ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን ጦርነት ምክንያት የቻይናው ጉዟቸውን አራዘሙ
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ በኢራን ጦርነት ምክንያት ከሁለት ሳምንት በኋላ ሊያደርጉት የነበረውን ተጠባቂውን የቻይና ጉዟቸውን ለአንድ ወር በሚጠጋ ጊዜ ለማራዘም ማቀዳቸውን ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ በዋይት ሐውስ በጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ጉዞውን “በአንድ ወር ወይም እንዲያ አካባቢ ለማዘግየት ጥያቄ አቅርበናል” ብለዋል።
ትራምፕ እና የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ሺፒንግ ይገናኙበታል ተብሎ የሚጠበቀው ጉብኝት ከመጋቢት 22 እስከ 24/2018 ዓ.ም. እንዲካሄድ ቀጠሮ ተይዞለታል።
እንደ ትራምፕ ገለጻ ጉዞውን ማራዘም ውሳኔ ላይ የተደረሰው ከእስራኤል ጋር በመሆን ኢራን ላይ የከፈቱትን ጦርነቱን ለመምራት አገር ውስጥ መሆን አስፈላጊ በመሆኑ ነው።
“በጣም ቀላል ነው። ጦርነት እያካሄድን ነው። እዚህ መሆኔ አስፈላጊ ይመስለኛል” ሲሉ ተናግረዋል። ትራምፕ እዚህ ውሳኔያቸው ውስጥ “ምንም ማታለል” እንደሌለበት አጽንኦት የሰጡ ሲሆን የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጋር መገናኘት እንደሚፈልጉም አክለዋል።
ትራምፕ ይህንን ያሉት ከብሪታኒያው ጋዜጣ ፋይናንሻል ታይምስ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፤ ቻይና ሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲከፈት የማታግዝ ከሆነ ጉብኝታቸው ሊያራዝሙ እንደሚችሉ ከተናገሩ በኋላ ነው።
በሁለቱ ግዙፍ የዓለም ኢኮኖሚዎች መካከል ያለው ፍትጊያ በኢራን ጦርነት ምክንያት ተባብሷል። የኢራን የኢነርጂ ኤክስፖርት ዋነኛ ገዢ የሆነችው ቻይና አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ ከፈቱትን ጥቃት ተቃውማለች።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ በበኩላቸው “ከፕሬዝዳንት ትራምፕ የቻይና ጉብኝት ቀን እና ተያያዥ ጉዳዮችን” በተመለከተ ቤይጂንግ እና ዋሽንግተን እየተነጋገሩ መሆኑን ማክሰኞ ዕለት ገልጸዋል።