አሜሪካ እና ኢራን ግጭቱን “ለመግታት” መስማማታቸው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሜሪካ እና ኢራን ባለፉት ጥቂት ቀናት የገቡበትን ግጭት “ለመግታት” መስማማታቸው ተዘገበ።
የዋሽንግተንን ባለሥልጣን ጠቅሰው የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ሁለቱ አገራት የተኩስ ልውውጡን ለማቆም ተስማምተዋል።
በሆርሙዝ ወሽመጥ እና በዙሪያው ሁለቱ አገራት የተኩስ ልውውጥ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
አሜሪካ እና ኢራን የተኩስ አቁም ስምምነትን በመጣስ አንዳቸው ሌላቸውን ሲከሱም ነበር።
የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ያነጋገራቸው ባለሥልጣን እንዳሉት አሁን ላይ መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል “በነጻነት” ማለፍ ይችላሉ።
አገራቱ ጦርነቱን ለመግታት የሚያደርጉትን ውይይት እንደሚቀጥሉም ገልጿል።
ኢራን ጥቃት ለማቆም መስማማቷን በሚገልጸው ዘገባው ላይ እስካሁን አስተያየት አልሰጠችም።
ኢራን እና አሜሪካ የፈረሙት የመግባቢያ ሰነድ “በሁሉም ግንባሮች ወታደራዊ ግጭት” እንደሚቆም ይገልጻል።
ኢራን በስምምነቱ መሠረት በ60 ቀናት ውስጥ በሆርሙዝ ወሽመጥ የንግድ መርከቦች ከክፍያ ነጻ እንዲያልፉ ትፈቅዳለች።
ባለፉት ቀናት ሁለቱ አገራት የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸው የመግባቢያ ሰነዱን አደጋ ውስጥ ከትቶታል።

