ትራምፕ ሆርሙዝ እንዲከፈት የጊዜ ገደብ ሲያስቀምጡ ኢራን ደግሞ ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የኢነርጂ ጣቢያዎች ለማጥቃት ዛተች

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥን እንድትከፍት የ48 ሰዓት የጊዜ ገደብ አስቀመጡ። ኢራን በበኩሏ በኃይል ማመንጫዎቿ ላይ ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ በባሕረ ሰላጤው የሚገኙ እና ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የኢነርጂ ጣቢያዎች እንደምታጠቃ አስጠንቅቃለች።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ኢራን 3,800 ኪሎ ሜትር በሚርቀው የአሜሪካ እና ዩኬ የጦር ሰፈር ላይ ሚሳዔል ማስወንጨፏ ተገለጸ

    ኢራን፤ ዲዬጎ ጋርሺያ በተባለው የአሜሪካ እና የዩናይትድ ኪንግደም ጋራ የጦር ሰፈር ላይ ሁለት መካከለኛ ርቀት ተወንጫፊ ባለስቲክ ሚሳዔሎችን መተኮሷን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    ዎል ስትሪት ጆርናል ጋዜጣ በርካታ ምንጮችን ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ፤ የተተኮሱት ሁለቱም ሚሳዔሎች በሕንድ ውቅያኖስ ላይ የሚገኘውን ጦር ሰፈር እንዳልመቱት አስታውቋል።

    ሴኤንኤን በበኩሉ፤ ሚሳዔሎቹ የተተኮሱት በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር አርብ ንጋት ላይ እንደሆነ ከአሜሪካ ባለሥልጣን መስማቱን ዘግቧል።

    ከኢራን እስከ ዲዬጎ ጋርሺያ ያለው ርቀት 3,800 ኪሎ ሜትር ገደማ ነው። የቀድሞው ኢራን ጠቅላይ መሪ የአገሪቱ ሚሳዔል የሚወነጨፍበት ርቀት ከ2,000 እንዳይበልጥ ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር።

    ቢቢሲ ስለ ጥቃቱ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ለአሜሪካ ፔንታገን እና ለዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርቧል። የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስቴር ፔንታጎን “በአሁኑ ሰዓት ማቅረብ የሚችለው ምንም ነገር እንደሌለ” ገልጿል።

  2. የሆርሙዝ ወሽመጥ፡ የትራምፕ ራስ ምታት

    ኢራን ላይ የሚካሄደው የአሜሪካ እና የእስራኤል ዘመቻ ከተጀመረ በኋላ ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋቱ የጦርነቱ ተጽእኖ በመላው ዓለም እንዲሰማ አድርጓል።

    ለፕሬዝዳንት ትራምፕም ዋነኛ ራስ ምታት የሆነው የባሕር መተላለፊያው መስመር ጉዳይ ነው። አጋር አገራት ሆርሙዝን በመጠበቅ እንዲያግዟቸው ቢጠይቁም ሰሚ ሳያገኙ ቀርተዋል።

    ትራምፕ መርከቦች በሆርሙዝ በኩል እንዲያልፉ ለማድረግ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስዱ ያሳወቁ ሲሆን ሊረዷቸው ፈቃደኛ ያልሆኑትን የኔቶ አጋሮቻቸውን ደግሞ ክፉኛ ተችተዋል።

    ኢራንም ለተከፈተባት ጥቃት አጸፋ በጠባቡ የባሕር መተላለፊያ ላይ የሚገኝን ማንኛውንም መርከብ “እንደምታጋይ” ማሳወቋን ተከትሎ፣ ፕሬዝዳንት ትራምፕ “አስፈላጊ ከሆነ አሜሪካ ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን በባሕር ኃይሏ ታጅባለች” ብለው ነበር።

    ቀጥለው ደግሞ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚተላለፈውን ነዳጅ “ለማስቆም ማንኛውንም ነገር የምታደርግ ከሆነ፤ ከተፈጸመባት ድብደባ ከሃያ እጥፍ በላይ በሆነ ኃይል ትመታለች” ብለዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በተጨማሪም አጋሮቻቸው የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት እንዲተባበሩ የጠየቁ ሲሆን፣ “በርካታ አገራት በተለይም በመዘጋቱ የተጎዱት የጦር መርከቦችን ይልካሉ” ብለው ነበር።

    ነገር ግን የቅርብ አጋሮቻቸው የሆኑት የኔቶ አባላት እስራኤል እና አሜሪካ በከፈቱት ጦርነት ውስጥ የመሳተፍ ፍላጎት እንደሌላቸው በመግለጽ እራሳቸውን አርቀዋል።

    በዚህም የተነሳ የኔቶ አጋሮቻቸውን “ፈሪዎች” ሲሉ ዘልፈዋል። “የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ በማለት ያማርራሉ፤ ነገር ግን በቀላል ወታደራዊ ስምሪት የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት መተባበር አይፈለጉም” ሲሉም ተችተዋቸዋል።

  3. ዩናይትድ ኪንግደም፤ አሜሪካ የጦር ሰፈሮቿን ተጠቅማ በሆርሙዝ የሚገኙ ኢራን ይዞታዎችን እንድታጠቃ ፈቀደች

    ዩናይትድ ኪንግደም፤ አሜሪካ በወሳኙ የባሕር መተላለፊያ ሆርሙዝ ወሽመጥ የሚገኙ የኢራን ይዞታዎች ላይ ለምትፈጽማቸው ጥቃቶች የጦር ሰፈሮቿን እንድትጠቀም ፈቀደች። ኢራን፤ ይህ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ውሳኔ “የብሪታኒያ ዜጎችን ሕይወት አደጋ ላይ ይጥላል” በማለት አስጠንቅቃለች።

    የአገሪቱ መንግሥት ከዚህ ቀደም ኢራን የብሪታኒያን ጥቅም እና ዜጎች የሚጎዳ የሚሳዔል ጥቃት እንዳትፈጽም ለመከላከል በሚከናወኑ ዘመቻዎች ወቅት የአሜሪካ ኃይሎች የብሪታኒያ የጦር ሠፈሮችን እንዲጠቀሙ ፈቅዶ ነበር።

    የዩናይትድ ኪንግደም ሚኒስትሮች አርብ ምሽት ባደረጉት ስብሰባ፤ አሜሪካ የጦር ሠፈሮቹን የምትጠቀምበትን ዓላማ አስፍተዋል።

    በዚህም በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን መጠበቅን ጨምሮ ለዘመቻዎቿ እንድትትጠቀም ፈቅደዋል።

    ይህ ውሳኔ ቢተላለፍም አሁንም ዩናይትድ ኪንግደም ጦርነቱ ውስጥ በቀጥታ እንደማትሳተፍ የአገሪቱ መንግሥት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። “ዩናይትድ ኪንግደም ጦርነቱን በተመለከተ ከያዘችው አቋም ጀርባ ያሉት መርሆዎች ተመሳሳይ ሆነው ይቀጥላሉ” ብሏል።

    የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ እንደተናገሩት የጦር ሰፈሮቹ “በሆርሙዝ ወሽመጥ በመርከቦች ላይ ጥቃት ለመፈጸም የሚውሉ አቅሞችን” ዒላማ በማድረግ ለሚከናወኑ “የአሜሪካ የመከላከያ ዘመቻዎች” ጥቅም ላይ እንዲውሉ ሚኒስትሮቹ ተስማምተዋል።

    ስለዚህ ውሳኔ አስተያየት የሰጡት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር አሜሪካ የብሪታኒያ ጦር ሰፈሮችን እንድትጠቀም በመፍቀዷ “የብሪታኒያ ዜጎችን ሕይወት አደጋ ላይ ጥለዋል” ብለዋል።

    ኢራን “ራሷን የመከላከል መብቷን ትጠቀማለች” ሲሉም አሳስበዋል። አራግቺ በኤክስ ገጻቸው ባጋሩት ልጥፍ “በርካታው የብሪታኒያ ሕዝብ እስራኤል እና አሜሪካ ኢራን ላይ በወሰዱት የጦርነት ምርጫ በምንም መልኩ መሳተፍ አይፈልግም” ብለዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ “ስታርመር የራሱነ ሕዝብ ችላ ብሎ የዩናይትድ ኪንግደም የጦር ሠፈሮች በኢራን ላይ ለሚፈጸም ጥቃት ጥቅም እንዲውሉ በመፍቀድ የብሪታኒያውያንን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሏል” በማለት ጽፈዋል።

  4. አሜሪካ በኢራን ነዳጅ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ በጊዜያዊነት አነሳች

    በከፍተኛ መጠን የጨመረው የነዳጅ ዋጋ እንዲቀንስ እየጣረ ያለው የአሜሪካ መንግሥት ግምጃ ቤት፤ ቀድሞውኑም ባሕር ላይ ያለ የኢራን ነዳጅ ለ30 ቀናት በማዕቀብ ነጻ እንዲሆን ወሰነ።

    የግምጃ ቤት ሚኒስትሩ ስኮት ቤሴንት “ይህ የአጭር ጊዜ ፈቃድ” 140 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ወደ ዓለም የኢነርጂ ገበያ እንዲገባ እንደሚያደርግ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ገልጸዋል።

    ይሁን እንጂ ኢራን ከነዳጅ ሽያጩ የሚገኘውን ትርፍ “ለማግኘት አዳጋች” እንደሚሆንባት ቤሴንት ተናግረዋል።

    የማዕቀብ ማንሳት ውሳኔው “ቀድሞውኑ እየተጓጓዘ ያለ ነዳጅ ላይ ብቻ ተገደበ” መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ “አዲስ ግዢን ወይም ምርት አይፈቅድም” ብለዋል።

    “በመሠረቱ የነዳጅ ዋጋን ለመቀነስ የኢራንን በርሜሎች በራሷ በቴህራን ላይ እንጠቀማለን” በማለት ጸፈዋል።

    የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ እንዲሁም ቴህራን በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የኢነርጂ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ከፈጸመች በኋላ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኘ መጠን ጨምሯል።

    የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ አርብ ዕለት የ3 በመቶ ጭማሪ በማሳየት በበርሜል 113 ዶላር ገብቷል። ይህ ዋጋ ካባለፈው ዓመት ጋር ሲጻጸር የ53 በመቶ ጭማሪ አለው።

  5. የትራምፕ አስተዳደር ኢራን ውስጥ ሊደረግ ለሚችል የምድር ጦር ስምሪት ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ተዘገበ

    የአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት (ፔንታጎን) ባለሥስልጣናት የአገሪቱ እግረኛ ጦር ኢራን ውስጥ የሚሰማራበትን መንገድ በተመለከተ ዝርዝር ዕቅድ ማዘጋጀታቸውን በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውዝ ዘገበ።

    በሌላ በኩል በሺህዎች የሚቆጠሩ የአሜሪካ ወታደሮች እና ሦስት ተጨማሪ የጦር መርከቦች ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እየተሰማሩ መሆኑን የዜና ወኪሎቹ አሶሺዬትድ ፕሬስ እና ሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል።

    ሲቢኤስ ኒውስ በጉዳዩ ላይ ገለጻ የተደረገላቸውን ምንጮች ጠቅሶ ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው፤ ከፍተኛ የአሜሪካ የጦር አዛዦች ኢራን ውስጥ እግረኛ ወታደሮችን የማሰማራትን አማራጭ በተመለከተ ዝግጅት ለማድረግ ጥያቄ አቅርበዋል።

    ምንጮች እንደገለጹት፤ ትራምፕ በቀጣናው የምድር ጦር ማሰማራትን በተመለከተ እያሰቡበት ነው። ፕሬዝዳንቱ በምን ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ እግረኛ ወታደሮችን ሊጠቀሙ ይችላሉ የሚለው ግልጽ እንዳልሆነ ዘገባው ያመለክታል።

    ትራምፕ ሐሙስ ዕለት በዋይት ሐውስ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ግን “ወታደሮችን ወደ የትም አላሰማራም” ብለው ነበር።

    ፕሬዝዳንቱ እግረኛ ጦር ሊያሰማሩ እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ “ቢሆን በእርግጠኝነት እነግራችሁ ነበር” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ይሄንን ቢሉም ተጨማሪ የአሜሪካ ወታደሮች ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እየተጓዙ እንደሆነ አሶሺዬትድ ፕሬስ እና ሮይተርስ ዘግበዋል።

    የኤፒ ዘገባ እንደሚያመለክተው ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሚላኩት ሦስት ተጨማሪ የባሕር ላይ ጥቃት ፈጻሚ የጦር መርከቦች እና 2,500 ወታደሮች ናቸው።

    የሚሰማሩት ወታደሮች ወደፊት ሊከናወን በሚችል ዘመቻ ላይ እገዛ ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የሮይተርስ ዘገባ ያሳያል። የዜና ወኪሉ በዘገባው፤ ትራምፕ ኢራን ውስጥ ወታደሮችን የማሰማራት ሀሳብን በተመለከተ ውሳኔ ላይ አልደረሱም ብሏል።

  6. ፕሬዝዳንት ትራምፕ የኢራን ጦርነትን “ለማጠቃለል እያሰብን ነው” አሉ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ላይ በተከፈተው ጦርነት ያቀድናቸውን “ግቦች ለማሳካት እጅግ በመቃረባችን” ጦርነቱን “ለማጠቃለል እያሰብን ነው” ሲሉ ተናገሩ።

    ኢራን የዘጋችውን የሆርሙዝ ወሽመጥ የማስከፍት ጉዳይ ግን የመርከብ መተላለፊያ መስመሩን “የሚጠቀሙት አገራት” ኃላፊነት መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

    ትራምፕ ‘ትሩዝ ሶሻል’ በተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ “ግቦቻችንን ለማሳካት በጣም እየተቃረብን በመሆኑ፤ ሽብርተኛውን የኢራን አገዛዝ በተመለከተ፤ በመካከለኛው ምሥራቅ የምናደርገውን ታላቅ ወታደራዊ ጥረት ለማቆም እያሰብን ነው” ብለዋል።

    እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ ኢራን ላይ የተከፈተው ጥቃት አምስት ዓላማዎች ነበሩ። በቀዳሚነት የጠቀሱት “የኢራንን ሚሳዔል አቅም፣ ማስወንጨፊያዎች እና ተያያዥነት ያላቸው ነገሮችን በጠቅላላ ሙሉ በሙሉ ማዳከም” የሚለውን ነው።

    “የኢራንን የመከላከያ ኢንዱስትሪ ሰፈርን ማውደም” እንዲሁም የአገሪቱን “የባሕር እና የአየር ኃይል፣ የፀረ-አውሮፕላን የጦር መሣሪያዎችን ጭምር ማጥፋት” የሚለውን ከግቦቹ መካከል ጠቅሰዋል።

    ትራምፕ በአራተኛነት የጠቀሱት ግብ “ኢራን ፈጽሞ ወደ ኒውክሌር አቅም እንዳትቀርብ ማድረግ” እና አድርጋ ከተገኘችም አሜሪካ “በፍጥነት እና በኃይል ምላሽ መስጠት የምትችልበት ደረጃ” ላይ እንድትሆን ማድረግን ነው።

    እንዲሁም እስራኤል፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኳታር፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ባህሬን፣ ኩዌት እና ሌሎችንም የመካከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካ አጋሮችን “በከፍተኛ ደረጃ መጠበቅ” ከግቦቹ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

    ፕሬዝዳንቱ በዚህ ልጥፋቸው የተለያዩ አገራትን እገዛ ጠይቀው በጎ ምላሽ ስላላገኙበት የሆርሙዝ ወሽመጥ ጉዳይም አንስተዋል።

    “እንደ አስፈላጊነቱ የሆርሙዝ ወሽመጥ በሚጠቀሙበት ሌሎች አገራት ሊጠበቅ እና ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል፤ አሜሪካ ግን አትጠቀምበትም!” ሲሉ የባሕር መስመሩን ማስከፈት የአገራቸው ኃላፊነት እንዳልሆነ አመልክተዋል።

    ይሁን እንጂ ወሽመጡን የሚጠቀሙበት አገራት የአሜሪካንን እገዛ ፈልገው ጥያቄ የሚያቀርቡ ከሆነ ግን “እናግዛቸዋለን” ብለዋል።

    “ነገር ግን አንዴ የኢራን ስጋት ከተወገደ በኋላ ግን [የሆስሙዝ ወሽመጥን መጠበቅ] አስፈላጊ አይሆንም። ቀላል ወታደራዊ ዘመቻ ይሆንላቸዋል” ሲሉ ጽፈዋል።

  7. ትራምፕ የኔቶ አጋሮቸውን ‘ፈሪዎች’፣ ኔቶን ደግሞ ‘የወረቀት ላይ ነብር’ ሲሉ ወረፉ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኔቶ አጋሮቻቸው የሆርሙዝ ወሽመጥን ከኢራን ጥቃት ለመጠበቅ እንዲተባበሯቸው ያቀረቡትን ጥያቄ ባለመቀበላቸው “ፈሪዎች” ሲሉ፣ ማኅበሩን ደግሞ አሜሪካ ባትኖርበት ደካማ ይሆን ነበር ሲሉ ተቹ።

    ፕሬዝዳንቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚተላለፉ መርከቦችን መጠበቅ ለኔቶ አባል አገራት “ቀላል” ይሆን ነበር በማለት ለመሳተፍ ባለመፍቀዳቸው “ፈሪዎች” በማለት ተችተዋቸዋል።

    ትራምፕ በትሩዝ የማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሠራጩት ጽሁፍ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን አገራት ማኅበር ኔቶን እና አባላቱን ክፉኛ አብጠልጥለዋቸዋል።

    "ካለ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ኔቶ የወረቀት ላይ ነብር ነው። ኢራን ኒውክሌር እንዳትታጠቅ በሚደረገው ፍልሚያ ውስጥ ለመሳተፍ አልፈለጉም።

    "አሁን ጦርነቱን በወታደራዊ ኃይል አሸንፈናል፣ እነሱ [የኔቶ አባላት] በነዳጅ ዋጋ መጨመር እያማረሩ ነው። ነገር ግን የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ለመጨመሩ ብቸኛው ምክንያት የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥን በቀላል ወታደራዊ ስሪት ለማስከፈት ለማገዝ ፈቃደኛ አልነበሩም” ሲሉ ወቅሰዋል።

    "በትንሽ ዋጋ በቀላሉ የሚፈጽሙት ነገር ነበር። ፈሪዎች፣ አንረሳውም!” በማለት የኔቶ አጋሮቻቸውን አጥብቀው ወርፈዋል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱትን ጥቃት ተከትሎ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በሚያልፉ ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ጥቃት በመፈጸሟል የነዳጅ ምርት መንቀሳቀስ ባለመቻሉ በዓለም ዙሪያ ዋጋው ጨምሯል።

    አሜሪካም የኔቶ አባል አገራት በወሽመጡ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን ደኅነንት በመጠበቅ እንዲያግዙ ብትጠይቅም ወደ ጦርነቱ መግባት እንደማይፈልጉ በመለግጽ ጥያቄውን ሳይቀበሉት በመቅረታቸው ትራምፕ ተቆጥተው ቆይተዋል።

  8. ኢራን የአሜሪካ እና የእስራኤል ባለሥልጣናትን በየትኛም ቦታ ዒላማ እንደምታደርግ ዛተች

    በአሜሪካ እና በእስራኤል ጥቃት በርካታ ባለሥልጣናቷ የተገደሉባት ኢራን በአጸፋው የአሜሪካንን እና የእስራኤልን ባለሥልጣናት እንዲሁም ወታደራዊ አዛዦችን በየትኛውም ቦታ ላይ ዒላማ እንደምታደርግ ዛተች።

    ዛሬ አርብ የኢራን መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ የአገሪቱ ጦር ኃይሎች ቃል አቀባይ የሆኑትን አቦልፋዚል ሼካርቺን ጠቅሶ እንደዘገበው በሁለቱ አገራት ባለሥልጣናት ላይ ለሚፈጽሙት ጥቃት የአገሪቱ ሠራዊት ክትትል እያደረገ መሆን አመልክቷል።

    ቃል አቀባዩ “ፈሪዎቹን ባለሥልጣኖቻችሁን፣ የጦር አዛዦቻችሁን፣ ፓይለቶቻችሁን እና ወታደሮቻችሁን በዐይነ ቁራኛ እየተከታተልናቸው ነው” ብለዋል።

    አክለውም "በዓለም ዙሪያ ባሏችሁ ፓርኮች፣ የመዝናኛ ቦታዎች እና ቱሪስቶች ውስጥ ባለን መረጃ መሠረት ከዚህ በኋላ ደኅንነታችሁ የተጠበቀ አይሆንም” በማለት ዒላማ እንደሚያደርጓቸው ዝተዋል።

    ሦስት ሳምንት በሆነው ጦርነት የአገሪቱን ጠቅላይ መሪን ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ባለሥልጣናት ኢራን ተገድለውባታል።

  9. በጦርነት ውስጥ ሆነው አዲስ ዓመታቸውን የተቀበሉት ኢራናውያን

    አሜሪካ እና እስራኤል የከፈቱባትን ጥቃት ተከትሎ ሦስት ሳምንት በሆነው ጦርነት ውስጥ የምትገኘው ኢራን በራሷ የዘመን አቆጣጠር መሠረት ዛሬ አርብ አዲስ ዓመቷን ጀምራለች።

    ‘ኖውሩዝ’ በመባል የሚጠራውን የፋርስ አዲስ ዓመት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ እየተጸመ ባለው ጥቃት እና ኢራን በበኩሏ በአጸፋው በምትሰነዝረው ጥቃት የጦርነት ስጋት ስር ሆነው ኢራናውያን እየተቀበለው ነው።

    በስጋት ውስጥ ያሉት ኢራናውያን አዲሱ ዓመት ምን ይዞ እንደሚመጣ እርግጠኛ አይደሉም።

    አሚር እንደለሚው "በጦርነቱ ምክንያት ሰዎች ሥራቸውን እያጡ ነው። ከሁሉ የሚያሳስበን የአገራችን መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደርሰው ጉዳት ነው” ብሏል።

    ለሦስት ሳምንታት በዘለቀው ያልተቋረጠ ጥቃት በርካታ የኢራን ተቋማት ዒላማ ሆነዋል።

    በዚህም ምክንያተ “በሚታየው ሁኔታ ብዙ የሚተርፍ ነገር የሚኖር አይመለስኝም። ይሄ የመጨረሻችን አዲስ ዓመት እንዲሆን አልፈልግም” በማለት አሚር ስጋቱን ገልጿል።

    ይህ የአዲስ ዓመት አከባበር ለጥንታዊቷ አገር ኢራን ዜጎች ታሪካቸው እና ብሔራዊ መለያቸው ሲሆን፣ ላለፉት ሦስት ሺህ ዓመታት ሲከበር የዘለቀ መሆኑ ይነገራል።

    ለወትሮው በአዲሱ የኢራን አዲስ ዓመት ወቅት በአገሪቱ የሚገኙ የገበያ ቦታዎች፣ የገበያ ማዕከላት እና መንገዶች በሕዝብ ተሞልተው የሚደምቁ ሲሆን፣ የዘንድሮው ግን ለየት ብሏል።

    ዘንድሮ የአዲስ ዓመት ድባቡ ቀዝቀዝ ያለ ቢሆንም፤ አንዳንድ ኢራናውያን በለመዱት መንገድ ለአዲሱ ዓመት በዓል አከባበር መዘጋጀታቸው ተዘግቧል።

    የዋና ከተማዋ ቴህራን ነዋሪ የሆነችው ፓርሚስ በዚህ ሁሉ ውስጥ ለበዓሉ ከተዘጋጁት መካከል ናት።

    "እንደ እኔ ሁሉ አንዳንዶች በዚህ ሁሉ ውስጥ የለመዱትን ማከናወን ቀጥለዋል። ለምሳሌ ከባድ ፍንዳታ በተከሰተበት ጊዜ የውበት ሳሎን ውስጥ ነበርኩ፣ ምንም እንዳልተፈጠረ ሁሉ ማንም ንቅንቅ አላለም” በማለት በዙሪያዋ ያሉ ሰዎች ካለው ሁኔታ ጋር እየተላመዱ መሆናቸውን ገልጻለች።

    *በዘገባው ውስጥ የተጠቀሱት ሰዎች ስም ለደኅንነታቸው ሲባል ተቀይሯል።

  10. የአቡ ዳቢ ፖሊስ ከ100 በላይ የተለያዩ አገራት ዜጎችን በቁጥጥር ስር አዋለ

    በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ የአቡ ዳቢ ፖሊስ የተለያዩ አገራት ዜግነት ያላቸው ከ100 በላይ ሰዎች በአገሪቱ ላይ ከሚፈጸመው ጥቃት ጋር በተያያዘ የተለያዩ ቦታዎችን “በመቅረጽ እና አሳሳች መረጃን” በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በማጋራት መያዙን አሳወቀ።

    ፖሊስ በኤክስ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ የተለያዩ 109 ሰዎች በሕዝቡ መካከል የተሳሳተ አመለካከትን የሚፈጥሩ እና ያልተረጋገጡ ወሬዎችን በማሠራጨት በቁጥጥር ስር አውሏል።

    ፖሊስ ጨምሮም ማኅበራዊ ሚዲያን ተገቢ ላልሆነ ዓላማ የሚጠቀሙ ሰዎችን በመከታተል የአገሪቱ የደኅንነት ባለሥልጣን አስፈላጊው ሕጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቋል።

    የአገሪቱ ዜጎች ወቅታዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ ከሚመለከታቸው አካላት እና ከሚታመኑ ምንጮች ብቻ መረጃ እንዲያገኙ በማሳሰብ የሕዝብ ጥቅምን እና አሠራሮችን በማክበር ከአንዳንድ ቦታዎች “ፎቶ ከማንሳት እና ቪዲዮ ከመቅረጽ እንዲሁም ከማጋራት እንዲቆጠቡ” አሳስቧል።

  11. አንድ የእስራኤል ሠራዊት አባል ለኢራን በመሰለል ተጠርጥሮ ተያዘ

    የእስራኤል ፖሊስ አንድ የአገሪቱ ጦር ተጠባባቂ አባል ለኢራን ሲሰልል ነበር በሚል ጥርጣሬ በቁጥጥር ስር መዋሉን ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

    የፈረንሳይ ዜና ወኪል የፖሊስ መግለጫን ጠቅሶ እንደዘገበው “ራዝ ኮኽን የተባለው የ26 ዓመቱ የኢየሩሳሌም ነዋሪ፣ ከኢራን ሰላዮች ጋር በመገናኘት በእነሱ መመሪያ መሠረት የስለላ ተግባር ማከናወንን ጨምሮ ሌሎች የደኅንነት ጥሰቶችን ፈጽሟል በሚል ተይዟል።”

    ተጠባባቂ ወታደሩ በእስራኤል የአየር ጥቃት መከላከያ ምድብ ውስጥ ተሰማርቶ የነበረ ሲሆን፣ “ከኢራን የስለላ አባላት ጋር ግንኙነት በመመሥረት በተለይ በሥራ አጋጣሚ የሚያገኘውን ጥብቅ መረጃ አሳልፎ በመስጠት እና ሌሎች ተግባራትን በመፈጸም” ተጠርጥሯል።

    ወታደሩ “ከኢራን ወኪሎች ጋር ግንኙነት እያደረገ እንደነበር” እንደሚያውቅ እና ገንዘብም ይከፈለው እንደነበር በተደረገበት ምርመራም መታወቁም ተገልጿል።

    ፖሊስ እና የእስራኤል የአገር ውስጥ ደኅንነት አገልግሎት (ሺም ቤት) የኢራን የስለላ ተቋም እስራኤላውያንን በመመልመል ወደ ተቋሞች ሰርጎ ለመግባት ጥረቶች እንደሚያደርግ በማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ሲያስጠነቅቁ ነበር።

  12. የአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት በኢስፋሃን የሚገኙ 21 ታሪካዊ ቅርሶችን ማውደሙ ተገለፀ

    የኢስፋሃን አስተዳዳሪ መህዲ ጃማልላይጃድ አገራቸው ከእስራኤል እና ከአሜሪካ ጋር እያደረገችው ባለው ጦርነት “21 ታሪካዊ ቅርሶች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል” ሲሉ ተናገሩ።

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን ጃማልላይጃድ ጠቅሰው ጉዳቱ “በቅርሶች ላይ 500 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ውድመት” ማድረሱን ዘግበዋል።

    አስተዳዳሪው የኢስፋሃንን ታሪካዊ ቅርሶች መጠበቅ “ብሔራዊ ኃላፊነት ነው” ማለታቸው የተዘገበ ሲሆን፣ የደረሰውን ጉዳት በሚመለከት “ካሳ እና ለመጠገን የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ሕጋዊ በሆነ መልኩ በሚመለከታቸው አካላት በኩል” እንደሚጠይቁ ተናግረዋል።

  13. ኢራን የብሪታኒያ ጦር ሠፈሮችን አሜሪካ እንድትጠቀም መፍቀድ “ጠብ አጫሪነት” ነው አለች

    ኢራን የብሪታኒያ ጦር ሠፈሮችን አሜሪካ እንድትጠቀም መፍቀድ “ጠብ አጫሪነት” ነው ስትል ለዩኬ መናገሯን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    አሜሪካ የዩኬን ወታደራዊ ጦር ሠፈር እንድትጠቀም መፍቀድ “በግጭት ውስጥ እንደመሳተፍ” እንደሚቆጠር ቴህራን ለዩኬ መግለጿን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ ከዩኬ አቻቸው ዪቬት ኩፐር ጋር ባደረጉት ውይይት ዩኬ ለአሜሪካ የምትሰጠው የትኛውም ድጋፍ “ሁኔታው እንዲባባስ” እንደሚያደርግ መናገራቸውን ተጠቅሷል።

    አራጋቺ ዩኬ እና ሌሎች የአውሮፓ አገራት አሜሪካ እና እስራኤል ለፈጸሙት “ግልጽ ጥቃት” የሚከተሉት “ለአንድ ወገን ያደላ አቀራረብ” መሆኑን በመናገር ወንጅለዋቸዋል።

    አራጋቺ በተጨማሪም ዩኬ የእስራኤል በሳውዝ ፓርስ የጋዝ ማምረቻ ላይ የፈጸመችውን ጥቃት ባለማውገዟ መተቸታቸው ተዘግቧል።

    በጉዳዩ ላይ የዩኬ መንግሥት እስካሁን ድረስ ምንም ያለው ነገር የለም። ቢቢሲ የዩኬ የውጭ ጉዳይ ቢሮን በጉዳዩ ላይ ምላሽ ቢጠይቅም ማግኘት አልቻለም።

  14. የኢራን አብዮታዊ ዘብ ቃል አቀባይ ተገደሉ

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ ቃል አቀባይ በአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት መገደላቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ ቃል አቀባይ እና ምክትል ሕዝብ ግንኙነት አሊ ሞሃመድ ናኢኒ በአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃቶች መገደላቸውን የአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን አስታውቋል።

    አሊ ሞሐመድ ናኢኒ የአብዮታዊ ዘቡን ለአራት አስርታት ያገለገሉ ሲሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ቃል አቀባይ በመሆን ሰርተዋል ሲል ፋርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    አሜሪካ እና እስራኤል የካቲት 21 2018 ዓ.ም. ኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱበት ዕለት አንስቶ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ በርካታ አመራሮች ተገድለዋል።

    የቀድሞው ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ጦርነቱ በጀመረ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የተገደሉ ሲሆን ሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ አመራሮችም የአሜሪካ እና የእስራኤል ጥቃት ዒላማ ሆነዋል።

  15. በቴህራን መሰማት የቀጠሉት ከባድ ፍንዳታዎች

    እስራኤል ኢራናውያን አዲስ ዓመታቸውን በሚያከብሩበት ወቅት በቴህራን ከፍተኛ የአየር ድብደባዎችን መፈጸሟ ተገለፀ።

    የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ፐርዢያ እንደተናገሩት ከባድ ፍንዳታዎች በዋና ከተማዋ ቴህራን ተሰምቷል። የእስራኤል ጦር “በኢራን በሚገኙ የመንግሥት መሠረተ ልማቶች ላይ” ጥቃቶችን መፈጸሙን አስታውቋል።

    ሐሙስ ዕለት እስራኤል በኢራን ላይ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች የሰላማዊ ሰዎች መኖሪያ ስፍራዎች መውደማቸውን ተከትሎ ስጋቶች ጨምረዋል።

    ሌሊቱን ቴህራን ወደ እስራኤል ሚሳዔሎችን ያስወነጨፈች ሲሆን ቴል አቪቭ ማክሸፏን አስታውቃለች።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ኢራን “መውደሟን” እና ዩራኒየም ማበልጸግም ሆነ ባሌስቲክ ሚሳዔል ማምረት አትችልም ሲሉ ተናግረዋል።

    በዚህ ሳምንት ቴህራን እስራኤል በሳውዝ ፓር ጋዝ ማምረቻ ስፍራ ላይ የፈጸመችውን ጥቃት ተከትሎ የአጸፋ እርምጃ የወሰደች ሲሆን ይህም የጋዝ ዋጋ እንዲጨምር አደርጓል።

    ሐሙስ ዕለት ዩናይትድ ኪንግደም እና ሌሎች አጋር አገራት በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚደረግ የመርከቦች ጉዞን አስተማማኝ ለማድረግ የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ “ዝግጁ” መሆናቸውን በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይ ጠቅሰዋል።

  16. በዓለም ግዙፉ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻ ላይ የደረሰው ውድመት ኳታርን ቢሊዮኖች ያስወጣታል- የኢነርጂ ሚኒስትሩ

    የኳታር ኢነርጂ ሚኒስትር ኢራን በራስ ላፋን የጋዝ ማምረቻ ተቋም ላይ የፈጸመችውን ጥቃት ተከትሎ ከፍተኛ ውድመት መድረሱን እና አገሪቱን ቢሊዮኖችን እንደሚያስወጣት ተናግረዋል።

    ኳታር ወደ ውጭ የምትልከው ፈሳሽ ተፈጥሯዊ ጋዝ (ኤልኤንጂ) በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ብቻ በ17 በመቶ የሚቀንስ ሲሆን አገሪቱ በዓመት 20 ቢሊዮን ዶላር አንድታጣ ያደርጋታል ብለዋል።

    ሚኒስተሩ አክለውም በኢራን ጥቃት ካሏቸው 14 ማምረቻዎች ሁለቱ ወድመዋል ብለዋል።

    ኢራን በኳታር ራስ ላፋን የተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻ ላይ ጥቃት የፈጸመችው ረቡዕ ዕለት እስራኤል በሳውዝ ፓርስ የጋዝ ማምረቻ ላይ ድብደባ መፈጸሟን ተከትሎ ነው።

    ከኳታር የተፈጥሮ ጋዝ የሚያገኙት የእስያ አገራት መካከል ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሕንድ እና ቻይና ይገኙበታል። ከአውሮፓ ደግሞ ጣሊያን እና ቤልጂየም ዋነኛ አስመጪዎች ናቸው።

    የዩክሬን ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲሀ ፊታቸውን ከሩሲያ ወደ መካለኛው ምሥራቅ ያዞሩት የእስያ አገራት ከኳታር በሚያገኙት የተፈጥሮ ጋዝ ላይ ጥገኛ ናቸው።

    በዓለም አቀፉ የተፈጥሮ ጋዝ ግብይት ውስጥ ኳታር ከቀዳሚዎቹ አገራት መካከል አንዷ ናት።

  17. የኩዌት ነዳጅ ማጣሪያ የድሮን ጥቃቶች ደረሰበት

    ምንም እንኳ ኢራን የምትፈጽማቸውን ጥቃቶች እንድታቆም ጥሪ ቢቀርብም የኩዌት መንግሥት የነዳጅ ድርጅት የሆነው ኬፒሲ ነዳጅ ማጣሪያዎቹ በበርካታ የድሮን ጥቃቶች መመታታቸውን አስታውቋል።

    እስካሁን ድረስ ስለደረሰው ጉዳት ይፋ የሆነ መረጃ የለም።

    በሚና አል አህማዲ የነዳጅ ማጣሪያ ላይ የተቀሰቀሰውን እሳት ለማጥፋት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች እየተረባረቡ ነው።

    የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የማጣሪያው የተወሰኑ ክፍሎች መዘጋታቸውን ዘግበዋል።

    የባሕረ ሰላጤው የነዳጅ መሠረተ ልማቶች በኢራን ተደጋጋሚ ጥቃቶችን አስተናግደዋል።

    እስራኤል የቴህራንን ጋዝ ማምረቻን ሳውዝ ፓርስን ካጠቃች በኋላ ኢራን በገልፍ ባሕረ ሰላጤው አገራት የሚገኙ የነዳጅ እና የጋዝ ማምረቻዎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ፈጽማለች።

    መላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ለአንድ ወር ቆየውን የረመዳን ጾም አጠናቅቀው ዛሬ የኢድ አል ፈጥር በዓልን እያከበሩ ቢሆንም በመካከለኛው ምሥራቅ የተጀመረው ጦርነት የሚቆም አይመስልም።

  18. የባሕረ ሰላጤው አገራት ላይ የሚፈጸመው የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃት

    የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ኩዌት፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ባህሬን ባለፉት ጥቂት ሰዓታት ውስጥ የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃቶች እንደተፈጸመባቸው ተናግረዋል።

    የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የመከላከያ ሚኒስቴር በአሁኑ ጊዜ ከኢራን የተተኮሱ ሚሳዔሎችን እና ድሮኖችን የማክሸፍ ሥራ እየሠራ መሆኑን ተናግሮ፣ የአገሪቱ ዜጎች የአየር መከላከያ ስርዓቶች ጥቃቶችን ሲያከሽፉ የሚፈጠሩ ፍንዳታዎችን ሊሰሙ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

    ኩዌት በአየር መከላከያ ስርዓቷ ምክንያት ስለሚፈጠሩ ፍንዳታዎች ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች፤ እናም ዜጎች ከባለሥልጣናት የተሰጡ የደህንነት መመሪያዎችን እንዲከተሉ ጠይቃለች።

    የሳዑዲ አረቢያ የመከላከያ ሚኒስቴር በአገሪቱ ምሥራቃዊ አካባቢ አምስት ተጨማሪ ድሮኖች መክሸፋቸውን እና ጥቃት መፈጸማቸውን አስታውቋል።

    የባህሬን የውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የአደጋ ጊዜ ደወል ከተሰማ ነዋሪዎች በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ደህንነቱ የተጠበቀ ቦታ እንዲሄዱ ጠይቋል። ሚሳዔሎቹ "ከኢራን የተተኮሱ" መሆናቸውን እና ስብርባሪው ያደረሰው ፍንዳታ በአንድ መጋዘን ላይ እሳት እንዳስከተለ ጨምሮ አስታውቋል።

  19. ኤፍቢአይ የኢራን የመረጃ መዝባሪዎች ይጠቀሙበታል ያላቸውን አራት ድረገጾች በቁጥጥር ስር አዋለ

    ኤፍቢአይ መቀመጫቸውን ኢራን አድርጎ በአሜሪካ ኩባንያዎች ላይ የሳይበር ጥቃት፣ የመረጃ ምዝበራ እና ምንተፋ የሚያካሄድ ቡድን የሚገለገልባቸውን አራት ድረ ገጾች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታወቀ።

    የአሜሪካ የፍትህ ቢሮ በቁጥጥር ሥር የዋለው "የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ የስለላ እና የደህንነት ሚኒስቴር የሚያካሄደውን የመረጃ ብርበራ እና የድንበር ተሻጋሪ ምንተፋ እቅዶችን ለማደናቀፍ የሚደረገው ቀጣይነት ያለው ጥረት አካል ነው" ብሏል።

    የፍትህ ቢሮ እንዳስታወቀው፣ የተያዙት ድረ ገጾች ጋዜጠኞችን፣ የአገዛዙን ተቃዋሚዎች እና የእስራኤልን ሕዝብ እንዲገደሉ ጥሪ ይተላለፍባቸው ነበር ብሏል።

    “ኢራን አሜሪካውያንን ለማሸበር እና ተቃዋሚዎችን ዝም ለማሰኘት የሐሰት ድረ ገጾችን እና ኪቦርድ ጀርባ ልትደብቅ እንደምትችል አስባ ነበር” ሲሉ የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ካሽ ፓቴል ተናግረዋል።

    “የዘመቻቸው አራቱን ምሰሶዎች አፍርሰናል፤ አልጨረስንም" ያሉት ፓቴል "ኤፍቢአይ ከእነዚህ ፈሪ የሞት ዛቻዎች እና የሳይበር ጥቃቶች በስተጀርባ ያሉትን ሁሉመም ተዋናዮች ያድናል፤ እንዲሁም የአሜሪካን የሕግ አስከባሪ ኃይሎች ሙሉ ኃይል በእነሱ ላይ ያዘምታል" ብለዋል።

  20. ኔታንያሁ ጦርነቱ “አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ ይቀጥላል” ሲሉ ተናገሩ

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ትናንት ምሽት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ኢራን “ከምንጊዜውም በላይ ደካማ ሆናለች” ሲሉ ተናግረዋል።

    ኢራን ዩራኒየም የማበልጸግም ሆነ ባሌስቲክ ሚሳዔል የመስራት አቅም አይኖራትም ሲሉ ተደምጠዋል።

    ይሁን አንጂ በኢራን ላይ እያካሄዱት ያለው ወታደራዊ ዘመቻ “አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ” ሊቀጥል ይችላል በማለት መቼ እንደሚያበቃ ከመናገር ተቆጥበዋል። ኔታንያሁ ጦርነቱ ሰዎች ከሚያስቡት ጊዜ ፈጥኖ ይጠናቀቃል ሲሉ ተናግረዋል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱት ወታደራዊ ዘመቻ ሦስት ግቦች አሉት ያሉት ኔታንያሁ የኒውክሌር እና የባሌስቲክ ሚሳዔልን ስጋት ማስወገድ እና ኢራናውያን “ነጻነታቸውን እንዲቀዳጁ” የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት መሆናቸውን ተናግረዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ እስራኤል አሜሪካን ወደዚህ ጦርነት ስባ አለማስገባቷን የተናገሩ ሲሆን ትራምፕ የራሳቸውን ውሳኔ ይወስናሉ ሲሉ በስፍራው ለተገኙ ጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም በቅርቡ በኢራን የተፈጥሮ ጋዝ መሠረተ ልማቶች ላይ የፈጸሙትን ጥቃት “እስራኤል ብቻዋን ያካሄደችው ነው” ካሉ በኋላ ትራምፕ ወደፊት የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለጊዜው ገታ አንዲያደርጉ እንደጠየቋቸው ተናግረዋል።