የአሜሪካ መንግሥት በቬንዙዌላ ነዳጅ ላይ ከኩባንያዎች ጋር ንግግር ጀመረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን በቬንዙዌላ የነዳጅ ጉዳይ ላይ ከአሜሪካ ኩባንያዎች ጋር ንግግር እየተካሄደ መሆኑን ለቱርክ የዜና ወኪል፣ አናዶሉ ተናገሩ።
የአሜሪካ መንግሥትን በመወከል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ እና የኤነርጂ ሚኒስትሩ ክሪስ ራይት ውይይቱን እየመሩት መሆናቸውን የገለጹት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱት ባለሥልጣን፤ ነገር ግን የትኞቹ ኩባንያዎች ተሳተፊ እንደሆኑ ከመናገር ተቆጥበዋል።
“ፕሬዝዳንት ትራምፕ በቬንዙዌላ ውስጥ ስላሉት አዳዲስ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ከአሜሪካ የነዳጅ ኩባንያዎች ጋር ለመነጋገር እንደሚፈልጉ ገልጸዋል" በማለት የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ካሮላይን ሌቪት ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል።
የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሽግግር እስኪካሄድ ድረስ አሜሪካ አገሪቱን እንደምትመራ እና የነዳጅ ተቋማቷን በመጠገን ሥራቸውን እንደሚያስቀጥሉ ገልጸዋል።
“በዓለም ላይ የትም ቦታ ላይ የሌሉ የአሜሪካ ግዙፍ ነዳጅ አምራች ኩባንያዎች ወደ ቬጀንዙዌላ ገብተው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በማውጣት በከፍተኛ ደረጃ የተበላሹትን የአገሪቱን የነዳጅ መሠረተ ልማቶች ይጠግናሉ” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።




















