ቀጥታ, አሜሪካ እና ኢራን ግጭቱን “ለመግታት” መስማማታቸው ተገለጸ

አሜሪካ እና ኢራን ባለፉት ጥቂት ቀናት የገቡበትን ግጭት “ለመግታት” መስማማታቸው ተዘገበ። የዋሽንግተንን ባለሥልጣን ጠቅሰው የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት፤ ሁለቱ አገራት የተኩስ ልውውጡን ለማቆም ተስማምተዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ የፖሊስ አዛዥ ከግድያ ሙከራ አመለጡ

    ሜጀር ጀነራል ፌሮዝ ካሀን

    የፎቶው ባለመብት, Gallo via Getty Images

    ከደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ የፖሊስ አዛዦች አንዱ የሆኑት ሜጀር ጀነራል ፌሮዝ ካሀን ከግድያ ሙከራ ማምለጣቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

    የወንጀል ምርመራ ክፍል ምክትል ኃላፊ የሆኑት ሜጀር ጀነራል ፌሮዝ ትናንት እሑድ ምሽት ወደ ቤታቸው እየነዱ ሳለ ጥይት እንደተተኮሰባቸው ተገልጿል። ወደ ድንገተኛ የሕክምና ክፍል መወሰዳቸውም ተዘግቧል።

    በደቡብ አፍሪካ በፖሊስ ኃይል የሚፈጸም ወንጀልን በተመለከተ ምርመራ የሚያካሂድ ኮሚቴ የተዋቀረ ሲሆን፤ ከፍተኛ የፖሊስ አዛዡ ከቀናት በኋላ ለኮሚቴው ቃላቸውን እንደሚሰጡ ይጠበቅ ነበር።

    የደቡብ አፍሪካ የፖሊስ ቃል አቀባይ ብርጋዲየር አትሌንዳ ሜት ክስተቱ ላይ ምርመራ መከፈቱን አስታውቀዋል።

    “ክስተቱ፤ መርማሪ ኮሚቴው ፊት ሊቀርቡ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው ማለት ወቅቱን ያልጠበቀ እና ኃላፊነት የጎደለው ነው” ብለዋል።

    የምርመራ ኮሚቴው የተዋቀረው ከፍተኛ የፖሊስ አዛዥ ሌተናንት ጀነራል ናለናሀል ምክዌንዚ የወንጀል ቡድኖች በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሰርገው ገብተዋል ብለው በመክሰሳቸው ነበር።

  2. ኢራን እና አሜሪካ በቴክኒክ ጉዳዮች ውይይት እንደሚቀጥሉ ተዘገበ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ኢራን እና አሜሪካ የተኩስ ልውውጡን ለመግታት መስማማታቸውን ተከትሎ የመግባቢያ ሰነዱ ላይ ያሉ የቴክኒክ ጉዳዮችን በተመለከተ ውይይት እንደሚቀጥሉ የዋሽንግተን ባለሥልጣን ገለጹ።

    ኤኤፍፒ ያነጋገራቸው የአሜሪካ ባለሥልጣን “በስምምነቱ ያሉ ሁሉም የቴክኒክ ጉዳዮችን በተመለከተ ውይይቶች ይቀጥላሉ። ለአሁኑ ሁለቱም ወገኖች ግጭቱን ከማባባስ ይቆጠባሉ። መርከቦችም በነጻነት መጓዝ ይችላሉ” ብለዋል።

    የኢራን ባለሥልጣናት እስካሁን ድረስ ጉዳዩን በተመለከተ አስተያየት አልሰጡም።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደርን በተመለከተ ውዝግቦች የተነሱ ሲሆን፤ ቴህራን እና ዋሽንግተን ባለፉት ቀናት ግጭት ውስጥ ገብተዋል።

    አሁን ላይ ግጭቱን ለመግታት መስማማታቸው ተገልጿል።

  3. ፓኪስታን በአፍጋኒስታን ላይ ባደረሰችው ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

    የፓኪስታን  እና አፍጋኒስታን ድንበር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ፓኪስታን በአፍጋኒስታን ላይ የአየር ጥቃት ካደረሰች በኋላ እግረኛ ጦሯን ማሰማራቷ ተገለጸ።

    የአፍጋኒስታን ባለሥልጣናት እንደተናገሩት በምዕራብ ድንበር በተፈጸመው ጥቃት ብዙ ንጹኃን ዜጎች ተገድለዋል።

    የታሊባን መንግሥት ጥቃቱን “የፈሪነት ድርጊት” እንዲሁም “ጭፍጨፋ እና ወንጀል” ሲል አውግዟል። ቢያንስ 100 ሰዎች እንደተጎዱ ወይም እንደተገደሉም አስታውቋል።

    የፓኪስታን የመረጃ ሚኒስትር አቱላህ ታራር እንዳሉት ምሽጎች ላይ ባነጣጠረው ጥቃት 29 ወታደሮች ተገድለዋል።

    “በቅርቡ በንጹኃን ላይ ለተፈጸመ የሽብር ጥቃት የአጸፋ ምላሽ ነው” ብለዋል።

    ታሊባን እንዳለው ፓኪስታን ጥቃት የፈጸመችው የንጹኃን መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ነው። ፓኪስታን ግን ዒላማ ያደረገችው የወታደሮችን ምሽግ መሆኑን በመግለጽ አስተባብላለች።

    ፓኪስታን ሽብርተኞችን በመደበቅ አፍጋኒስታንን ስትከስ ቆይታለች። የታሊባን መንግሥት ግን ክሱን አስተባብሏል።

  4. አሜሪካ እና ኢራን ግጭቱን “ለመግታት” መስማማታቸው ተገለጸ

    በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፍ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አሜሪካ እና ኢራን ባለፉት ጥቂት ቀናት የገቡበትን ግጭት “ለመግታት” መስማማታቸው ተዘገበ።

    የዋሽንግተንን ባለሥልጣን ጠቅሰው የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ሁለቱ አገራት የተኩስ ልውውጡን ለማቆም ተስማምተዋል።

    በሆርሙዝ ወሽመጥ እና በዙሪያው ሁለቱ አገራት የተኩስ ልውውጥ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን የተኩስ አቁም ስምምነትን በመጣስ አንዳቸው ሌላቸውን ሲከሱም ነበር።

    የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ያነጋገራቸው ባለሥልጣን እንዳሉት አሁን ላይ መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል “በነጻነት” ማለፍ ይችላሉ።

    አገራቱ ጦርነቱን ለመግታት የሚያደርጉትን ውይይት እንደሚቀጥሉም ገልጿል።

    ኢራን ጥቃት ለማቆም መስማማቷን በሚገልጸው ዘገባው ላይ እስካሁን አስተያየት አልሰጠችም።

    ኢራን እና አሜሪካ የፈረሙት የመግባቢያ ሰነድ “በሁሉም ግንባሮች ወታደራዊ ግጭት” እንደሚቆም ይገልጻል።

    ኢራን በስምምነቱ መሠረት በ60 ቀናት ውስጥ በሆርሙዝ ወሽመጥ የንግድ መርከቦች ከክፍያ ነጻ እንዲያልፉ ትፈቅዳለች።

    ባለፉት ቀናት ሁለቱ አገራት የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸው የመግባቢያ ሰነዱን አደጋ ውስጥ ከትቶታል።

  5. ኢራን ስምምነቱ ከተጣሰ “ከፍተኛ እርምጃ” እንደምትወስድ አስታወቀች

    አባስ አራግቺ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ “ስምምነቱን በጣሰው በዛኛው ወገን ላይ ከፍተኛ እርምጃ እንወስዳለን” ሲሉ አስጠነቀቁ።

    ከኢራቅ ፕሬዝዳንት ናዚር አሚዲ ጋር የተወያዩት አራግቺ “በአሜሪካ እና በጽዮናዊው አስተዳደር አንዳንድ መግባቢያዎች መጣሳቸው ሰላም እና መረጋጋት በቀጣናው እንዳይሰፍን ከፍተኛ መሰናክል ይሆናል” ብለዋል።

    የስምምነቱ “በተለይ የመጀመሪያው አንቀጽ” መጣስ ሰላም እና መረጋጋትን እንደሚያውክ ገልጸዋል።

    “የመግባቢያ ሰነዱን በጥሩ መንፈስ እና ለስምምነቱ ታማኝ በመሆን መተግበር እንፈልጋለን” ብለዋል።

    ሆኖም ግን ስምምነቱ “በዚያኛው ወገን ከተጣሰ ከፍተኛ እርምጃ እንወስዳለን” በማለት አስጠንቅቀዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደር ውስጥ ማንኛውም ጣልቃ ገብነት ውጥረቱን እንደሚያባብስ መናገራቸውም ይታወሳል።

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል እያለፈ የነበረ በፓናማ የተመዘገበ መርከብ ትናንት ቅዳሜ ጥቃት ከደረሰበት በኋላ አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት ፈጽማለች።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በአጸፋ ምላሽ በኩዌት እና ባሕሬን በሚገኙ የአሜሪካ መሠረተ ልማቶች ላይ የድሮን እና ሚሳዔል ጥቃቶች ማድረሱን ገልጿል።

    ኩዌት እና ባሕሬን በኢራን የደረሰባቸውን ጥቃት አውግዘዋል።