ከ640ሺህ በላይ ሊባኖሳውያን ስደተኞች ወደ ቤታቸው መመለሳቸው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ግጭቶች መርገባቸውን ተከትሎ ከ640 ሺህ በላይ ሊባኖሳውያን ስደተኞች ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም (አይኦኤም) አስታወቀ።
የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነትን ለማስቆም ስምምነቶች በመፈረማቸው እና ግጭት በመቆሙ ስደተኞቹ መመለሳቸውን ተቋሙ ገልጿል።
ተቋሙ እንዳለው አሁንም ድረስ ወደ 500 ሺህ የሚሆኑ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬያቸው መመለስ አልቻሉም።
አይኦኤም አሐዙን ይፋ ያደረገው ከሊባኖስ ባለሥልጣናት ጋር በመሆን ከአውሮፓውያኑ ሰኔ 22 ጀምሮ መረጃ አሰባስቦ ነው።
በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ በእስራኤል ላይ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ሊባኖስ ወደ ቀጣናዊው ጦርነት ገብታለች።
እስራኤል በአየር ጥቃት እና በደቡብ ሊባኖስ እግረኛ ጦር በማሰማራት የአጸፋ ምላሽ አድርጋለች። አሁንም የተወሰኑ የደቡብ ሊባኖስ አካባቢዎች በእስራኤል ጦር ይዞታ ሥር ይገኛሉ።
እስራኤል ባደረሰችው ጥቃት ወደ 4,300 ሰዎች እንደተገደሉ እና በተለይ ከደቡብ የአገሪቱ ክፍል እና ከደቡብ ቤሩት ሚሊዮኖች እንደተፈናቀሉ ሊባኖስ አስታውቃለች።
ኢራን እና አሜሪካ የፈረሙት የመግባቢያ ሰነድ ሊባኖስን ጨምሮ በሁሉም የጦር ግንባሮች ውጊያ ማቆምን ያካትታል።
ከስምምነቱ በኋላ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ደቡብ ሊባኖስ አካባቢዎች እና ደቡብ ቤሩት እየተመለሱ ይገኛሉ።






















