ቀጥታ, በአያቶላህ ዓሊ ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት “እስከ 20 ሚሊዮን ሰዎች” ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገለጸ

በቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ ዓሊ ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት የመጀመሪያ ቀን በርካቶች ታድመዋል። የኻሜኒ አስከሬን ባለበት የቴህራን ትልቁ መስጊድ የተገኙት ሰዎች ጥቁር በጥቁር ለብሰው ሐዘናቸውን እየገለጹም ነው።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በአያቶላህ ዓሊ ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት “እስከ 20 ሚሊዮን ሰዎች” ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገለጸ

    የአያቶላህ ዓሊ ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ ዓሊ ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት የመጀመሪያ ቀን በርካቶች ታድመዋል።

    የኻሜኒ አስከሬን ባለበት የቴህራን ትልቁ መስጊድ የተገኙት ሰዎች ጥቁር በጥቁር ለብሰው ሐዘናቸውን እየገለጹም ነው።

    የኢራን ባለሥልጣናት እንዳሉት በኢራን እና በኢራቅ ለቀናት በሚካሄደው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ “ከ15 እስከ 20 ሚሊዮን” የሚደርሱ ሰዎች እንደሚገኙ ይጠበቃል።

    በርካታ የኢራን መንግሥት ደጋፊዎች ዛሬ ቅዳሜ አደባባይ ወጥተው ለኻሜኒ ግድያ አሜሪካ ላይ የበቀል እርምጃ እንዲወሰድ የሚጠይቁ መፈክሮች አሰምተዋል።

    የ37 ዓመቱ ፕ/ር ረዛ “ወደ ቀብር ሥነ ሥርዓቱ የመጣነው ከጠቅላይ መሪው ጋር እስከመጨረሻው አብረን ለመቆም ቃል ስለገባን ነው” ሲል ለኤኤፍፒ ተናግሯል።

    “ለረዥም ጊዜ ራሳችንን ለጠቅላይ መሪው ስንል መስዋዕት እንደምናደርግ ተናግረናል። እሳቸው ግን ለእኛ ሲሉ መስዋዕት ሆኑ” በማለትም አክሏል።

    የ40 ዓመቱ አራሽ ራሐሚ ደግሞ “ሁሉም እዚህ የመጣው የጠቅላይ መሪውን ሞት ለመበቀል ነው” ሲል ለሮይተርስ ተናግሯል።

    ከአራት ወራት በፊት አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት መሰንዘር ሲጀምሩ ነበር ኻሜኒ የተገደሉት።

    ቀብራቸው የሚፈጸመው በትውልድ ከተማቸው ማሻሀድ የፊታችን ሐሙስ ይሆናል። እስከዚያም አስከሬናቸው በቴህራን በሚገኘው ግራንድ ሞሳላ መስጊድ ይቆያል።

    የአያቶላህ ዓሊ ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአያቶላህ ዓሊ ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአያቶላህ ዓሊ ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

  2. ከ640ሺህ በላይ ሊባኖሳውያን ስደተኞች ወደ ቤታቸው መመለሳቸው ተገለጸ

    ሊባኖሳውያን ወደ ቤታቸው ሲመለሱ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ግጭቶች መርገባቸውን ተከትሎ ከ640 ሺህ በላይ ሊባኖሳውያን ስደተኞች ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም (አይኦኤም) አስታወቀ።

    የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነትን ለማስቆም ስምምነቶች በመፈረማቸው እና ግጭት በመቆሙ ስደተኞቹ መመለሳቸውን ተቋሙ ገልጿል።

    ተቋሙ እንዳለው አሁንም ድረስ ወደ 500 ሺህ የሚሆኑ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬያቸው መመለስ አልቻሉም።

    አይኦኤም አሐዙን ይፋ ያደረገው ከሊባኖስ ባለሥልጣናት ጋር በመሆን ከአውሮፓውያኑ ሰኔ 22 ጀምሮ መረጃ አሰባስቦ ነው።

    በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ በእስራኤል ላይ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ሊባኖስ ወደ ቀጣናዊው ጦርነት ገብታለች።

    እስራኤል በአየር ጥቃት እና በደቡብ ሊባኖስ እግረኛ ጦር በማሰማራት የአጸፋ ምላሽ አድርጋለች። አሁንም የተወሰኑ የደቡብ ሊባኖስ አካባቢዎች በእስራኤል ጦር ይዞታ ሥር ይገኛሉ።

    እስራኤል ባደረሰችው ጥቃት ወደ 4,300 ሰዎች እንደተገደሉ እና በተለይ ከደቡብ የአገሪቱ ክፍል እና ከደቡብ ቤሩት ሚሊዮኖች እንደተፈናቀሉ ሊባኖስ አስታውቃለች።

    ኢራን እና አሜሪካ የፈረሙት የመግባቢያ ሰነድ ሊባኖስን ጨምሮ በሁሉም የጦር ግንባሮች ውጊያ ማቆምን ያካትታል።

    ከስምምነቱ በኋላ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ደቡብ ሊባኖስ አካባቢዎች እና ደቡብ ቤሩት እየተመለሱ ይገኛሉ።

  3. ሁቲዎች በሳዑዲ አውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ ጥቃት ለማድረስ ዛቱ

    የየመን ሁቲ አማጺያን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የየመን ሁቲ አማጺያን የሳዑዲ አረቢያን አውሮፕላን ማረፊያዎች እና ሌሎችም ቁልፍ ሥፍራዎችን የጥቃት ዒላማ እንደሚያደርጉ ዛቱ።

    ሁቲዎች፤ የኢራን የሲቪሎች አውሮፕላን በሰንዓ አውሮፕላን ማረፊያ እንዳያርፍ ከልክለዋል ካሏቸው “የሳዑዲ ተዋጊዎች” ጋር ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ገልጸዋል።

    የሁቲ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ፤ ሳዑዲ “የየመንን የአየር ክልል መጣስ የምትቀጥል ከሆነ በየብስ እና በባሕር ላይ ያሉ ቁልፍ ሥፍራዎችን እና አውሮፕላን ማረፊያዎችን የጥቃት ዒላማ” እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

    ውዝግቡ እንዳለ ሆኖ በሰንዓ እና ቴህራን መካከል ያለው በረራ መቀጠሉን ተናግረዋል።

    በሳዑዲ የሚመራው ጥምር፣ ሁቲዎች ላወጡት መግለጫ በሰጠው ምላሽ “መግለጫው ቡድኑ በየመን ሕዝብ ላይ የሚፈጽመውን ድርጊት ትኩረት ለማስለወጥ ያለመ ነው” ብሏል።

    ለሁቲ ቅርበት ያለው አል-ማሲራህ ቴሌቭዥን እንደዘገበው፤ የኢራን አውሮፕላን ሰንዓ የደረሰው ትናንት አርብ ነው።

    የሁቲ ልዑካንን ወደቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ ዓሊ ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት ለመውሰድ አውሮፕላኑ መጓዙ ተገልጿል።

    ሳዑዲ የምትመራው ጥምር ጦር በበኩሉ የሳዑዲን አልያም የየመንን ሉዓላዊነት የሚገዳደር ሙከራ ላይ “ጠንካራ እርምጃ” እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።

    ከአውሮፓውያኑ 2015 ጀምሮ ጦሩ በየመን ጦርነት ውስጥ ተሳትፎ ማድረጉን ቀጥሏል።

  4. የሩሲያ ጦር በቻይና ሥልጠና አድርጓል መባሉን ተከትሎ ጀርመን የቤይጂንግን አምባሳደር አነጋገረች

    ዢ ጂንፒንግ እና ፑቲን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የሩሲያ ጦር በቻይና ሥልጠና እያደረገ ነው የሚል ሪፖርት መውጣቱን ተከትሎ ጀርመን ከቤይጂንግ አምባሳደር ማብራሪያ መጠየቋን አስታወቀች።

    የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ ቻይና ለሩሲያ ጦር ድጋፍ ማድረጓን የሚጠቁመው መረጃ “በጣም አሳሳቢ ነው” ብሏል።

    በዚህም ምክንያት የቻይናው አምባሳደር ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠርተዋል።

    “ሩሲያ በዩክሬን ላይ የቀጠለችውን ጦርነት የሚደግፍ ማንኛውም ድርጊት ለደኅንነታችን አስጊ ነው” ሲልም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

    የጀመርን መንግሥት ቻይና ለሩሲያ ታደርጋለች የተባለውን ድጋፍ በተመለከተ ያለውን ቅሬታ በተደጋጋሚ ለቤይጂንግ ገልጿል።

    መራሔ መንግሥት ፍሬድሪክ ማርትዝ ከወራት በፊት ወደ ቻይና ሲጓዙም ይሄንኑ መግለጻቸው ተዘግቧል።

  5. ከሩሲያ አደጋ የተጋረጠባት ፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር “ቀጣይ ወራት ወሳኝ ናቸው” አሉ

    የፖላንድ ጦር

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ከሩሲያ አደጋ የተጋረጠባት ፖላንድ “ለተለያዩ ሁኔታዎች ራሷን እያዘጋጀች” እንደምትገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ ተናገሩ።

    ሞስኮ ወታደራዊ “ትንኮሳ” ልትፈጽም ትችላለች የሚሉ ሪፖርቶችን በተመለከተም ቀጣዮቹ ወራት “ወሳኝ” መሆናቸውን ገልጸዋል።

    የአሜሪካ የደኅንነት መረጃዎችን በመጥቀስ የወጡ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፤ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) አቅምን ለመፈተሽ ሩሲያ ፖላንድ ላይ ጥቃት ልትሰነዝር ትችላለች።

    “ማንንም ማስፈራራት አልፈልግም። የጦርነቱ ሁኔታ እየተለወጠ ከመሆኑ አንጻር ግን ቀጣዮቹ ወራት በጣም ወሳኝ ናቸው። በባልቲክ አገሮች ስጋቱ አንዣብቧል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

    የፖላንዱ ኦኔት ለፕሬዝዳንት ካሮል ናዋርኮኪ ቅርብ የሆኑ ምንጮችን እንደዘገበው፤ አሜሪካ ሩስያ የምታደርሰውን ጥቃት በተመለከተ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ለዋርሳው ሰጥታለች።

    ቢቢሲ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከዋይት ሀውስ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

    የዩናይትድ ኪንግደሙ ዘ ቴሌግራፍ ባወጣው ዘገባ መሠረት የፖላንድ መሠረተ ልማቶች በሚሳዔል ወይም በድሮን ሊመቱ የሚችሉ ሲሆን፤ የኔቶ አባል ወደሆነችው አገር ወታደሮች ሊሰማሩ የሚችሉበትም ዕድል አለ።

  6. ለቀናት የሚዘልቀው የኢራን የቀድሞ ጠቅላይ መሪ የቀብር ሥነ ሥርዓት ተጀመረ

    የቀብር ሥነ ሥርዓት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የኢራን የቀድሞ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ ዓሊ ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት እና ሕዝባዊ ሐዘን ተጀምሯል።

    ከአራት ወራት በፊት አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት መሰንዘር ሲጀምሩ ነበር ኻሜኒ የተገደሉት።

    ቀብራቸው የሚፈጸመው በትውልድ ከተማቸው ማሻሀድ የፊታችን ሐሙስ ይሆናል። እስከዚያም አስከሬናቸው በቴህራን በሚገኘው ግራንድ ሞሳላ መስጊድ ይቆያል።

    የኢራን ባለሥልጣናት “የዘመኑ የቀብር ሥነ ሥርዓት” ሲሉ ክንውኑን የገለጹት ሲሆን፤ ከ12 እስከ 20 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች እንደሚገኙ ተገልጿል።

    ኢራን እና አሜሪካ የመግባቢያ ሰነድ ከተፈራረሙ በኋላ ለተወሰኑ ቀናት የተኩስ ልውውጦች ቢደረጉም፤ ወደ ድርድር ለመመለስ ተስማምተዋል።

    ትናንት አርብ የኻሜኒ የሬሳ ሳጥን በኢራን ሰንደቅ ዓላማ ተሸፍኖ መስጊድ ውስጥ ታይቷል።

    በሥፍራው ከተገኙ መካከል የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዤሽኪያን ይገኙበታል።

    አሜሪካ እና ኢራንን ያደራደረችው የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሻባዝ ሻሪፍ፣ የቀድሞው የሩሲያ ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ማድቬዴቭ እና የአፍጋኒስታኑ ታሊባን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሚር ካሀን ሙታቂም ተገኝተዋል።

    የቀብር ሥነ ሥርዓት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የቀብር ሥነ ሥርዓት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

  7. እስራኤል የኢራን ተደራዳሪዎችን ለመግደል እያሴረች እንደነበር ተዘገበ

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ ጋሊባፍ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አራግቺ

    የፎቶው ባለመብት, Getty

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ ጋሊባፍ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አራግቺ

    አሜሪካና ኢራን ወሳኝ የሆነውን የተኩስ አቁም ስምምነት በደረሱበት እስራኤል የኢራንን ከፍተኛ ተደራዳሪዎች ለመግደል እያሴረች እንደነበር የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንደሚያምኑ ‘ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ’ ጋዜጣ ዘገበ።

    ባለፈው ሚያዝያ አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱን በተኩስ አቁም ጋብ ለማድረግ ያስቻለው ንግግር ወደ መቋጫው ሲቃረብ ዋነኛ የኢራን ተደራዳሪዎች የሆኑት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ እና የፓርላማው አፈ ጉባኤ መሐመድ ባገር ጋሊባፍ የእስራኤል ዒላማ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ስጋት አሜሪካ ተፈጥሮባት እንደነበር ባለሥልጣናት መናገራቸውን ጋዜጣው አስነብቧል።

    እንደ ዘገባው ከሆነ ከፍተኛ ስጋት የተፈጠረበት የትራምፕ አስተዳደር እስራኤል ሁለቱን የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ዒላማ ልታደርግ እንደምትችል ቴህራንን እንዲያስጠነቅቁ በአካባቢው አገራት በኩል መልዕክት አስተላልፏል።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናት በሚያዝያ ወር ድርድሩ ከተጀመረ በኋላ የሚደረግ ማንኛውም የግድያ ሙከራ ውይይቱን እንደሚያቆመው እና ግጭቱን እንደገና እንደሚያባብሰው ስላመኑ ነበር ስጋት የተፈጠረባቸው ተብሏል።

    የኢራኑ ፓርላማ አፈ ጉባዔ እና ዋነኛው ተደራዳሪ ጋሊባፍ የእስራኤል የግድያ ዒላማ ዝርዝር ውስጥ መግባታቸውን አሜሪካ ከተረዳች በኋላ እስራኤል ምንም ዓይነት እርምጃ እንዳትወስድ እንዳሳሰበች ጋዜጣው ዘግቧል።

    የኢራን ባለሥልጣናት እስራኤል በዲፕሎማሲያዊ ስብሰባዎች ወቅት የድርድር ቡድኗን ዒላማ እንዳታደርግ በፓኪስታን እና በኳታር አሸማጋዮች በኩል የአሜሪካን ዋስትና እንደምትፈልግ መጠየቋንም ጠቅሷል።

    ዘገባው ጨምሮም ሚያዝያ ወር ላይ የኢራን የደኅንነት ኃይሎች ሁለት የእስራኤል አውሮፕላኖች ወደ ኢራን የአየር ክልል መግባታቸውን በመጥቀስ ከፓኪስታን ወደ ቴህራን የመልስ በረራ ወደ ላይ የነበሩት ጋሊባፍ አቅጣጫቸውን ቀይረው ማሽሃድ ወደተባለችው የኢራን ከተማ ማምራታቸውን ገልጿል።

    ዘገባውን በተመለከተ በአሜሪካ የሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ ባለሥልጣናት አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ጋዜጣው አመልክቷል።

  8. አሜሪካዊው እስራኤል ውስጥ ለኢራን በመሰለል ተያዘ

    የእስራኤል የፀጥታ ኃይል አባላት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አንድ ነዋሪነቱ እስራኤል ውስጥ የሆነ አሜሪካዊ አይሁድ ለኢራን በመሰለል ክስ እንደተመሠረተበት የእስራኤል ዐቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

    ኢየሩሳሌም ውስጥ ተማሪ የሆነው የ21 ዓመቱ አሜሪካዊ ኤሊ ላቮን በእስራኤል ላይ ለሚያካሂደው ስለላ ከኢራን በኩል በክሪፕቶከረንሲ ክፍያ እንደሚሰጠው ተገልጿል።

    የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ግለሰቡ ከኢራን የስለላ ወኪሎች ጋር ግንኙነት የጀመረው በኅዳር 2025 ቤተሰቦቹን ለመጠየቅ ወደ አሜሪካ በሄደበት ጊዜ በቴሌግራም ላይ ለወጣ የሥራ ማስታወቂያ ምላሽ ከሰጠ በኋላ ነው።

    ከአንድ ወር በኋላም ወጣቱ ወደ እስራኤል ሲመለስ የኢራን የስለላ ተቋምን የወከለ ሰው በቴሌግራም መልዕክት በማስተላለፍ ፎቶዎችን እንዲያነሳ እና ቪዲዮዎችን እንዲቀርጽለት ትዕዛዝ እንደተሰጠው በቀረበበት ክስ ላይ ተመልክቷል።

    በተጨማሪም የተለያዩ ቦታዎችን ቪዲዮ መቅረጹን እና የታዘዘውን መፈጸሙን የሚገልጽ መልዕክት ማስተላለፉ የተገለጸ ሲሆን፣ ለዚህ ሥራውም በመቶዎች የሚቆጠር ዶላር በክሪፕቶከረንሲ እንደተከፈለው ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።

    እስራኤል ባለፉት ዓመታት በርካታ የስለላ ድርጊቶች ያጋጠሟት ሲሆን አሁን የተከሰሰው ወጣት በዚህ ድርጊት የተያዘ የመጀመሪያው አሜሪካዊ ነው።

    ዐቃቤ ሕግ እንደሚለው በኢራን የተመለመሉ ሰላዮች ካስተላለፏቸው ቪዲዮች መካከል በርካታዎቹ ኢራን ላይ በፈጸመቻቸው የሚሳዔል ጥቃቶች ዒላማ ሆነዋል።

    ባለፈው ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ በቁጥጥር ስር የዋለው ላቮን ላይ ከውጭ የስለላ ወኪል ጋር በመገናኘት ሁለት ክሶች እንዲሁም ለጠላት ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችን አሳልፎ በመስጠት 14 ክሶች እንደቀረቡበት ተዘግቧል።

  9. በፈረንሳይ ከከፍተኛ ሙቀት ጋር በተያያዘ ከ2 ሺህ በላይ ተጨማሪ ሞቶች ተመዘገቡ

    ጃንጥላ የተዘረጋላቸው አዛውንት ከሁለት ሰዎች ጋር መንገድ ሲያቋርጡ

    የፎቶው ባለመብት, Thibaut Durand / Hans Lucas / AFP via Getty Images

    ፈረንሳይ ባለፈው ሳምንት ከ2 ሺህ በላይ ተጨማሪ ሞቶችን መመዝገቧን አስታወቀች።

    ይህ የተመዘገበው በአውሮፓ ከፍተኛው ሙቀት በተመዘገበበት የአውሮፓውያኑ ሰኔ ወር የመጨረሻ ሳምንት ነው።

    በዚህ ሳምንት ከከፍተኛ ሙቀት ጋር ተያይዞ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ቀድሞ ከነበረው ሳምንት ጋር ሲነፃፀር 29 በመቶ ጨምሯል።

    በፓሪስ ብቻ የሟቾች ቁጥር 62 በመቶ መጨመሩ ተገልጿል።

    የፈረንሳይ የጤና ሚኒስትር ስቴፋኒ ሪስት ዕድሜያቸው ከ45 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ሞት መጨመሩን ገልጸዋል።

    በፈረንሳይ ሰኔ 24 በአማካይ ሞቃታማው ቀን ሆኖ አልፏል።

    የሙቀት መጠኑ በመዲናዋ ፓሪስ 41 ዲግሪ ሴትንቲ ግሬድ የነበረ ሲሆን ግማሹ የአገሪቷ ክፍል በቀይ የማስጠንቀቂያ ዞን ውስጥ ገብቷል።

    ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በሌሎች የአውሮፓ ክፍሎችም ሙቀቱ ያየለ ሲሆን አዲስ ሞቶች ተመዝግበዋል።

    የአየር ንብረት ትንበያ ባለሙያዎችም በሚቀጥሉት ቀናት በአሕጉሪቱ ከፍተኛ የሙቀት መጠን እንደሚኖር አስጠንቅቀዋል።

  10. ዩናይትድ ኪንግደም በየቀኑ ለ30 ደቂቃ በእግር የሚጓዙ ዜጎቿን ልትሸልም ነው

    በእግራቸው የሚጓዙ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ብሔራዊ ጤና አገልግሎት (NHS) የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለሚያደርጉ የአገሪቱ ዜጎች ሽልማት መስጠት ሊጀመር ነው።

    አገልግሎቱ ከቀጣዩ የአውሮፓውያን አዲስ ዓመት አንስቶ ሰዎች በቀን ለ30 ደቂቃ በእግራቸው እንዲጓዙ የሚጠይቀውን ‘ማራቶን ኤ መንዝ’ የተሰኘ መርሃ ግብር ይፋ ያደርጋል።

    መርሃ ግብሩ ይህንን ስያሜ ያገኘው፤ ያለ ማቋረጥ በየቀኑ ለ30 ደቂቃ የሚጓዙ ሰዎች በአንድ ወር ውስጥ የማራቶን ሩጫ ውድድር ርቀት የሆነውን 41 ኪሎ ሜትር መራመድ ስለሚችሉ ነው።

    ተጠቃሚዎች ሞባይል ስልካቸውን ወይም ‘ስማርት ዎች’ በመጠቀም በየቀኑ የተጓዙት ርቀት መጠን ማስመዝገብ ይችላሉ።

    በአንድ ወር ውስጥ የማራቶን ርቀትን መጓዝ የቻሉ ሰዎች ለሽልማት ብቁ እንደሚሆኑ ተገልጿል። ሽልማቱ ጥቅማ ጥቅም እና የዋጋ ቅናሽ ሊሆን ይችላል።

    የዩኬ ብሔራዊ ጤና አገልግሎት ይህንን መርሃ ግብር ያዘጋጀው፤ኦሊምፒክ ሜዳሊያ አሸናፊው ብሬንዳን ፎስተር ጋር በመተባበር ነው። በየቀኑ የተጓዙት የእርምጃ ብዛት የሚያስመዘግቡ ሰዎችን ብዛት 100,000 እንዲደርስ ለማድረግ ታቅዷል።

    ለመርሃ ግብሩ የሚሆነው የመጀመሪያው በጀት በአገልግሎቱ የሚሸፈን ሲሆን፣ ወደፊት ግን ግዙፍ ኩባንያዎች የሚደግፉት የበጎ አድራጎት እንዲሆን ታስቧል።

    ቢቢሲ ያነጋገራቸው ዕድሜያቸው ከ25 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች በሃሳቡ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል። ላውረን አንድሪው የተባለች አንዲት ወጣት ሀሳቡ ጥሩ ነው ብላ እንደምታስብ ተናግራለች።

    “አደርገዋለሁ” የምትለው ላውረን፤ ለሽልማት የተዘጋጀው ጥቅማጥቅም እና የዋጋ ቅናሽ ግን በሌላ ቢቀየር ትመርጣለች። “እርምጃዬ ወደ እንደ መጠጥ እና ምግብ ባሉ በነጻ የሚሰጡ ነገሮች ቢቀየር ለመራመድ ይረዳኛል” ብላለች።

  11. በሶሪያ ዋና ከተማ ካፌ ውስጥ በደረሰ ፍንዳታ ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

    ጥቃት በደረሰበት ካፌ የቆሙ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በማዕከላዊ ደማስቆ በደንበኞች በተሞላ ካፌ ውስጥ በደረሰ የቦንብ ፍንዳታ ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውን የሶሪያ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገበ።

    የሶሪያ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር፤ ካፌ ውስጥ ፈንጂ መሣሪያ ተጠምዶ እንደነበር ገልጿል። ጥቃት የደረሰበት ካፌ ዋና ዋና የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ከሚገኙበት ‘ፓላስ ኦፍ ጀስቲስ’ ከተባለው ሕንጻ 100 ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው።

    እስካሁን ድረስ ለጥቃቱ ኃላፊነት የወሰደ አካል የለም። ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተፈጸመ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት 25 ሰዎች ከተገደሉ በኋላ መሰል ፍንዳታ ሲደርስ የአሁኑ የመጀመሪያው ነው።

    በወቅቱ ‘ሳራያ አንሳር አል ሱናህ’ የተባለው ጂሃዳዊ ቡድን ከፍንዳታው ጀርባ እጁ እንዳለ ቢገልጽም፤ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለጥቃቱ ተጠያቂ ያደረጉት ኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) የተባለውን ቡድን ነበር።

    የአሁኑ ጥቃት ከደረሰበት ካፌ አጠገብ የሚገኝ መደበር ባለቤት የሆነ ግለሰብ ፍንዳታው በሶሪያ የእርስ በእስር ጦርነት ወቅት ደማስቆ ውስጥ ይደርሱ ከነበሩ ፍንዳታዎች ጋር ተመሳሳይ እንደሆነበት ተናግሯል።

    ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የወጣ አንድ ምስል ላይ እንቅስቃሴ የሌላቸው ቢያንስ ሁለት ሰዎች በካፌው በረንዳ ላይ ተኝተው ያሳያል።

    ከጥቃቱ በኋላ በስፍራው የተገኙት የደማስቆ ገዥ ማህር ማርዋን ኢድሊቢ፤ ለዚህ ገዳይ ጥቃት ተጠያቂ የሆኑ አካላት እንደሚቀጡ ተናግረዋል። “አገሪቱ የመረጋጋት ጊዜ ውስጥ በገባች ቁጥር ተንኮለኛ አካላት ለመበጥበጥ ይሞክራሉ” ሲሉም ወቅሰዋል።

    በእስላማዊ ኃይሎች የሚመሩ አማጺያን ከ13 ዓመት አውዳሚ የእስር በእስር ጦርነት በኋላ ባለፈው ዓመት ታህሳስ ላይ በሽር አል አሳድን ከጣሉ ወዲህ ደማስቆ ውስጥ በርካታ ጥቃቶች ተፈጽመዋል።

    ጊዜያዊ ፕሬዝዳንቱ አህመድ አል ሻራ ወደ ሥልጣን ከወጡ ወዲህ በመላው አገሪቱ ያላቸውን ቁጥጥር ለማጠናከር እና የአገሪቱን ደኅንነት ለመመስ እየታገሉ ነው።

  12. በአፍሪካ እና አውሮፓ የአሜሪካ ምድር ኃይል አዛዥ የሆኑት ጄነራል ሥልጣናቸውን ለቀቁ

    ጄነራል ክሪስቶፈር ዶናሂው

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    በአፍሪካ እና በአውሮፓ የሚገኘው የአሜሪካ የምድር ኃይል እንዲሁም የኔቶ ምድር ኃይል አዛዥ የሆኑት ጄነራል ክሪስቶፈር ዶናሂው ኃላፊነታቸውን በይፋ ለቀቁ።

    ከአንድ ዓመት በላይ በኃላፊነቱ ላይ የቆዩት ጄነራል መልቀቃቸው የታወቀው ከሳምንት በፊት ቢሆንም በይፋ የተሰናበቱት ትናንት ሐሙስ ነው።

    የአሜሪካ ሠራዊት ጄነራሉ ከኃላፊነት የወረዱበት ምክንያቱ ምን እንደሆነ እስካሁን አልገለጸም። ለቦታው ተተኪ እስኪሾም ድረስ ሜጀር ጄነራል ክሪስቶፈር ኖሬዬጋ በአፍሪካ እና በአውሮፓ የሚገኙ የአሜሪካ ኃይሎችን በተጠባባቂነት እንደሚመሩ ተገልጿል።

    የጄነራል ክሪስቶፈር ዶናሂው ከኃላፊነት መልቀቅ የታወቀው የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ፔት ሄግሴት በጦር ኃይሉ ከፍተኛ አዛዦች ላይ መጠነ ሰፊ ለውጥ ማካሄድ መጀመራቸውን ተከትሎ ነው። ባለ አራት ኮከብ ጄነራሎች ዝቅ ብለው ባለ ሦስት ኮከብ አዛዥ እንዲሆኑ እንደሚደረግ ተገልጿል።

    አሁን ኃላፊነታቸውን የለቀቁት ጄነራል ወደ አፍሪካ እና አውሮፓ የአሜሪካ የምድር ኃይል አዛዥነት ከመምጣታቸው በፊት 18ኛውን አየር ወለድ ጓድን እንዲሁም 82ኛው አየር ወለድ ክፍልን መርተዋል።

    ጄነራሉ በተለይ የሚታወቁት የአሜሪካ ኃይሎች በ2021 አፍጋኒስታንን ለቅቀው ሲወጡ የመጨረሻው የአሜሪካ ወታደር በመሆናቸው ነው።

  13. እስከ 100 ቢሊዮን ዶላር የሚገመተው የኢራን የታገደ ሀብት የት ነው ያለው?

    ኻሜኒ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ከየካቲት አንስቶ በአሜሪካ እና በእስራኤል የተከፈተባት ጦርነትም ኢኮኖሚውን ይበልጥ ጫና ውስጥ ከትቶታል።

    ይሁን እንጂ በዕግድ ላይ ባለው የኢራን ሀብት ጉዳይ ባለበት የሕግ፣ የፋይናንስ እንዲሁም ፖለቲካዊ እንቅፋቶች የተነሳ ገንዘቧን ለማስለቀቅ የተፈረመው ስምምነት ወደ ተግባር ለማውረድ ጊዜ የሚወስድ እና ውስብስብ ሂደት መሆኑ አይቀርም።

    እነዚህ ሀብቶች በትክክል ምንድናቸው? የኢራንስ ምን ያህል በቀላሉ ልታገኘው ትችላለች? ዝርዝሩን እዚህ ያንብቡ እስከ 100 ቢሊዮን ዶላር የሚገመተው የኢራን የታገደ ሀብት የት ነው ያለው?

  14. ኢራን በቀድሞው ጠቅላይ መሪ ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት ወቅት አሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት እንዳይፈጽሙ አስጠነቀቀች

    መኪናዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የካቲት ላይ በተፈጸመው የመጀመሪያ ጥቃት ለተገደሉት የቀድሞው ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ መንግሥታዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት ለማካሄድ እየተዘጋጀች ያለችው ኢራን፤ አሜሪካ እና እስራኤል ማንኛውም ጥቃት እንዳይሰነዝሩ አስጠነቀቀች።

    የቀድሞው ጠቅላይ መሪ የቀብር ሥነ ሥርዓት ከሐሙስ እስከ ቅዳሜ ድረስ በኢራን እና ኢራቅ ውስጥ የተለያዩ ስፍራዎች እንዲካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ነው። በተለያዩ ደረጃዎች ያሉ የበርካታ አገራት ባለሥልጣናትም በሥነ ሥርዓቱ ለመታደም ወደ ቴህራን እንደሚጓዙ አስታውቀዋል።

    ቻይና፣ ፓኪስታን፣ ሕንድ እና ኳታር ባለሥልጣናቶቻቸውን ከሚልኩ አገራት መካከል ተጠቅሰዋል። ጦርነቱን ለመቋጨት አሸማጋይ የሆነችው የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ የአያቶላህ ኻሜኒን ቀብር ለመታደም ወደ ኢራን እንደሚጓዙ መንግሥታቸው ገልጿል።

    ለቀብር ሥነ ሥርዓቱ ወደ ኢራን ለሚመጡ “ሁለት ሺህ” የአፍጋኒስታን ዜጎች ቪዛ እንደተሰጠም ቢቢሲ ፐርሺያ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።

    ይህ ዝግጅት እየተካሄደ ባለበት ወቅት ኻታም አል አንቢያ በመባል የሚታወቀው የኢራን ጦር ሠራዊት ማዕከላዊ ማዘዣ የማስጠንቀቂያ መግለጫ ማውጣቱን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    ዋና አዛዡ አሊ አብዶላህ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በተላለፈ መግለጫቸው፤ “የኢራንን ጠላቶች በተለይም አሜሪካን እና ጽዮናዊውን ሥርዓት (እስራኤል) ከማንኛውም የተሳሳተ ስሌት እንዲቆጠቡ” አስጠንቅቀዋል።

    “አገራችን ላይ ለሚቃጣ ማንኛውም ስጋት እና ጥቃት በጦር ኃይሎቻችን ስለሚሰጠው ከባድ የአጸፋ እርምጃ እንዲያስቡ እናስጠነቅቃለን” ሲሉም አሳስበዋል።

    ረቡዕ ዕለትም የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ፤ በአገሪቱ ሕዝብ ወይም አመራር ላይ ለሚሰነዘር ማንኛውም ስጋት አፋጣኝ እና ጠንካራ ምላሽ እንደሚሰጥ በመግለጽ ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር።

    አራግቺ ይህንን ማስጠንቀቂያ የሰጡት የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ የአሁኑ የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ “ለሞት የታጩ ናቸው” የሚል አስተያየት ከሰጡ በኋላ ነው።

    በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ወቅት ከፍተኛ የደኅንነት እርምጃዎች እንደሚተገበሩ እንዲሁም በበርካታ ከተሞች ጊዜያዊ የአየር ክልል እገዳ እንደሚጣል መገለጹን ሮይተርስ ዘግቧል።

  15. ዜጋዬ ተገድሏል ያለችው ጋና ከደቡብ አፍሪካ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ውስጥ ገባች

    ዶላ እና ጋሻ የያዙ ተቃዋሚ ሰልፈኞች

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ማክሰኞ ዕለት አፍሪካውያን ስደተኞች ደቡብ አፍሪካን ለቅቀው የሚጠይቁ ሰልፈኞች በተለያዩ ከተሞች አደባባይ ወጥተው ነበር

    አንድ ጋናዊ በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ ካለው ፀረ ስደተኞች ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ተገደለ መባሉን ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ተቀስቅሷል።

    የጋና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዜጋው ኬፕ ታውን ውስጥ በመገደሉ ይፋዊ ተቃውሞውን እና ለፖሊስ አቤቱታ ማቅረቡን ገልጿል።

    የደቡብ አፍሪካ የፍትሕ ሚኒስትር ግን “የጋና ባለሥልጣናት መደበኛ ካልሆኑ ስደተኞች ጋር በተያያዘ ባለው ሁኔታ ላይ የሐሰት መረጃዎችን እያስተላለፉ ነው” ሲሉ ተቃውሞ አሰምተዋል።

    የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ በበኩሉ ተገደለ ስለተባለው ጋናዊ መረጃ እንደሌለው፤ ነገር ግን ከወንጀል ጋር በተያያዘ ስለተገደለ ሌላ ጋናዊ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አሳውቋል።

    የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣን የሆኑት ክሌይሰን ሞንዬላ ከፀረ ስደተኞች ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ጋናዊ ተገድሏል መባሉን “የፈጠራ ታሪክ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    ጋና በዜጋዋ ላይ የተፈጸመውን ግድያ በመቃወም ባወጣችው መግለጫ “የማንንም ሕይወት መንጠቅ ተቀባይነት የሌለው ድርጊት በመሆኑ ተጠያቂዎቹ በአፋጣኝ ለፍርድ መቅረብ አለባቸው” ስትል ጠይቃለች።

    "የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት በግድያው ዙሪያ ፈጻሚዎቹ ተይዘው ለፍርድ እንዲቀርቡ የሚደያርግ ሙሉ፣ ግልጽ እና ፈጣን ምርመራ እንዲያደርጉ እንፈልጋለን” ብሏል የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ።

    የጋና አንድ ሬዲዮ ጣቢያ እንደዘገበው የተገደለው ጋናዊ ለ20 ዓመታት ያህል በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የኖረ የልብስ ስፌት ባለሙያ እየነበረ ሲሆን በተቃዋሚዎች በጥይት ተገድሏል። አስከሬኑን ወደ አገሩ ለመውሰድ በጋና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ጥረት እየተደረገ ነው።

    ባለፈው ማክሰኞ ፀረ ስደተኞች ተቃዋሚዎች አፍሪካውያን ስደተኞች ደቡብ አፍሪካን ለቅቀው እንዲወጡ ያስቀመጡት ቀነ ገደብ የነበረ ሲሆን፣ በተለያዩ ከተሞች ውስጥ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል።

    ጋና፣ ማላዊ እና ናይጄሪያ ከቀነ ገደቡ በፊት የተወሰኑ ዜጎቻቸውን ከደቡብ አፍሪካ ካስወጡ አገራት መካከል ናቸው። እስካሁን 25 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ደቡብ አፍሪካን ለቅቀው ወጥተዋል።

  16. ሩሲያ በኪየቭ ላይ በፈፀመችው መጠነ ሰፊ ጥቃት ቢያንስ 18 ሰዎች ተገደሉ

    በጥቃቱ የወደመ ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, t.me/dsns_telegram

    የሩሲያ ኃይሎች በኪየቭ ላይ በፈጸሙት መጠነ ሰፊ የድሮን እና የሚሳዔል ጥቃት ቢያንስ 18 ሰዎች ተገደሉ።

    በጥቃቱ ከተገደሉት በተጨማሪ 90 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።

    የጥቃቱ ሰለባ ከሆኑት መካከል አብዛኞቹ ሕፃናት እንደሆኑ የኪየቭ የጦር አስተዳደር ኃላፊ ታይሙር ቲካቼንኮ ተናግረዋል።

    በርካታ ነዋሪዎችም ተፈናቅለዋል።

    ጥቃቱ ከ11 ሰዓታት በላይ እንደዘለቀ የተነገረ ሲሆን፣ በኪየቭ የሚገኘው የቢቢሲ ቡድን ረቡዕ ምሽት ከባድ ፍንዳታዎችን ሰምቷል።

    የከተማዋ ከንቲባ ቫታሊ ክሊትሽኮ ጥቃቱን በዩክሬን መዲና ላይ የተፈጸመ “እጅግ ከባድ ጥቃት” ያሉት ሲሆን፣ አርብ ዕለት የሀዘን ቀን እንዲሆን አውጀዋል።

    በጥቃት ከተመቱ ሥፍራዎች መካከል የአምቡላንስ ጣቢያ እንደሚገኝበትም ከንቲባው ገልጸዋል።

    ዩክሬን የሰላማዊ ሰዎች መኖሪያን ዒላማ በማድረግ ሩሲያን ከስሳለች።

    ሞስኮ በበኩሏ በሩሲያ የሲቪል መሠረተ ልማት ላይ ለተፈጸመው ጥቃት አፀፋ “የጦር መሣሪያ ማምረቻ ነው” ባለችው ላይ እርምጃ መውሰዷን ገልጻለች።

    የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲመትሪ ፔስኮቭ ሐሙስ ዕለት "ሩሲያ ያስቀመጠችውን ግብ ለማሳካት በኪየቭ መንግሥት ላይ የምታደርገውን ጫና እንደምትጨምር" ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    የዩክሬን አየር ኃይል እንዳለው ሩሲያ በረቡዕ ምሽቱ ጥቃት 74 ሚሳዔሎችን እና 496 ድሮኖችን አስወንጭፋለች።

    ሆኖም አብዛኞቹ በአገሪቷ የአየር ጥቃት መከላከያ መክሸፋቸውን እና 25 ባልስቲክ ሚሳዔሎች እና 12 ድሮኖች ብቻ በ33 ቦታዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን አየር ኃይሉ ገልጿል።

    በጥቃት በወደመ ሥፍራ ላይ ፊት ለፊት ተራርቀው የቆሙ ግለሰቦች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

  17. የኢራን ጠቅላይ መሪ ሚስት ቀብር የባለቤታቸው አስከሬን ባልተገኘበት ተፈጸመ

    የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ሲፈጸም

    የፎቶው ባለመብት, IRNA

    በአሜሪካ እና በእስራኤል ጥቃት ከወራት በፊት የተገደሉት የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ ባለቤት ዛሃራ ሃዳድ የቀብር ሥነ ሥርዓት ባላቸው ባልተገኙበት ረቡዕ ዕለት ቴህራን ውስጥ መፈጸሙ ተዘገበ።

    ዛሃራ ሃዳድ አዴል በመጀመሪያው ዕለት ጥቃት ከተገደሉት የኻሜኒ ቤተሰብ አባላት አንዷ ናቸው። በመጀመሪያው ዕለት የቦምብ ጥቃት የኢራን ጠቅላይ መሪ እና ሌሎች በርካታ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት መገደላቸው ይታወሳል።

    በተጨማሪም የአባታቸውን ሥልጣን የተረከቡት የዛሃራ ባለቤት ሞጅታባ ኻሜኒ በጥቃቱ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው በተደጋጋሚ ቢነገርም እስካሁን በተጨባጭ የተረጋገጠ ነገር የለም።

    የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ መሪ ከሆኑ በኋላ የጽሁፍ መልዕክት ከማስተላለፍ ውጪ በይፋ ለሕዝብ ያልታዩት ሞጅታባ በጥቃቱ በደረሰባቸው ከባድ ጉዳት ምክንያት እንደሆነ ይነገራል።

    በመጀመሪያው ዕለት ጥቃት የተገደሉት የሞጅታባ ሚስት ዛሃራ የሟቹ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ አማካሪ እና በእስላማዊው ሪፐብሊክ ውስጥ ተደማጭ የሆኑት ጎላማሊ ሃዳድ አዴል ልጅ ነበሩ።

    ከጥቂት ቀናት በፊት ጎላማሊ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ከከፈቱ ወዲህ የሟች ሴት ልጃቸው ባለቤት የሆኑትን ሞጅታባ ኻሜኒን አግኝተዋቸው እንደማያውቁ ተናግረዋል።

  18. “የሆርሙዝ ወሽመጥ የኢራን የማያሻማ ሉዓላዊ ግዛት አካል ነው” - የኢራን ጦር

    የኢራን ሰንደቅ ዓላማ እና ባሕር ላይ የሚቀዝፍ የጭነት መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ሆርሙዝ ወሽመጥ የማያሻማ የኢራን ሉዓላዊ የውሃ አካል በመሆኑ ለወራሪዎች ቦታ እንደሌለው ኻታም አል-አንቢያ በመባል የሚታወቀው የኢራን ጦር ሠራዊት ማዕከላዊ ማዘዣ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

    ስለዚህም “ከአሜሪካ በኩል በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚደረግ የትኛውም ዓይነት ጠልቃ ገብነት ከኢራን ጦር ኃይሎች ፈጣን እና የማያዳግም ምላሽ ይሰጠዋል” በማለት አስጠንቅቋል።

    ከማዘዣ ማዕከሉ የወጣውን መግለጫ ጠቅሰው የኢራን መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት “ወሳኝ የውሃ ላይ መተላለፊያ የሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ ደኅንነት እና አስተዳደር ጉዳይ የኃያላኑ የእስላማዊት ኢራን ጦር ኃይሎች የማይታለፍ ቀይ መስመር ነው” በማለት አጽንኦት መስጠቱን አመልክተዋል።

    “ሆርሙዝ ወሽመጥ የወራሪዋ አሜሪካ የምትቆጣጠረው መስክ ሳይሆን፣ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ የማያሻማ ሉዓላዊ ግዛት ነው” ሲል ኢራን በባሕር መተላለፊያው ላይ ያላትን የበላይነት ገልጿል።

    ሁሉም የንግድ መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ደኅንነታቸው ተጠብቆ በሰላም ለማለፍ በኢራን የተቀመጠውን መስመር ብቻ መከተል እንዳለባቸው እና ካልሆነ ግን የሚገጥማቸውን ቅጣት መቀበል እንደሚገባቸው አስጠንቅቋል።

    ኢራን በአሜሪካ እና በእስራኤል ጦርነት ከተከፈተባት በኋላ በወሳኙ የባሕር መስመር በኩል ላይ በሚያልፉ መርከቦች ላይ ጥቃት መሰንዘር በመጀመሯ ሆርሙዝ ዝግ ሆኖ ቆይቷል።

    ሆርሙዝ ከዓለም ፍጆታ ከ20 በመቶ በላይ የሚሆነው ነዳጅ እና ጋዝ ከፋርስ ባሕረ ሰላጤው አገራት በመነሳት የሚተላለፍበት ወሳኝ የባሕር መስመር ነው። በጦርነቱ ወቅት መርከቦች ማለፍ ባለመቻላቸው በዓለም ዙሪያ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቶ ነበር።

  19. አሜሪካ ጦሯን ከሳዑዲ አረቢያ ለማስወጣት እያሰበች እንደሆነ ተዘገበ

    ትራምፕ እና መሐመድ ቢን ሰልማን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አሜሪካ በሳዑዲ አረቢያ የሚገኝ ጦሯን ለመቀነስ ወይም የተወሰነውን ወታደራዊ ኃይል ከሳዑዲ አስወጥታ ወደ ሌላ ቦታ ለማዘዋወር እያሰበች እንደሆነ ዋል ስትሪት ጆርናል የተመለከተውን ሪፖርት ጠቅሶ ዘገበ።

    አሜሪካ ይሄንን እርምጃ ለመውሰድ እያሰበች ያለው በዋሽንግተን እና በሪያድ መካከል ያለውን ውጥረት ተከትሎ ነው ተብሏል።

    ሁለቱ አገራት በኢራን ጦርነት እንዲሁም በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን ደኅንነት ከማስጠበቅ ጋር በተያያዘ ውጥረታቸው ተባብሷል።

    ዋል ስትሪት ጆርናል የተመለከተው ሪፖርት እንደሚጠቁመው፤ ከ100 በላይ የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላኖች የሆርሙዝ ወሽመጥ ክፍት ሆኖ እንዲቀጥል ለማስቻል በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚገኙ የጦር ሰፈሮች እና ከወታደራዊ መርከቦች በመነሳት በረራ አድርገዋል።

    ይህ ስምሪት ከሳዑዲ አረቢያ ያልተጠበቀ መሰናክል እንደገጠመው ዘገባው ያትታል።

    በሳዑዲ የሚገኙ የጦር ሰፈሮች እና የአገሪቱ የአየር ክልል ለዚህ ስምሪት ከፍተኛ ድርሻ ያለው ቢሆንም ሪያድ ከዋሽንግተን ጋር ለመተባበር አልፈቀደችም።

    ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የአሜሪካ ባለሥልጣን ለዋል ስትሪት ጆርናል እንደገለጹት፤ የሳዑዲ ተቃውሞ አሜሪካ ‘ኦፕሬሽን ፕሮጀክት ፍሪደም’ የተባለውን ስምሪት እንድታቋርጥ አስገድዷታል።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይፋ ያደረጉት ኦፕሬሽን መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲተላለፉ ለማስቻል ያለመ ነበር።

    አሜሪካ ኦፕሬሽኑን ያቋረጠችው በግማሽ ልብ ሆና ነው ተብሏል።

    አሜሪካ በሳዑዲ ያላትን ጦር ለመቀነስ አልያም የተወሰነ ወታደራዊ ኃይሏን ከሳዑዲ አስወጥታ ወደ እስራኤል ወይም ዮርዳኖች ለማዘዋወቅ ማሰቧን የዋል ስትሪት ዘገባ ይገልጻል።

    በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ እንዳልተደረሰም ዘገባው ያትታል።

    አሜሪካ ወታደሮቿን ለማስወጣት ከመወሰኗ በፊት አማራጮችን እንደምትመለከትም ተገልጿል።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናት ስለ ጉዳዩ ማረጋገጫም ማስተባበያም አልሰጡም።

  20. ሆርሙዝ በአሜሪካ ሳይሆን በኢራን ቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ መታወቅ አለበት - ኢራን

    መርከብ በሆርሙዝ ላይ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የሆርሙዝ ወሽመጥ በአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ ሳይሆን በኢራን ቁጥጥር ሥር ነው ሲሉ የአገሪቱ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዜም ጋሪባባዲ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ገለጹ።

    የአሜሪካ ጦር ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ በኢራን ላይ የሚካሄደውን ወታደራዊ ዘመቻ የሚመራ ሲሆን፣ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ላይ ያለውን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠር እና በኢራን ላይ እስካሁን የተፈጸሙ ጥቃቶችን የሚያስተባብር አካል ነው።

    ‘ሴንትኮም’ የተባለው ይህ ወታደራዊ ዕዝ በወሳኙ የባሕር መተላለፊያ ወሽመጥ ላይ ዋነኛ ኃይል ነው። ነገር ግን የኢራን ጦር በአካባቢው ባለው ሉዓላዊነት የተነሳ በቀጣናው መርከቦች እንዳይንቀሳቀሱ ለማገድ ችሎ ቆይቷል።

    በዚህም የተነሳ ኢራን በመተላለፊው ላይ ያላትን ቁጥጥር ለማጥበቅ ሕግ እስከማውጣት ደርሳለች። ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩም ከአሜሪካ ጋር እየተካሄደ ያለው ንግግር ኢራን በሆርሙዝ ላይ ያላትን የበላይነት አሳልፎ የሚሰጥ አለመሆኑን አስረግጠው ገልጸዋል።

    ጋሪባባዲ ጨምረውም "ባህሬን ውስጥ የሚካሄደው ወታደራዊ ውይይት የባሕረ ሰላጤውን ደኅንነት የተመለከተ ሕጋዊ አሠራርን የሚፈጥር አይደለም። ከዚያ ይልቅ የቀጣናው ደኅንነት የሚረጋገጠው የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ሲያበቃ እና ከአካባቢው ስትወጣ፣ የአገራት ሉዓላዊነት ሲከበር እንዲሁም ከአሜሪካ የበላይነት ውጪ አዲሱን ጂኦፖለቲካዊ እውነታን በመቀበል ነው” ብለዋል።

    ባለፉት ወራት ተዘግቶ ቆይቶ ከሳምንት በፊት የተከፈተው ሆርሙዝ ወሽመጥ አሁንም ደኅንነቱ የተጠበቀ ባለመሆኑ ማኅበራት እና የመርከብ ኩባንያዎች መተላለፊያው “የጦርነት ቀጣና” ሆኖ መታየቱ እንደሚቀጥል አሳውቀዋል።

    ሆርሙዝ መጀመሪያ ላይ በዚህ ምደባ ውስጥ የተካተተው አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ ከቀናት በኋላ በመርከቦች ላይ ጥቃት መድረሱን ተከትሎ ነበር። አሁንም በመርከቦች ላይ አልፎ አልፎ ጥቃቶች እየተፈጸሙ በመሆናቸው ነው ስጋቱ የተፈጠረው።