የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ትራምፕ ግሪንላንድን በተመለከተ "ማስፈራራታቸውን" እንዲያቆሙ ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግሪንላንድን ስለመቆጣጠር "የሚሰነዝሩትን ዛቻ እንዲያቆሙ" ጠየቁ።
ሜቴ ፍሬድሪክሰን “ዩናይትድ ስቴትስ ግሪንላንድን ለመጠቅለል ስላላት ፍላጎቷ ማውራቷ ፈጽሞ ትርጉም የለውም” ሲሉ ተናግረዋል። “አሜሪካ በዴንማርክ መንግሥት ውስጥ ካሉት ሦስት ግዛቶች አንዱን የመገንጠል መብት የላትም” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ይህንን አስተያየት የሰጡት ከትራምፕ ረዳቶች አንዱ የሆኑት የስቴፈን ሚለር ባለቤት ኬቲ ሚለር በግሪንላንድ ካርታ ላይ የአሜሪካን ባንዲራ ያስቀመጠ እና "በቅርቡ" የሚል ጽሁፍን የያዘ ልጥፍ በትዊተር ገጻቸው ላይ ካጋሩ በኋላ ነው።
ትራምፕ ግሪንላንድ ያላትን ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ እና የማዕድን ሀብቷን በመጥቀስ ከአሜሪካ ጋር ልትቀላቀል እንደምትችል በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ፍሬደሪክሰን አስተያየት ከሰጡ በኋላ ደግሞ ትራምፕ ግዛቲቱ ለአሜሪካ ትገባለች የሚለውን ንግግራቸውን አጠንክረው ቀጥለዋል።
ፍሬደሪክሰን በዴንማርክ መንግሥት ድረ ገጽ ላይ ባሰፈሩት መግለጫ ለአሜሪካ “በቀጥታ” መልዕክት እያስተላለፉ እንደሆነ ተናግረዋል።
“አሜሪካ ታሪካዊ የቅርብ አጋሯ በሆነች አገር ላይ እንዲሁም ሌላ አገር እና ሌላ ሕዝብ በግልጽ ለሽያጭ አይቀርብም እያለ ባለበት ማስፈራራቷን እንድታቆም አበክሬ እጠይቃለሁ።”
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ይህንን ካሉ ከሰዓታት በኋላ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በኤርፎርስ ዋን ላይ ሆነው “ግሪንላንድን የምንፈልገው ከብሔራዊ ደህንነት አንጻር ነው። ዴንማርክ ደግሞ ያንን ማድረግ አትችልም” ብለዋል።
ከዚህ አስቀድሞ በአሜሪካ የዴንማርክ አምባሳደር ሁለቱ አገራት የቅርብ አጋር መሆናቸውን “ማስታወስ እፈልጋለሁ” ካሉ በኋላ አሜሪካ የዴንማርክን የግዛት አንድነት አንድታከብር ጠይቀዋል።
በሁለቱ አገራት መሪዎች መካከል ይህ የቃላት ምልልስ የተሰማው አሜሪካ ቅዳሜ ዕለት በቬንዚዌላ ወታደራዊ ዘመቻ ካካሄደች እና ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ እና ባለቤታቸውን በቁጥጥር ሥር ካዋለች በኋላ ነው።
ትራምፕ በኋላ ላይ አሜሪካ ቬንዙዌላን "እንደምትመራ" እና የአሜሪካ የነዳጅ ኩባንያዎች "ለአገሪቱ ገንዘብ ማስገኘት እንደሚጀምሩ" ተናግረዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ቀደም ሲል በአርክቲክ ውስጥ የምትገኘውን ግዙፍ ደሴት፣ ግሪንላንድን ለመቆጣጠር ኃይል መጠቀምን እንደ አማራጭ እንደማይቀርብ በግልጽ አልተናገሩም ነበር።
የትራምፕ አስተዳደር በቅርቡ ለግሪንላንድ ልዩ መልዕክተኛ የሾመ ሲሆን ይህም ዴንማርክን አስቆጥቷል።
57 ሺህ ሕዝ ያላት ግሪንላንድ እአአ ከ1979 ጀምሮ ራሷን በራሷ ታስተዳድራለች።
የውጭ ጉዳይ እና መከላከያን በሚመለከት ግን ሙሉ ኃላፊነት ያለበት የዴንማርክ መንግሥት ነው።

