን ኢነርጂ መሠረተ ልማት እንደምታወድም ዛተች

    ኢራን ዳግም የኢነርጂ ተቋማቷ ጥቃት የሚደርስባቸው ከሆነ የአሜሪካ እና የእስራኤል አጋር የሆኑ የባሕረ ሰላጤው አገራት የኢነርጂ መሠረተ ልማቶቸን “ሙሉ በሙሉ እስኪወድሙ ድረስ” እንደምትደበድብ አስጠነቀቀች።

    ቴህራን እስራኤል በደቡብ ፓርስ የሚገኝ የጋዝ ማምረቻ ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ በባሕረ ሰላጤው በሚገኙ የጋዝ እና ነዳጅ ዘይት ማምረቻ እና ማከማቻዎች ላይ ተከታታይ ጥቃት ፈጽማለች ብላለች።

    የኢራን ጦር ማዕከላዊ ዕዝ ቃል አቀባይ “የጠላቶቻችን ኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ የኢነርጂ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት በመፈጸማቸው ትልቅ ስህተት መሥራታቸውን አስጠንቅቀናቸዋል” ማለታቸውን ከጦሩ ጋር ግንኙነት ያለው የፋርስ ዜና ወኪል ዘግቧል።

    “ይሀ የሚደገም ከሆነ በእናንተ እና በአጋሮቻችሁ የኢነርጂ መሠረተ ልማት ላይ የምንፈጽመው ተከታታይ ጥቃት ሙሉ በሙሉ እስኪወድም ድረስ አይቋረጥም” ሲሉ ዝተዋል።

    አክለውም የኢራን ምላሽ ከዚህ ቀደም ከነበረው ጥቃት “በጣም ከባድ ሊሆን እንደሚችል” አስጠንቅቀዋል።

  10. ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚተላለፉ መርከቦችን ለማስከፈል እያሰበች ነው

    ኢራን በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ በኩል የሚተላለፉ መርከቦች የአገልግሎት ክፍያ እና ታክስ ለኢራን እንዲከፍሉ የሚያስገድድ ሕግ በአገሪቱ ፓርላማ አባላት መነጋገሪያ መሆኑ ተገለጸ።

    በኢራን ፓርላማ (መጅሊስ) ውስጥ የዋና ከተማዋ ቴህራን ተወካይ የሆኑት ሶማያህ ራፌ የሆርሙዝ ወሽመጥ ደኅንነቱ ተጠብቆ የመርከቦች፣ የነዳጅ እና የምግብ ምርቶች መተላለፊያ እንዲሆን ከተፈለገ ኢራን አስፈላጊውን ጥቅም እንድታገኝ የሚያደርግ ሕግ ላይ እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።

    ኢስና የተባለው የኢራን ዜና አገልግሎት የፓርላማ አባሉ ቴህራን ውስጥ በሚገኝ አደባባይ ላይ ለሕዝብ ባደረጉት ንግግር ኢራን በሆርሙዝ ላይ የሚኖራትን የባለቤትነት ሥልጣንን አስረድተዋል።

    ኢራን “የሆርሙዝ ወሽመጥን ደኅንነት ማረጋገጥ እና የአገሪቱን ጥቅም መጠበቅ” ቀዳሚ አጀንዳዋ መሆኑን ጠቅሰው “አሁን ጠላቶቻችንን ያለችግር በምቾት ሲጠቀሙበት የነበረውን ነጥቀናቸዋል፤ ነገር ግን ይህንን እውነታ ለመቀበል አልቻሉም፤ ሊወጡት የሚችሉት አይደለም” በማለት በወሽመጡ መዘጋት የተፈጠረውን ሁኔታ አመልክተዋል።

    ጨምረውም “በፈጣሪ ፈቃድ በኢራን ወሳኝ እና እርግጠኛ ድል ጦርነቱ ይጠናቀቃል፤ ከዚያ በኋላም በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ማለፍ ለጠላቶቻችን ፈተና ይሆናል” ብለዋል።

  11. አሜሪካ ወታደሮቿን በኢራን ደሴት እና በሆርሙዝ ወሽመጥ የማሰማራት ሃሳብ እንዳላት ተነገረ

    በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄደው ጦርነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ሊሸጋገር ይችላል የሚል ስጋት የገባው የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን በማሰማራት ዘመቻውን ለማጠናከር እያሰበ መሆኑን ሮይተርስ ዘገበ።

    የዜና ወኪሉ አንድ ባለሥልጣን እና ሦስት ምንጮችን ጠቅሶ ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው፤ አሜሪካ በኢራን ላይ እያካሄደች ያለው ጦርነት ሦስተኛ ሳምንት እየተገባደደ ባለበት በአሁኑ ጊዜ አዲስ የሚሰማሩት ወታደሮች አሜሪካ ለምትወስደው እርምጃ ተጨማሪ አማራጮችን ሊሰጣት ይችላል።

    የአየር እና የባሕር ኃይልን በመጠቀም በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ደኅንነት መጠበቅም ተጨማሪ ወታደሮችን ከማሰማራት ጋር የሚወሰድ እርምጃ ሊሆን ይችላል ተብሏል።

    ሮይተርስ ያነጋገራቸው ምንጮች እንዳሉት የሆርሙዝ ሰርጥ መተላለፊያን የመጠበቁ ጉዳይ በኢራን የባሕር ዳርቻዎች ላይ ጭምር የአሜሪካ ኃይሎችን ማሰማራትን ሊጨምር ይችላል።

    በተጨማሪም ኢራን ወደ ውጭ ከምትልከው የነዳጅ ምርት 90 በመቶው በሚያልፍበት የኻርግ ደሴት ላይ እግረኛ ሠራዊትን ለማስፈር እያሰቡ መሆናቸውን ምንጮቹ ተናግረዋል።

    አንድ ባለሥልጣን ግን ቦታዎቹ በኢራን የሚሳዔል እና የድሮን ዒላማ ስር በቀላሉ ስለሚወድቁ ይህ የአሜሪካ ወታደሮችን በኢራን ይዞታዎች ላይ የማሰማራት ዕቅድ አደጋ ሊያስከትል ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

    ኢራን ጥቃት መፈጸሟን የምትቀጥል ከሆነ ለኢራን ከፍተኛ የነዳጅ ገቢ የሚያስገኘውን የኻርግ ደሴትን እንደሚያወድሙ ፕሬዝዳንት ትራምፕ አስጠንቅቀዋል።

    ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ አሜሪካ በወታደራዊ ዒላማዎች ላይ ጥቃት የፈጸመችበት ኻርግ ደሴት ወሳኝ የነዳጅ መሠረተ ልማቶችን ያያዘ በመሆኑ ከማውደም ይልቅ በቁጥጥር ስር ማዋል የተሻለው አማራጭ እንደሆነ ወታደራዊ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

    ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት በመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት ውስጥ እንደማይሳተፉ የገቡትን ቃል በማጠፋቸው በኢራን ላይ ለከፈቱት ጥቃት ከአሜሪካውያን ያገኙት ድጋፍ ዝቅተኛ ነው። በመሆኑም ወታደሮችን ወደ ኢራን የሚያሰማሩ ከሆነ ፕሬዝዳንቱ በአገር ውስጥ ከፍተኛ ፖለቲካዊ አደጋ ይገጥማቸዋል።

  12. ዌስት ባንክ ውስጥ በሚሳዔል ጥቃት ሦስት ሴቶች ተገደሉ

    የእስራኤል ጦር ኢራን ሚሳዔሎችን ማስወንጨፏን ከገለጸ በኋላ በወረራ በተያዘው ዌስት ባንክ ውስጥ በሚገኝ የውበት ሳሎን ላይ በወደቀ ፍንጣሪ ሦስት ሴቶች መገደላውን የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ አስታወቀ።

    ቤት አዋ በተባው የዌስት ባንክ አካባቢ በደረሰው ጥቃት ስምንት ሰዎች ላይ ከባድ እና ቀላል ጉዳት እንደደረሰ ተገልጿል። የአካል ክፍሉ መቆረጥ ያለበት አንድ ሰው ደግሞ ወደ ሆስፒታል መወሰዱን የቀይ ጨረቃ መግለጫ ያስረዳል።

    የውበት ሳሎኑ የተመታው የእስራኤል ጦር ኢራን ሚሳዔሎችን ማስወንጨፏን ካስታወቀ ከአጭር ጊዜ በኋላ ነው።

    የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ማኅበር እንደገለጸው እስራኤል አካባቢው ላይ ባስቀመጠቻቸው መዝጊያዎች የተነሳ “ሠራተኞቹ አደጋ ወደ ደረሰበት ስፍራ በፍጥነት” መድረስ አልቻሉም። ይህም ሁኔታ “የተጎዱ ሰዎችን ነፍስ ለማዳን የሚደረገው ጥረት ላይ ቀጥታ እና ከፍተኛ ተጽዕኖ” ማሳደሩንም ገልጿል።

    “ወራሪው ኃይል ኃላፊነቱን እንዲወጣ እንዲሁም የነፍስ አድን ሥራዎችን እንዲያመቻች እና እንዳያሰናክልም” አሳስቧል።

  13. የኢራንን ጦርነት ተቃውመው ከሥልጣናቸው የለቀቁት የአሜሪካ ባለሥልጣን በኤፍቢአይ እየተመረመሩ መሆኑ ተገለጸ

    የኢራንን ጦርነት ተቃውመው ከሥልጣናቸው የለቀቁት የአሜሪካ ብሔራዊ የፀረ ሽብር ማዕከል የቀድሞ ዳይሬክተር ጆ ኬንት፤ በኤፍቢአይ ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሆነ ተገለጸ።

    ምርመራው ምሥጢራዊ መረጃዎችን ለተለያዩ ምንጮች አሹልከዋል በሚል የተከፈተ እንደሆነ በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ለጉዳዩ ቅርበው ያላቸውን ምንጮችን ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ ያሳያል።

    በኤፍቢአይ የወንጀል ክፍል የተያዘው ይህ ምርመራ ባለሥልጣኑ ከኃላፊነት ከመልቀቃቸው አስቀድሞ የተጀመረ እና ለተወሰነ ጊዜ ሲካሄድ የቆየ መሆኑን ምንጮች ተናግረዋል ተብሏል።

    የቀድሞው የፀረ ሽብር ኃላፊ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከኃላፊነታቸው የለቀቁት ኢራን “ምንም ድርስ አደጋ” አልደቀነችም እንዲሁም “ጦርነቱ የተጀመረው በእስራኤል እና ጉልበት ባላቸው የአሜሪካ የውትትወታ ተቋማት ግፊት ነው” በሚል ነበር።

    ረቡዕ ዕለት ከወግ አጥባቂው የፖለቲካ አስተያት ሰጪ ታከር ካርልሰን ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ ደግሞ፤ የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ መገደላቸውን ተቃውመዋል። ኻሜኒን መግደል አሜሪካ ልትወስድ ከምትችላቸው እርምጃዎች መካከል “የመጨረሻ” መሆን እንደነበረበት ተናግረዋል።

    “የኒውክሌር ፕሮግራማቸውን እያለዘበ ነበር፤ የኒውክሌር መሳሪያ እንዳያገኙ እየተከላከላቸው ነበር” ብለዋል።

  14. የአሜሪካ ከፍተኛ የስለላ ኃላፊ የኢራን መንግሥት “ባለበት” ቢሆንም “በከፍተኛ ሁኔታ ተዳክሟል” አሉ

    የአሜሪካ ብሔራዊ ስለላ መሥሪያ ቤት ዳይሬክተር ቱልሲ ጋባርድ፤ የኢራን መንግሥት መዋቅር “እንዳለ ቢሆንም በአመራሩ እና በወታደራዊ አቅሙ ላይ በተፈጸመበት ጥቃም ምክንያት በከፍተኛ መጠን ተዳክሟል” ሲሉ ተናገሩ።

    ዳይሬክተሯ እና ሌሎች የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከፍተኛ ባለሥልጣናት በኮንግረስ ቀርበው ከሁለት ሰዓት በላይ የቆየ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

    የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገው ይህ ይፋዊ የማብራሪያ መርሃ ግብር የተካሄደው የፀረ ሽብር ከፍተኛ ባለሥልጣን ኢራን አሜሪካ ላይ ድረስ ስጋት አልደቀነችም በሚል ጦርነቱን ተቃውመው ከኃላፊነታቸው በለቀቁ ማግሥት ነው።

    የአገሪቱን ስለላ ኦፕሬሽኖች የሚያስተባብሩት ዳይሬክተሯ ጋባርድ፤ ኢራን አሜሪካ ላይ ድርስ ስጋት ደቅናለች ብለው ያምኑ እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ ግልጽ ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል። “ጉዳዩ ድርስ ስጋት የሚደቅን እንደሆነ እና እንዳልሆነ የሚወስኑት ብቸኛው ሰው ፕሬዝዳንቱ ናቸው” ብለዋል።

    ዳይሬክተሯ ጦርነቱ ቴህራን ላይ ስላደረሰው ጉዳት ሲናገሩም “የስለላ ማኅበረሰቡ ባለበት ያለ የሚመስለውን የኢራን አገዛዝን ሁኔታ ገምግሟል፤ አመራሩ እና ወታደራዊ አቅሞቹ ላይ በተፈጸሙት ጥቃቶች ምክንያት በከፍተኛ መጠን ተዳክሟል” ሲሉ ተናግረዋል።

    ኢራን ባለፈው ዓመት ከእስራኤል ጋር በተካሄደው የ12 ቀናት ጦርነት ወቅት “ከፍተኛ ጉዳት” የደረሰበትን የኒውክሌር መሠረተ ልማት “መልሳ ለመገንባት እየሞከረች” ነበር ሲሉ ተደምጠዋል። “ለኒውክሌር ግዴታዎቿን ለመገዛትም ፈቃደኛ አለመሆኗን ቀጥላለች” በማለት ለኮንግረስ ምላሽ ሰጥተዋል።

    የአሜሪካ ሴንትራል ኢንተለጀንስ ኤጀንሲ (ሲአይኤ) ዳይሬክተር ጆን ራትክሊድ በበኩላቸው “ለረጅም ጊዜያት ኢራን ለአሜሪካ የማያቋርት ስጋት ሆና ቀጥላለች፤ በዚህ ጊዜም አስቸኳይ ስጋት ደቅናለች ብዬ አምናለሁ” ብለዋል።

  15. የአሜሪካ መከላከያ በኢራን ለሚካሄደው ጦርነት ከ200 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተጨማሪ በጀት ጠየቀ

    የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር በኢራን ለሚካሄደው ጦርነት የ200 ቢለዮን ተጨማሪ በጀት እንዲጸድቅለት ለፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ጥያቄ ማቅረቡን አንድ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን ለዋሽንግተን ፖስት ተናገሩ።

    የተጠየቀው ገንዘብ የትራምፕ አስተዳደር እስካሁን ካወጣው የመከላከያ ገንዘብ የበለጠ ሲሆን፣ በጣም ወሳኝ የሆኑ እና “በአስቸኳይ” የሚፈለጉ የጦር መሳሪያዎች ምርትን ለመጨመር እንደሚውል ተገልጿል።

    ይህ ከፍተኛ የመከላከያ በጀት ጭማሪ ጥያቄ በቀጥታ በፕሬዝዳንቱ የሚጸድቅ አይደለም፤ በአገሪቱ ምክር ቤት በኩል አልፎ ይሁንታን ማግኘት ይኖርበታል።

    ባለፈው ታኅሣሥ ላይ የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች ከፍተኛ ነው የተባለውን 901 ቢሊየን ዶላር የመከላከያ በጀት ያጸደቁ ሲሆን፣ በወቅቱ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ያቀረቡት የበጀት ጥያቄ ከዚህም ከፍ ያለ ነበር።

    ፕሬዝዳንቱ አሁን ያለንበትን ጊዜ “የተረበሸ እና አደገኛ ወቅት” በማለት በቀጣዩ የአውሮፓውያን ዓመት የአሜሪካ የመከላከያ በጀት 1.5 ትሪሊየን ዶላር እንዲደርስ ጥረት እያደረጉ ነው።

    ከፍተኛው በጀት የሚፈቀድ ከሆነ አሜሪካ “ታይቶ የማይታወቅ ሠራዊት” በመገንባት አገሪቱን “ደኅንነቷ የተጠበቀ” ያደርጋታል ሲሉ ባለፈው ጥር ወር ላይ ተናግረው ነበር።

    ሦስት ሳምንት የሆነው የኢራን ጦርነት አሜሪካን ምን ያህል እንዳስወጣት በይፋ የተባለ ነገር የለም። ነገር ግን የተለያዩ የዜና ተቋማት አሜሪካ ኢራን ላይ በፈጸመችው የመጀመሪያ ሳምንት ጥቃት ከ11 ቢሊየን ዶላር በላይ ማውጣቷን ዘግበዋል።

  16. ፕሬዝዳንት ትራምፕ የኢራንን የጋዝ ማምረቻ ስፍራ “በከፍተኛ መጠን እንደሚያጋዩ” አስጠነቀቁ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ኢራን በኳታር ራስ ላፋን የተፈጥሮ ጋዝ ማውጫ ላይ በድጋሚ ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ፤ የቴህራንን የጋዝ ማምረቻ ስፍራ “ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ” መጠን “እንደሚያጋዩ” አስጠነቀቁ።

    ትራምፕ ይህንን ያሉት ደቡብ ፓርስ ውስጥ የሚገኘው የተፈጥሮ ጋዝ ስፍራ በእስራኤል ጥቃት የተመታባት ኢራን፤ ኳታር ውስጥ በሚገኝ ተመሳሳይ የኢነርጂ መሠረተ ልማት ላይ የሚሳዔል እና የሮኬት ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ነው።

    በኳታር የአጸፋ ጥቃት የተፈጸመበት ራስ ላፋን የተሰኘው የኢንዱስትሪ ስፍራ በዓለም ትልቁ የሆነውን የተጣራ የተፈጥሮ ነዳጅ ማቀነባበሪያ ይዟል።

    ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ረዘም ያለ ጽሁፍ፤ እስራኤል በኢራን የተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻ ላይ ስለፈጸመችው ጥቃት አሜሪካ “ምንም እንደማታውቅ” ገልጸዋል። እስራኤል“በመካከለኛው ምሥራቅ እየተፈጠረ ባለው ነገር ተናድዳ”፤ በኃይል” እርምጃ መውሰዷን አንስተዋል።

    “አሜሪካ ስለዚህኛው ጥቃት የምታውቀው ነገር አልነበረም፤ ኳታርም በየትኛውም መንገድ እና ቅርጽ ተሳትፎ አልነበራትም፤ ሊፈጸም እንደነበረም ምንም ሀሳብ አልነበራትም” ሲሉ ተከላክለዋል።

    ኳታር እና አሜሪካ ተሳትፎ እንደሌላቸው ኢራን አላወቀችም ያሉት ትራምፕ፤ ራስ ላፋን ላይ “አግባብ ያልሆነ እና ኢፍትሐዊ” ጥቃት ፈጽማለች በማለት ጽፈዋል።

    ኢራን “ሌላ ንፁህ አገርን ለማጥቃት ብልህ ያልሆነ ውሳኔ እስካላሳለፈች ድረስ” ከአሁን በኋላ እስራኤል ኢራን ውስጥ የሚገኘውን የደቡብ ፓርስ የጋዝ ማምረቻ ስፍራ እንደማታጠቃ ገልጸዋል።

    ፕሬዝዳንቱ፤ ኢራን በድጋሚ ኳታር ላይ ጥቃት ከፈጸመች ግን አሜሪካ "የደቡብ ፓርስ የጋዝ ስፍራን በሙሉ ኢራን አይታው በማታውቀው የጥንካሬ እና የኃይል መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ታጋየዋለች" ሲሉ ዝተዋል።

    ትራምፕ አክለውም፤ ኢራን ላይ “ረጅም ጊዜ የሚቆይ ተጽዕኖ” የሚኖረውን “በዚህ ደረጃ ያለ ጥቃት እና ውድመት” እንዲፈጸም ማዘዝ እንደማይፈልጉ ጠቅሰዋል። “የኳታር የተጣራ ተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻን በድጋሚ ካጠቃች ግን [ጥቃቱ እንዲፈጸም ለማዘዝ] አላንገራግርም” ብለዋል።

  17. የተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻ የተመታባት ኢራን በኳታር የነዳጅ ማውጫ ላይ የሚሳዔል እና የሮኬት ጥቃት ፈጸመች

    በግዛቷ ውስጥ የሚገኘው የዓለም ትልቁ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻ ስፍራ በእስራኤል የተመታባት ኢራን፤ የኳታር የነዳጅ ኩባንያ ላይ የሜሳዔል እና የሮኬት ጥቃቶችን ፈጸመች።

    ይህንን ጥቃት ተከትሎ ኳታር ኢራንን “ለቀጣናው ብሔራዊ ደኅንነት እና መረጋጋት ቀጥተኛ ስጋት” ስትል የገለጸች ሲሆን ሁለት የቴህራን ዲፕሎማቶችንም አባርራለች።

    ትናንት እስራኤል ደቡብ ፓርስ የሚገኘው የፔትሮኬሚካል ተቋም የአየር ድብደባ ከፈጸመች በኋላ ኢራን፤ ኳታር፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ውስጥ የሚገኙ የነዳጅ ማውጫ ስፍራዎች ላይ የአጸፋ ጥቃት እንደምትፈጽም አስጠንቅቃ ነበር።

    የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ደቡብ ፓርስ የጋዝ ስፍራ ላይ ከደረሰው ጥቃት በኋላ ባደረጉት ንግግር የዚህ ጥቃት “መዘዝ ከቁጥጥር ውጪ” እንደሚወጣ አሳስበዋል።

    ምሽት ላይ በኳታር ‘ራስ ላፋን ኢንዱስትሪያል’ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ዋነኛ የነዳጅ ማቀነባበሪያ ስፍራ በሚሳዔሎች እንደተመታ በአገሪቱ መንግሥት ባለቤትነት የተያዘው ‘ኳታር ኢነርጂ’ ኩባንያ አስታውቋል። በጥቃቱ የተነሳ ስፍራው በእሳት እንደተያያዘ እና ተቋሙ ላይ “ከፍተኛ ጉዳት” እንደደረሰም ገልጿል።

    ኩባንያው ዛሬ ንጋት ባወጣው መረጃ ደግሞ ኢራን በፈጸመችው ሌላ የሚሳዔል ጥቃት የኢነርጂ ተቋሙ ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል።

    ኳታር የኢራንን ጥቃት “ለቀጣናው ብሔራዊ ደኅንነት እና መረጋጋት ቀጥተኛ ስጋት” ስትል ገልጻዋለች። “የኢራን ወገን ቀጠናውን ወደ ገደል የሚወስደው እና የዚህ ቀውስ አካል ያልሆኑ አገራትን ወደ ግጭት አዙሪት የሚስበውን የማባባስ ፖሊሲ ቀጥሎበታል” ብላለች።

    “ምላሽ የመስጠት መብት እንዳላት” የገለጸችው ኳታር፤ “ሉዐላዊነቷን፣ ደኅንነቷን እና የዜጎቿን ደኅንነት ለማስጠበቅ አስፈላጊውን እርምጃ በሙሉ ከመውሰድ ወደ ኋላ እንደማትል” አስጠንቅቃለች።

    ከሰዓታት በኋላም ኳታር ሁለት የኢራን ዲፕሎማቶች በ24 ሰዓት ውሰጥ አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ አዝዛለች። ለቅቀው እንዲሄዱ የታዘዙት የኢራን ወታደራዊ እና የደኅንነት አታሼዎች እንደሆኑ የኳታር ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

  18. የኢራን ሴት እግር ኳስ ተጨዋቾች የአውስትራሊያ ጥገኝነትን ትተው ወደ አገራቸው ጉዞ ጀመሩ

    ለውድድር ወደ አውስትራሊያ ተጉዘው ከነበሩት የኢራን ሴት ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አባላት መካከል እዚያው በጥገኝነት ለመቆየት ፍላጎት የነበራቸው አምስት ተጫዋቾች ሃሳባቸውን ቀይረው ከቀሪው የቡድኑ አባላት ጋር ወደ አገራቸው ለመመለስ ጉዞ ጀመሩ።

    ወደ አገራቸው ለመመለስ ከአውስትራሊያ በማሌዢያ እና በኦማን በኩል ወደ ቱርክ የደረሱት ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾቹ፤ በአውቶብስ በድንበር በኩል ወደ ኢራን ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    በእስያ ዋንጫ የመክፍቻ ጨዋታ ላይ የአገራቸው ብሔራዊ መዝሙር በሚዘመርበት ጊዜ ዝም በማለታቸው የበቀል ቅጣት ሊጠብቃቸው እንደሚችል በመስጋት በርካታ የቡድኑ አባላት መጀመሪያ ላይ በአውስትራሊያ ለመቆየት የሚስችላቸውን የሰብአዊነት ከለላ ቪዛ ለማግኘት ፈልገው ነበር።

    በዚህም ምክንያት ጦርነት ውስጥ የምትገኘው የአገራቸው ባለሥልጣናት ተጫዋቾቹን “ከሃዲዎች” በማለት ወቅሰዋቸው ነበር። በኋላ ላይ ግን የተደረገባቸውን ጫና ተቋቁመው ወደ አገራቸው ለመመለስ በመወሰናቸው “የጠላትን ዕቅድ” በማክሸፍ እያወደሷቸው ነው።

    የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች ግን ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾቹ የጥገኝነት ጥያቄያቸውን ለመቀልበስ የተገደዱት ኢራን ውስጥ ባሉ በቤተሰቦቻቸው ላይ ጉዳት እንደሚደርስ ማስፈራሪያ እና ጫና ስለተደረገባቸው ነው ይላሉ።

    ከብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች መካከል ሁለቱ ብቻ የጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ ወደ አገራቸው ሳይመለሱ ቀርተዋል።

  19. የኢራን ፕሬዝዳንት የስለላ ሚኒስትሩን መገደል አረገገጡ

    ኢራን የስለላ ሚኒስትር ኢስማኢል ኻቲብ መገደላቸውን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን አረጋገጡ።

    እስራኤል ትናንት ምሽት በፈጸመችው ጥቃት ከፍተኛ የደኅንነት ኃላፊ የሆኑትን ኻቲብን መግደሏን ገልጻ ነበር።

    የኢራኑ ፕሬዝዳንት ከሰዓታት በኋላ በኤክስ ገጻቸው በሰፈሩት ጽሁፍ፤ የስለላ ሚኒስትሩን እና ሌሎች ኃላፊዎች “የፈሪ ግድያ” እንደተፈጸመባቸው ገልጸዋል።

    ፕሬዝዳንቱ “ውድ ባልደረቦቼ ኢስማኢል ኻቲባ፣ አሊ ላሪጃኒ እና አዚዝ ናስርዛዴህ እንዲሁም የተወሰኑ የቤተሰቦች አባላት እና አብረዋቸው የነበሩ ቡድኖች ላይ የተፈጸመው የፈሪ ግድያ ሐዘን ላይ ጥሎናል” ብለዋል።

    ፕሬዝዳንቱ የጠቀሷቸው የኢራን ብሔራዊ የደኅንነት ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ አሊ ላሪጃኒ በእስራኤል ጥቃት የተገደሉት ከትናንት በስቲያ ሌሊት ነበር።

    የቀድሞው መከላከያ ሚኒስትር አዚዝ ናስርዛዴህ ደግሞ በመጀመሪያው ቀን ጥቃት የጠቅላይ መሪው አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ጋር ከተገደሉ ወታደራዊ አመራሮች መካከል ናቸው።

  20. በኢራን የሚገኘው የዓለም ግዙፉ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻ ስፍራ ጥቃት ተፈጸመበት

    በኢራን ደቡብ ፓርስ የጋዝ ማምረቻ ስፍራ የሚገኘው የፔትሮኬሚካል ተቋም የአየር ድብደባ እንደተፈጸመበት ከእስላማዊው አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያለው ታስኒም የዜና ወኪል ዘገበ።

    ኳታር፤ እስራኤል በተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻ ስፍራው ላይ የፈጸመችውን ጥቃት “አደገኛ እና ኃላፊነት የጎደለው” ስትል ኮንናለች።

    የታስኒም ዘገባ እንደሚያመለክተው ጥቃቱ የተፈጸመው ዛሬ ረፋድ አካባቢ ነው። ከፊል ይፋዊው ፋርስ የዜና ወኩል በበኩሉ በቴሌግራም ገጹ ባወጣው ማስጠንቀቂያ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻው በእሳት መያያዙን ገልጿል። የእሳት እና የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በስፍራው እንደሚገኙም ጠቅሷል።

    በዓለም ትልቁ በሆነው የተፈጥሮ ጋዝ ማውጫ ስፍራ ደቡብ ፓርስ ውስጥ የኳታር እና ኢራን ማምረቻ ተቋማት ይንቀሳቀሳሉ።

    ኳታር በመግለጫዋ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻው ስፍራ ላይ ጥቃት የተፈጸመው በእስራኤል እንደሆነ የገለጸች ሲሆን፣ ድርጊቱንም “አደገኛ እና ኃላፊነት የጎደለው” ስትል አውግዛለች።

    የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ማጅድ አል አንሳሪ፤ በኢነርጂ መሠረተ ልማት ላይ የሚፈጸም ጥቃት “የዓለም የነዳጅ ደኅንነት ላይ ስጋት እንደሚደቅን” ተናግረዋል።

    “ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ እንደገለጽነው ወሳኝ ተቋማትን ዒላማ ከማድረግ መቆጠብ እንደሚስፈልግ እንገልጻለን" ያሉት ቃል አቀባዩ፤ "ሁሉም ወገኖች" ዓለም አቀፍ ሕግን እንዲያከብሩ እና ውጥረቱን ለማርገብ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።