የቬንዜዌላ መንግሥት የፖለቲካ እስረኞችን መልቀቅ ጀመረ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የቬንዙዌላ መንግሥት በሰብዓዊ መብት ቡድኖች የፖለቲካ እስረኞች ናቸው የተባሉ ሰዎችን መፍታት ጀመረ።
የስፔን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አምስት ዜጎቻቸው እንዲሁም አንድ ጥምር ዜግነት ያለውን ግለሰብን ጨምሮ ከእስር መለቀቃቸውን አስታውቋል።
ከእነዚህም መካከል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑት ሮሲዮ ሳን ሚጌል እንደሚገኙበት ይገመታል።
ይህ እርምጃ የተወሰደው አሜሪካ ቅዳሜ ዕለት በዋና ከተማዋ ካራካስ ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመፈጸም የአገሪቱን ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን እና ባለቤታቸውን በቁጥጥር ሥር ካዋለች በኋላ ነው።
ኒኮላስ ማዱሮ ወደ አሜሪካ ተወስደው በኒውዮርክ የአደንዛዥ ዕፅ እና የጦር መሳሪያ ዝውውር ክስ ተመሥርቶባቸዋል።
አሜሪካ በቬንዙዌላ በተለያዩ እስር ቤቶች የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች እንዲለቀቁ በተደጋጋሚ ስትጠይቅ ነበር።
የቬንዙዌላ ብሔራዊ ምክር ቤት ኃላፊ እና የቬንዙዌላ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ዴልሲ ሮድሪጌዝ ወንድም የሆኑት ጆርጅ ሮድሪጌዝ በመንግሥት ቴሌቪዥን ቀርበው "ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው" እስረኞች እንደሚፈቱ የተናገሩ ቢሆንም፤ ምን ያህል እና እነማን እንደሆኑ ሳይገልጹ ቀርተዋል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች በቬንዙዌላ እስር ቤቶች ውስጥ ይገኛሉ፤ እስካሁን የተፈቱት ጥቂቶች ብቻ ናቸው።
ጆርጅ ሮድሪጌዝ ጊዜያዊው መንግሥት የፖለቲካ እስረኞቹን "ለብሔራዊ አንድነት እና በሰላም አብሮ ለመኖር" በሚል እንደሚለቅቃቸው አስታውቀዋል።
በደኅንነት፣ በመከላከያ እና በቬንዙዌላ ወታደራዊ ዘርፍ ባለሙያ የሆኑት ሳን ሚጌል መፈታታቸው የተረጋገጠ የመጀመሪያው እስረኛ ናቸው።
ግለሰቧ በአውሮፓውያኑ የካቲት 2024 በካራካስ አቅራቢያ በሚገኘው በማይኬቲያ አየር ማረፊያ ተይዘው መታሰራቸው ይታወሰል።
ማዱሮን በመተቸት የሚታወቁት ሳን ሚጌል ፕሬዚዳንቱን ለመግደል በተቀናበረ ሴራ ውስጥ ተሳትፈዋል በሚል እና በአገር ክህደት፣ በማሴር እና በሽብርተኝነት ክስ ተመሥርቶባቸው ነበር።
አንዳንድ አባላቶቹ እና መሥራቾቹ በእስር ላይ የሚገኙት የቬንዙዌላ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች በእስረኞቹ መፈታት ዜና የተሰማውን ደስታ ገልጿል።





















