ኢራን ከአሜሪካ ጋር ወደፊት ስለሚኖራት ንግግር ከፓኪስታን ጋር ከተወያየች በኋላ እንደምትወስን ተዘገበ

የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock
ከኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያለው ታስኒም የዜና ወኪል ቴህራን ከአሜሪካ ጋር የሚኖራትን ቀጣይ ድርድር ከፓኪስታን ልዑክ ጋር ከተወያየች በኋላ እንደምትወሰን ዘገበ።
የዜና ኤጀንሲው “ስለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮችን” ጠቅሶ በቀጣዮ ዙር ውይይት ላይ ለመወሰን አሜሪካ እና እስራኤል ከሊባኖስ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ከደረሱ “ለኢራን እንደ በጎ ምልክት” መሆኑን ተናግሯል።
ይሁን እንጂ አሜሪካ "ምክንያታዊ የሆነ የድርድር ማዕቀፍን መከተል አለባት" ያሉት የዜና ኤጀንሲው ምንጮች "ከመጠን በላይ የተለጠጡ ፍላጎቶችን በማቅረብ ሂደቱን ማደናቀፍ" ወይም ከተኩስ አቁም በፊት የተደረጉትን ስምምነቶችን መጣስ እንደሌለባት ጨምረው ተናግረዋል።
ታስኒም ዋሺንግተን ቀጣዩን ዙር ውይይት ለማካሄድ ፈቃደኛ መሆኗን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን መዘገባቸውን ጠቅሶ፣ ነገር ግን የኢራን የልዑካን ቡድኑ ዩኤስ "ምክንያታዊ ድርድርን ለመጀመር የሚያስፈልጉትን የተወሰኑ መርሆዎችን ማክበር" እንደሚያስፈልጋት አፅንዖት ሰጥተዋል ብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ ከኢራን ጋር ስለ ሁለተኛ ዙር ድርድር እየተነጋገረች መሆኑን ቢቢሲ ማረጋገጥ ችሏል። ነገር ግን እስካሁን ድረስ ቀኑም ሆነ ቦታው አለመወሰኑ ተገልጿል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ኢራን ከስምምነት ለመድረስ ቁርጠኛ መሆኗን እስኪያረጋግጡ ድረስ የባሕር ኃይሉ የቴህራንን ወደቦችን ዘግቶ እንዲቆይ እንደሚፈልጉ ቢቢሲ መረዳት ችሏል።



















