የአሜሪካ ልዑካን ለድርድር ወደ ፓኪስታን ተመለሱ፤ ትራምፕ የኢራንን መሠረተ ልማት እንደሚያወድሙ ዝተዋል

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ልዑክ ከኢራን ጋር ለሚደረገው ሁለተኛ ዙር ድርድር ወደ ፓኪስታን ማቅናቱን ገለጹ። በአሁኑ ድርድር አሜሪካ የምታቀርበውን ስምምነት ኢራን የማትቀበል ከሆነ በአገሪቱ የሚገኙ “የኃይል ማመንጫዎች እና ድልድዮችን እንደሚመቱ” ዝተዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በኢራን እና ሊባኖስ የተደረሱት የተኩስ አቁም ስምምነቶች የያዙት ተስፋ እና አደጋ

    በሊባኖስ የተደረሰውን የተኩስ አቁም ተከትሎ ወደ መኖሪያ ቀያቸው የሚመለሱ ሊባኖሳውያን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ሐሙስ ምሽት በእስራኤል እና በኢራን በሚደገፈው ሄዝቦላህ መካከል የሚደረገው ጦርነት ለአስር ቀናት እንዲቆም መደረጉ ለኢራን ድል ነው።

    በቴህራን ያለው አገዛዝ በሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጠይቆ ነበር፤ ያለበለዚያ ከአሜሪካ ጋር የሚደረገው ውይይት ሊቀጥል፤ ሊሰምርም አይችልም ሲል ተደምጧል።

    ኢራን አሁን የተኩስ አቁሙን ተከትሎ የሆርሙዝ ወሽመጥ "ሙሉ በሙሉ ክፍት" መሆኑን በመግለጽ ምላሽ ሰጥታለች።

    ባለፈው ቅዳሜና እሁድ በኢዝላማባድ የተደረገው ረዥም ድርድር እንደሚያሳየው፣ በሊባኖስ የነበረው ጦርነት እየቀጠለ ቢሆንም ከመግባባት ላይ ለመድረስ ዕድል መኖሩን አመላክቷል።

    ነገር ግን ኢራን እና ፓኪስታን በተኩስ አቁም ላይ ሊባኖስ መካተት እንዳለባት አጥብቀው ተሟግተዋል።

    በእስራኤል ላሉ አንዳንዶች አሁንም ኢራን ጨዋታው ሜዳ ላይ የበላይ ሆና ወጥታለች። ዛሬም የእስራኤል የረዥም ጊዜ ጠላት ሁኔታዎችን የምትዘውር እና የቀጣናውን ፖለቲካ የምትወስን ሆናለች።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ለአሜሪካው ወዳጃቸው ፍላጎቶች እጃቸውን ሰተዋል ብለው የተቆጡም አልጠፉም።

    በእነዚህ አንዳቸው ከሌላኛቸው ጋር በተጋመዱ ግጭቶች ውስጥ የተሳተፉ ሁሉም ተፋላሚዎች ከቅርብ ጊዜው ስምምነት የየድርሻቸውን ማግኘታቸውን አይቀርም።

    ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና በኢራን ላለው አመራር፣ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ በማድረጋቸው ዕውቅና ይቸራቸዋል።

    ኔታንያሁ በበኩላቸው የእስራኤል ወታደሮች በደቡባዊ ሊባኖስ እንደሚቆዩ ሊያስረዱ ይችላሉ።

    ለሊባኖስ መንግሥት ደግሞ ከወራት ሙከራ እና ጥረት በኋላ ከእስራኤል ጋር ቀጥተኛ ድርድር የማድረግ ዕድል አግኝቷል።

    ሄዝቦላህ ደግሞ ምንም እንኳ አሁንም "ጣቴ በቃታው ላይ" ቢሆንም የተኩስ አቁሙን አከብራለሁ ብሏል።

    ነገር ግን ትጥቅ እንደማይፈታ አጥብቆ ይናገራል።

  2. መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ እያለፉ መሆኑን የመርከቦች መረጃ አመለከተ

    በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚተላለፉ መርከቦችን የሚያሳይ መረጃ

    የፎቶው ባለመብት, MarineTraffic

    የምስሉ መግለጫ, መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ እያለፉ ነው

    መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ማሪን ትራፊክ የተሰኘ ገፅ መረጃ ያሳያል።

    እንደ ድረ ገፁ ገለጻ በርካታ ነዳጅ፣ ፈሳሽ ጋዝ እና ኬሚካሎችን የጫኑ መርከቦች በወሽመጡ ሲንቀሳቀሱ የሚታዩ ሲሆን፤ መርከቦቹ ወደ ዋናው የባሕር ኮሪደር ሲያቋርጡ ይታያሉ።

  3. ስለ ሆርሙዝ ወሽመጥ ማን ምን አለ?

    በኦማን የባሕር ዳርቻ ላእ ኣለች መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ትራምፕ - የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በመካከለኛው ምሥራቅ ከኢራን ጋር “በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ያለ ይመስላል” ሲሉ ተናግረዋል። በሳምንቱ መጨረሻ ድርድር እንደሚካሄድ እና አሁን መናገር የማይችሉት “አንድ ጥሩ ዜና” መኖሩንም ተናግረዋል። ትራምፕ በትናንትናው እለት በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ የአሜሪካ የባሕር ኃይል "ከኢራን ጋር ያለው ስምምነት መቶ ፐርሰንት እስኪጠናቀቅ" ድረስ ወደቦቿን ዘግቶ ይቆያል ብለዋል።

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ - ሞሃመድ ባገር ጋሊባፍ ዩናይትድ ስቴትስ ከኢራን ጋር ባደረገችው ጦርነት ማሸነፏን አስመልክቶ ዶናልድ ትራምፕ የሰጡት አስተያየት “ሐሰት” ነው ብለዋል። አክለውም አሜሪካ እገዳውን ከቀጠለች የሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ " ክፍት ሆኖ አይቆይም "ብለዋል።

    የአውሮፓ መሪዎች - የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ማክሮን እና የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር ትናንት በፓሪስ ወደ 40 ከሚጠጉ አገራት ባካሄዱት ስብሰባ የባህር ወሽመጡን በመክፈት ላይ ተነጋግረዋል። ስታርመር እንዳሉት ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሣይ በባሕሩ ላይ የሚደረግ የመርከብ ትራንስፖርት ነፃነትን ለመጠበቅ “ሁኔታዎች ሲፈቅዱ ሰላማዊ እና መከላከል ላይ ብቻ ያተኮረ” ዓለም አቀፍ ተልእኮ እንደሚመሩ ተናግረዋል።

    የቻይናው ፕሬዝዳንት - ትራምፕ የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ "የሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ በመከፈቱ እና/ወይም በፍጥነት በመከፈቱ በጣም ደስተኛ ናቸው" ብለዋል። የዩኤስ ፕሬዝዳንት በቻይና ከግንቦት 14-15 በቻይና በሚያደርጉት ጉብኝት ወቅት ከዢ ጂንፒንግ ጋር የሚያደርጉት ውይይት “ልዩ እና ምናልባትም ታሪካዊ ይሆናል” ብለዋል።

  4. የእስራኤል ጦር በኢራን ላይ ወደ 11,000 የሚጠጉ ጥቃቶችን መፈጸሙን አስታወቀ

    በእስራኤል ትቃት የወደሙ አካባቢዎች

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የእስራኤል የመከላከያ ሠራዊት በኢራን ላይ ከፈጸመው የቦምብ ድብደባ ጋር የተያያዙ አዳዲስ አሃዞችን ይፋ አድርጓል።

    በዚህም ለስድስት ሳምንት በተካሄደው ጦርነት ወቅት በአገሪቱ ላይ ወደ 10,800 የሚጠጉ ጥቃቶችን መፈጸሙን አስታውቋል።

    መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የዜና ኤጀንሲ (ሂራና) የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት መደረሱን እስካወጁበት ሚያዝያ 7 ድረስ 1,701 ሰላማዊ ኢራናውያን መገደላቸውን ዘግቧል።

    የመከላከያ ሠራዊቱ በሊባኖስ ከ14,900 በላይ የመድፍ ድብደባዎችን እና 2,500 የአየር ድብደባዎችን መፈጸሙን ይፋ አደርጓል።

    አክሎም በግምት 165 ባለ ብዙ ሕንጻዎችን መምታቱን አስታውቋል።

    የሊባኖስ የጤና ባለሥልጣናት በሊባኖስ ለስድስት ሳምንታት በዘለቀው የአየር ጥቃት 2,100 ሰዎች መሞታቸውን እና ከአንድ ሚሊዮን በላይ መፈናቀላቸውን ተናግረዋል።

  5. ትራምፕ፣ የቻይናው መሪ ስለ ሆርሙዝ “በጣም ደስተኛ” መሆናቸውን ተናገሩ

    ትራምፕ እና ዢ በደቡብ ኮሪያ በተገናኙበት ወቅት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ዶናልድ ትራምፕ የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ "የሆርሙዝ ወሽመጥ ክፍት እና/ወይም በፍጥነት በመከፈቱ በጣም ደስተኛ ናቸው" ሲሉ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

    ትራምፕ በቻይና ግንቦት 14 እና 15 የሚያደርጉት ስብሰባ እንደሚካሄድ እና "ልዩ እና ምናልባትም ታሪካዊ" እንደሚሆን ተናግረዋል።

    "ብዙ ነገር ይሳካል!"

    ቻይና ትልቋ የኢራን ነዳጅ ገዢ ስትሆን 38 በመቶ የሚሆነውን ነዳጇን የምታገኘው በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በኩል ነው።

    ቻይና፣ ኢራን ከአሜሪካ ጋር እንድትደራደር በማሳሰብ ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውታለች። እንዲሁም የተኩስ አቁም ስምምነቱን እና የሰላም ድርድሩን እንደገና መጀመርን እንደምትደግፍ ትናገራለች።

  6. የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ የአሜሪካ እገዳ የሚቀጥል ከሆነ ሆርሙዝ “ክፍት ሆኖ አይቆይም” ሲሉ አስጠነቀቁ

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ ሞሐመድ ባጋር ጋሊባፍ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ ሞሐመድ ባጋር ጋሊባፍ

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ ሞሐመድ ባጋር ጋሊባፍ በኤክስ ገጻቸው ላይ ዶናልድ ትራምፕ “በአንድ ሰዓት ውስጥ ሰባት ነገሮችን ተናግረዋል፤ ሰባቱም ሐሰት ናቸው” ብለዋል።

    ጋሊባፍ “ጦርነቱን አላሸነፉም፤ በዚህ ውሸታቸው በድርድሮቹ የትም መድረስ እንደማይችሉ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል” ብለዋል።

    አፈ ጉባዔው ስለ ሆርሙዝ ወሽመጥ ሲናገሩም “የአሜሪካ እገዳ ስለቀጠለ”፤ “እንደተዘጋ ይቆያል” ብለዋል።

    የአፈጉባዔው አስተያየት ከዚህ ቀደም በኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የተባለውን ያረጋገጠ ሆኗል።

    “ወሽመጡ ክፍትም ሆነ ዝግ የሚመራበት ደንብ የሚወሰነው መሬት ላይ እንጂ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አይደለም” ብለው ነበር።

    ጋሊባፍ አስተያየታቸውን የሰጡት የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ በኤክስ ገጻቸው ላይ በእንግሊዘኛ የሆርሙዝ ወሽመጥ “በቀረው የተኩስ አቁሙ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ክፍት ነው” ካሉ በኋላ “ለሁሉም የንግድ መርከቦች ማለፍ ተፈቅዷል” ብለው ነበር።

    የአራጋቺ አስተያየት የተለያዩ ትችቶችን አስተናግዷል። የኢራን መገናኛ ብዙኃን እና ወግ አትባቂዎች ምን ማለታቸው እንደሆነ "ግልጽ" እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

    ጋሊባፍ በኤክስ ገጻቸው ላይ "የመገናኛ ብዙኃን ፐሮፖጋንዳ እና የሕዝብ አስተያየትን መቅረጽ የጦርነት አስፈላጊ አካል ናቸው፤ የኢራን ሕዝብ ግን በእነዚህ ስልቶች ተጽዕኖ አይደረግበትም" ብለዋል።

  7. በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚደረግ ጉዞ የኢራን አብዮታዊ ዘብ ፈቃድ እንደሚያስፈልገው ተዘገበ

    በሆርሙዝ የሚያልፍ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በሆርሙዝ በኩል የሚያልፉ “ሁሉም የንግድ መርከቦች ሚያደርጉት ጉዞ ለቀሪው የተኩስ አቁሙ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ክፍት እንዲሆን መታወጁን” በኤክስ ገጻቸው አስታውቀው ነበር።

    የኢራን መንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያ አንድ “ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣንን” ጠቅሶ ባስተላለፈው ዘገባ፤ የመርከቦቹ ጉዞ የሚከናወነው “በተለየ መስመር” እንደሆነ ገልጿል። መርከቦቹ ለማለፍ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ባሕር ኃይል ፈቃድ እንደሚያስፈልጋቸውም ጠቅሷል።

    ባለሥልጣኑ ለቴሌቪዥን ጣቢያው እንደተናገሩት፤ ይህ የተለየ የጉዞ መስመር የተወሰነው በኢራን የወደቦች እና ማሪታይም ድርጅት ነው።

    ጣቢያው ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣኑን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚደረግ የወታደራዊ መርከቦች ጉዞ አሁንም ቢሆን "የተከለከለ" ነው።

    በሌላ በኩል የመርከብ ጉዞ ኩባንያዎች የሆርሙዝ ደኅንነት እስከሚረጋገጥ ድረስ ወሽመጡን እንደማይጠቀሙ ተናግረዋል። ቢቢሲ ያነጋገረው አንድ የነዳጅ እና የጋዝ ጫኝ መርከቦች ኦፕሬተር፤ ለጊዜው የኢራን መግለጫ “ምንም የሚቀይረው ነገር የለም” ብሏል።

    “አላስፈላጊ አደጋ ውስጥ መግባት አለብን ብለን አናስብም፤ የኩባንያችን በወሽመጡ በኩል ቀድሞ የሚያልፍ ተቋም እንሆናለን የሚል አቋም የለውም” ሲል ገልጿል።

    በቀጣናው የሚገኙ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ኦፕሬተር የሆነው ‘ስቴና በልክ’ የተሰኘው ኩባንያ በበኩሉ “ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተለ” መሆኑን አስታውቋል።

    “የእያንዳንዱ ጉዟችን ውሳኔ የሚመሠረተው የሠራተኞቻችን እና የመርከቦቻችን ደኅንነት ላይ ነው፤ ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑን እስካላረካን ድረስ ጉዞ አንጀምርም” ብሏል።

  8. ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ ጉዞ ላይ የተጣለው እገዳ እንደሚቀጥል አስታወቁ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ከዚህ ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ የወሰደችው ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ ጉዞን የማገድ እርምጃ ቴህራን ስምምነት ላይ እስከምትደርስ ድረስ “በሙሉ ኃይል እና ተፈጻሚነት” እንደሚቀጥል ተናገሩ።

    ኢራን ዘግታ የቆየችውን የሆርሙዝ ወሽመጥ ለቀሪዎቹ የተኩስ አቁም ቀናት እንደምትከፍት አስታውቃለች።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለዚህ እርምጃ ምስጋና የሰጡበትን የትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ጽሁፍ ከለጠፉ በኋላ ሌላ መልዕክት አጋርተዋል።

    ሆርሙዝ ቢከፈትም፤ “ከኢራን ጋር ያለን ጉዳይ 100% እስኪጠናቀቅ ድረስ በኢራን ላይ የተደረገው የባህር ኃይል እገዳ በሙሉ ኃይል እና ተፈፃሚነት ይቀጥላል" ብለዋል።

    "አብዛኛዎቹ ነጥቦች ድርድር የተደረገባቸው በመሆኑ ይህ ሂደት በጣም ፈጣን መሆን አለበት። ለዚህ ጉዳይ ለሰጣችሁት ትኩረት አመሰግናለሁ! ፕሬዝዳንት ዶናልድ ጄ. ትራምፕ" ሲሉ ውሳኔያቸውን አስታውቀዋል።

    አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚጓዙ ወይም ከዚያ የሚመጡ መርከች ላይ እገዳ የጣለቸው ሰኞ ዕለት ነበር።

    የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር በዚህ እርምጃ አማካኝነት ኢራን ከፔትሮኬሚካል ሽያጭ የምታገኘው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እንዲቋረጥ የማድረግ ዓላማ አለው።

  9. ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥ ለቀሪዎቹ የተኩስ አቁሙ ቀናት መከፈቱን አስታወቀች

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የሆርሙዝ ወሽመጥ “ለቀረው የተኩስ አቁም ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ክፍት” እንደሚሆን የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ አስታወቁ።

    አራግቺ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ “ሊባኖስ ውስጥ በተደረሰው ተኩስ አቁም መሰረት በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚደረግ የሁሉም የንግድ መርከቦች ጉዞ ለቀሪው የተኩስ አቁሙ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ክፍት እንዲሆን ታውጇል” ብለዋል።

    ለ40 ቀናት የተዋጉት አሜሪካ እና ኢራን በፓኪስታን አሸማጋይነት የሁለት ሳምንት ተኩስ አቁም መፈጸማቸው ይታወሳል። ይህ ተኩስ አቁም በሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ይጠናቀቃል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ የመርከቦቹ ጉዞ የሚካሄደው “የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ የወደብ እና ማሪታይም ድርጅት አስቀድሞ ባሳወቀው የተቀናጀ መስመር” በኩል እንደሆነም ገልጸዋል።

    ለኢራን ውሳኔ ምላሽ የሰጡት አሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “አመሰግናለሁ” ሲሉ ትሩዝ ሶሻል በተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ጽፈዋል።

    ትራምፕ፤ “ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥ ሙሉ በሙሉ ክፍት መሆኑን እና ለሙሉ ጉዞ ዝግጁ መሆኑን አሁን አስታውቃለች። አመሰግናለሁ!" ብለዋል።

    የካቲት ላይ በአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት የተከፈተባት ኢራን ብዙ ከዓለም ነዳጅ ማጓጓዣ መስመሮች መካከል በርካታ መርከቦችን በማስተናገድ ቀዳሚ የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥ ዘግታ ቆይታለች።

    ለዚህ እገዳ ምላሽ የሰጠችው አሜሪካ ደግሞ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በወሽመጡ በኩል ወደ ኢራን ወደቦች ጉዞ እንዳይደረግ ከልክላለች።

  10. የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ሄዝቦላህ ላይ የተከፈተው ዘመቻ “አሁንም አልተጠናቀቀም” አሉ

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    እስራኤል፤ ዳግም ውጊያ የሚጀመር ከሆነ ወደ መኖሪያቸው በመመለስ ላይ ያሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ንጹኃን ሊባኖሳውያን በድጋሚ ከደቡብ ሊባኖስ ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ ማስጠንቀቋን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ (ኤኤፍፒ) ዘገበ።

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ በቴሌቪዥን በተላለፈ መግለጫቸው፤ ሊባኖስ ውስጥ የተፈጸሙ ጥቃቶች “በርካታ ግቦችን ማሳካታቸውን” ተናግረዋል። ቢሆንም ግን ሄዝቦላህ ላይ የተከፈተው ዘመቻ “አሁንም እንዳልተጠናቀቀ” ገልጸዋል።

    “ዳግም ውጊያ ከተጀመረ ተልዕኮውን ለማጠናቀቅ እንዲቻል ወደ ደኅንነት ዞኑ የተመለሱት እነዛ ነዋሪዎች ለቅቀው መውጣት ይኖርባቸዋል” ብለዋል።

    የእስራኤል ጦር "አፅድቶ የተቆጣጠራቸውን" ቦታዎች በሙሉ ይዞ እንደሚቀጥል መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

    ሄዝቦላህ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከተደረሰ በኋላ በሰጠው አስተያየት “"ማንኛውም የተኩስ አቁም በመላው የሊባኖስ ግዛት ሁሉን አቀፍ መሆን አለበት፤ ለጠላት እስራኤል ምንም ዓይነት የእንቅስቃሴ ነፃነት ሊፈቅድ አይገባም" ብሏል።

  11. የሄዝቦላህ አመራር ቡድኑ “መቼም ትጥቅ እንደማይፈታ” ለቢቢሲ ተናገሩ

    የሄዝቦላህ ከፍተኛ አመራር ዋፊቅ ሳፋ

    ሊባኖስ እና እስራኤል የደረሱት የ10 ቀን የተኩስ አቁም ስምምነት ከመጀመሩ አስቀድሞ ከቢቢሲ ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት የሄዝቦላህ ከፍተኛ አመራር ዋፊቅ ሳፋ ቡድን “መቼም፣ ጭራሽ” ትጥቅ እንደማይፈታ ገለጹ።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ሄዝቦላህን ትጥቅ ማስፈታት በቀጣይ ከሊባኖስ መንግሥት ጋር ለሚደረግ ድርድር የተቀመጠ መሠረታዊ ጥያቄ መሆኑን ተናግረዋል።

    ስለ ትጥቅ መፍታት የተጠየቁት ሳፋ ግን “ተገቢ ተኩስ አቁም፣ ትክክለኛ የሆነ እስከሚደረስ አይደረግም" ብለዋል።

    "እስራኤል ለቅቃ እስካልወጣች ድረስ አይሆንም። እስረኞች ከመመለሳቸው፣ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀያቸው ከመመለሳቸው እና መልሶ ግንባታ ከመጀመሩ በፊት ትጥቅ መፍታት አይኖርም። እስከዚያው ድረስ ስለ ሄዝቦላህ የጦር መሳሪያ ማውራት አይቻልም” ሲሉ ቅድመ ሁኔታዎቻቸውን ዘርዝረዋል።

    ቤይሩት ውስጥ በሚገኝ የመኖሪያ ሕንጻ ላይ የተደረገው ይህ ቃለ መጠይቅ በሄዝቦላህ እና በቀጣናዊ አጋሩ ኢራን መካከል ያለውን ቅንጅት ያሳያል። “ሄዝቦላህ እና ኢራን በአንድ ሰውነት ውስጥ ያሉ ሁለት ነፍሶች ናቸው” ብለዋል።

    “ያለ ኢራን ሄዝቦላህ ሊኖር አይችልም። ያለ ሄዝቦላህም አራን አትኖርም” ሲሉ በሁለቱ አካላት መካከል ስላለው “ሃይማኖታዊ፣ ሕጋዊ እና ርዕዮተ ዓለማዊ” ግንኙነት ገልጸዋል።

    የሺዓ እስልምና ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ቡድን የሆነው ሄዝቦላህ እንደ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ እስራኤል እና በርካታ የዓለም አገራት በሽብርተኛ ድርጅትነት ተፈርጇል።

    ቡድኑ የአሁኑን የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት የተቀላቀለው የካቲት ላይ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን ከተኮሰ በኋላ ነበር።

    ሄዝቦላህ ይህንን ጥቃት የፈጸመው በኢራን ጠቅላይ መሪ ላይ ለተፈጸመው ግድያ እንዲሁም ከህዳር 2016 ዓ.ም. አንስቶ እስራኤል በየቀኑ በሚባል ደረጃ ሊባኖስ ላይ ስትፈጽም ለነበረው ጥቃት በአጸፋ ምላሽነት መሆኑን ገልጿል።

    እስራኤልም ከፍተኛ የአየር ጥቃቶችን በመፈጸም እና ደቡባዊ ሊባኖስን በእግረኛ ወታደሮች በመውረር ምላሽ ሰጥታለች። ሄዝቦላህ ትጥቅ እስከሚፈታ ድረስም ይህንን ዘመቻ እንደምትቀጥል ተናግራለች።

    ሄዝቦላህ ቅድሚያ የሚሰጠው ለሊባኖስ ጥቅም ወይስ ለኢራን የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ሳፋ፤ “ያለ ምንም ጥርጥር ሄዝቦላህ የሚመለከተው የሊባኖስን ጥቅም ነው” ብለዋል።

    ኢራን ተኩስ አቁም ላይ እንዲደረስ ያሳደረችውን ግፊት ጨምሮ የምታደርጋቸው ድጋፎች ሊባኖስን ማገዛቸውን ጠቅሰዋል። ቢቢሲ ያነጋገራቸውን ጨምሮ በርካታ ሊባኖሳውያን ግን ቡድኑ ትጥቅ እንዲፈታ ይፈልጋሉ። አገሪቱን ግጭት ውስጥ ከትቷል ሲሉም ይወቅሳሉ።

    ሄዝቦላህ ትጥቅ ለመፍታት ፈቃደኛ ባለመሆኑ እና ሰፋ ያሉ ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጡ እንዲሁም እስራኤል የደኅንነት ጥያቄዎቿን አጥብቃ በመያዟ የተነሳ በሊባኖስ ተግባራዊ የሚሆን ማንኛውም ተኩስ አቁም ለረጅም ጊዜ የሚቆየውን ግጭት ለጊዜው ከመግታት ያለፈ ጥቅም ላይኖረው ይችላል።

  12. ኢራን የሊባኖስ ተኩስ አቁምን በበጎ እንደምትቀበለው ገልጻ ሄዝቦላህ ያደረገውን “ተጋድሎ” አወደሰች

    የሄዝቦላህን ባንዲራ የያዘ ታዳጊ ሌላ አዋቂ ሰው በሚነዳው ሞተር ላይ ተሳፍሮ

    የፎቶው ባለመብት, Adnan Abidi / Reuters

    ኢራን በሊባኖስ የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት ዲፕሎማሲያዊ ስኬት እና የሄዝቦላህ “ተጋድሎ” ውጤት እንደሆነ ገለጸች።

    ቴህራን የተኩስ አቁሙን የምትመለከተው በፓኪስታን አሸማጋይነት ከአሜሪካ ጋር የተደረሰው ሠፊ መግባባት አካል አድርጋ እንደሆነ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኢል ባቃኢ ተናግረዋል።

    ኢራን ሰፊ ቀጣናዊ የተኩስ አቁም እንዲደረስ ያለ ማቋረጥ ግፊት ስታደርግ መቆየቷንም በአጽንኦት አንስተዋል።

    የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተኩስ አቁም ላይ ለመደረሱ ለሄዝቦላህ እውቅና ሰጥተዋል። የፓርላማ አፈ ጉባኤው ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍ ኤክስ ገጻቸው ላይ በአረብኛ ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ ስምምነቱ “የሄዝቦላህ የጽናት እና የአክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ የአንድነት ውጤት እንጂ ሌላ አይደለም” ብለዋል።

    አፈ ጉባኤው የጠቀሱት ‘አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ’ ኢራን በቀጣናው ከሚገኙ አጋር ታጣቂ ቡድኖች ጋር የፈጠረችውን መረብ ለመግለጽ የምትጠቀምበት ስያሜ ነው።

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ የኩስድ ኃይሎች አዛዥ የሆኑት ኢስማኢል ቃኒ በበኩላቸው ሄዝቦላህን “ባለ ድል” ሲሉ ጠርተዋል። ስምምነቱ የሊባኖስ የትግል ኃይሎች የጽናት እና የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ድጋፍ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

    የኢራን መገናኛ ብዙኃንም የሊባኖስ ተኩስ አቁምን በተመለከቱ ዘገባዎቻቸው ያስተጋቡት የሄዝቦላህ “ተጋድሎ” እና የቴህራን ዲፕሎማሲያዊ ጫና ውጤት ነው የሚለውን የከፍተኛ ባለሥልጣናቱን አገላለጽ ነው።

  13. ሄዝቦላህ የተኩስ አቁም ጥሰቶች ከተፈጸሙ ‘ጣቴ ቃታ ላይ ነው’ አለ

    እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ ለስድስት ሳምንታት ባካሄደችው የኤር ድብደባ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው እየተመለሱ ነው
    የምስሉ መግለጫ, እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ ለስድስት ሳምንታት ባካሄደችው የኤር ድብደባ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው እየተመለሱ ነው

    ሄዝቦላህ በሊባኖስ እየተካሄደ ባለው የተኩስ አቁም ስምምነት ወቅት እስራኤል "ክህደት" ከፈጸመች "ጣቴ ቃታ ላይ ነው" ሲሉ አስታወቀ።

    በኢራን የሚደገፈው ቡድን በቴሌግራም ላይ ባወጣው መግለጫ እስካሁን ድረስ በግጭቱ ወቅት ያከናወናቸውን ተግባራት ሲገልጽ እአአ ከመጋቢት 2 እስከ ሚያዝያ 16 ባለው ጊዜ ውስጥ በእስራኤል ላይ 2 ሺህ 184 ዘመቻዎችን እንደፈጸመ ተናግሯል።

    እንግሊዝ እና አሜሪካን ጨምሮ በበርካታ አገሮች በሽብርተኛ ድርጅትነት የፈረጁት ሄዝቦላህ በተኩስ አቁም ድርድሩ ውስጥ አልተሳተፉም። ድርድሩ በእስራኤል እና በሊባኖስ መንግሥታት መካከል የተከናወነ ነው።

    ሐሙስ ዕለት ስለተገለጸው የተኩስ አቁም ስምምነት ምላሹን የሰጠው ሄዝቦላህ፤ "ማንኛውም የተኩስ አቁም ስምምነት በመላው የሊባኖስ ግዛት ውስጥ ተፈጻሚ መሆን አለበት። ጠላት የሆነችው እስራኤል የመንቀሳቀስ ነፃነት ሊፈቀድላት አይገባም” ብሏል።

    እስራኤል ለ10 ቀናት የሚቆይ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ብትስማም ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የእስራኤል ወታደሮች እስከ የተኩስ አቁም መጨረሻ ድረስ በሊባኖስ ግዛት "የደህንነት ቀጠና" ውስጥ እንደሚቆዩ ተናግረዋል።

  14. ፓኪስታን በሊባኖስ የተደረሰውን የተኩስ አቁም አወድሳ የትራምፕን “ብልሃት” የተሞላበት ዲፕሎማሲ አደነቀች

    የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ በእስራኤል እና በሊባኖስ መካከል ለአስር ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት በመደረጉ መደሰታቸውን ገልጸው፣ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን "ደፋር እና ብልህ የዲፕሎማሲ ጥረቶች" አወድሰዋል።

    ሸሪፍ አገራቸው "ለሊባኖስ ሉዓላዊነት እና ለግዛት አንድነት ያላትን የማይናወጥ ድጋፍ" አጽንኦት ሰጥተዋል።

    በዚህ ሳምንት በእስራኤል እና በሊባኖስ መካከል በዋሺንግተን ውይይት የተደረገ ሲሆን ይህም በጎረቤት አገራቱ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመጀመር ታሪካዊ እርምጃ መሆኑ ተገልጿል።

    ይህ የሆነው ባለፈው ሳምነት መጨረሻ በፓኪስታን አስተናጋጅነት በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የተደረገው ድርድር ሳይሳካ ከቀረ በኋላ ነው።

    ኢዝላማባድ በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ተግባራዊ የሆነውን የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት በማደራደር ረገድ ቁልፍ ሚና ተጫውታለች።

    የፓኪስታን ጦር አዛዥ ሐሙስ ዕለት የተኩስ አቁሙን ለማራዘም በሚደረገው ጥረት ዙሪያ ለመነጋገር በቴህራን ከኢራን ባለሥልጣናት ጋር እንደተገናኙ የሚገልጹ ዘገባዎች ወጥተዋል።

  15. ዩኬ እና ፈረንሳይ 40 አገራት የሚሳተፉበት በሆርሙዝ ወሽመጥ ዙሪያ የሚመክር ጉባዔ ዛሬ ያካሄዳሉ

    የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን (በስተግራ) የዩናይትድ ኪንግደሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመርን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ዩኬ እና ፈረንሳይ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በሆርሙዝ ወሽመጥ የመርከቦችን እንቅስቃሴ ወደነበረበት ለመመለስ ስለሚኖረው የጋራ ጥረት ለመወያየት ከአጋሮቻቸው ጋር ስብሰባ ሊያደርጉ ነው።

    ቴህራን ለአሜሪካ እና ለእስራኤል ጥቃቶች ምላሽ በመስጠት የኢራን ወሳኝ የሆነውን የውሃ መስመር ዘግታለች።

    አሜሪካ በበኩሏ የኢራን ወደቦችን በመዝጋቷ ምክንያት ለዓለም አቀፍ የኃይል ዋጋ መጨመር ምክንያት ሆኗል።

    ወደ 40 የሚጠጉ አገሮች ዛሬ ከሰዓት በኋላ በሚደረገው ስብሰባ ላይ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል ሲል የኪር ስታርመር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

    መሪዎቹ "በቀጣናው ውስጥ ያለውን የተኩስ አቁም ስምምነት በመደገፍ እና የመርከብ መንገዶች ለረዥም ጊዜ በኩል በድጋሚ እንዲከፈቱ እና እንዲጠበቁ በማድረግ ላይ ያተኩራሉ" ሲል አክሏል።

    ስታርመር ወሽመጡ “ያለ ቅድመ ሁኔታ እና በፍጥነት እንደገና መከፈቱ ዓለም አቀፍ ኃላፊነት ነው" በማለት ለተሰብሳቢዎቹ እንደሚገልጹ ዳውኒንግ ስትሪት አስታውቋል።

    በተጨማሪም "የመርከብ ነፃነትን ለማረጋገጥ ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ተልዕኮ" ሊሰማራ እንደሚችል ኤኤፍፒ ዘግቧል።

  16. ትራምፕ ኢራን ያበለጸገችውን ዩራኒየም ለማስረከብ ተስማምታለች አሉ

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ያበለጸገችውን ዩራኒየም ለማስረከብ መስማማቷን ተናገሩ።

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል እየተካሄደ በነበረው የሰላም ድርድር ላይ ካላግባቡ ነጥቦች መካከል ቴህራን ያበለጸገችው ዩራኒየም አንዱ ነበር።

    ፕሬዚዳንቱ በሳምንቱ መጨረሻ በዋሺንግተን እና በቴህራን መካከል ንግግር ሊቀጥል እንደሚችል ተናግረው፤ ከስምምነት ልንደርስ “በጣም ተቃርበናል” ብለዋል።

    ትራምፕ በላስቬጋስ በአሜሪካ ምጣኔ ኃብት ላይ ባተኮረ ጉባዔ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ጦርነቱ “ያለምንም እንከን” እየሄደ እንደሆነ ተናግረው በቅርቡ ማብቃት አለበት ብለዋል።

    ቀደም ሲል ዋይት ሐውስ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንደማይኖራት መስማማቷን ገልጾ ነበር።

    አክሎም ባለፈው ዓመት እስራኤል እና አሜሪካ የፈጸሙትን ድብደባ ተከትሎ ከመሬት በታች እንደተቀበረ የሚታመነውን የበለጸገ ዩራኒየም “የኒውክሌር አቧራ” አራግፈው ቆፍረው እንደሚያወጡ ተናግረው ነበር።

    ትራምፕ በቀጣይ ዙር በሚደረገው የሁለቱ አገራት ድርድር እርግጠኛ ሆነው ታይተዋል።

    ነገር ግን ከአምስት ቀናት በኋላ የሚያበቃው የተኩስ አቁም ስምምነቱ ስለመራዘሙ እርግጠኛ አለመሆናቸውን ጨምረው ተናግረዋል።

  17. በእስራኤል እና በሊባኖስ መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ምን ምን ነጥቦችን ይዟል?

    የእስራኤል ጦር በሊባኖስ ድንበር አቅራቢያ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የእስራኤልና የሊባኖስ መሪዎች በመካከላቸው የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት በደስታ ተቀብለውታል።

    ኔታንያሁም “ታሪካዊ የሰላም ስምምነት ለማድረግ እድል” እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

    የተኩስ አቁም ስምምነቱ ለአስር ቀናት የሚቆይ ሲሆን የሚደረጉ ድርድሮች የለውጥ ምልክቶችን ካሳዩ "በጋራ ስምምነት" ሊራዘም ይችላል።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው ዝርዝር መረጃ መሰረት ስምምነቱ የሚከተሉትን ነጥቦች ይዟል።

    • እስራኤል "በማንኛውም ጊዜ፣ በታቀዱ፣ በተጨባጭ ወይም በቀጣይ ከሚፈጸሙ ጥቃቶች ራሷን ለመከላከል አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ የመውሰድ” መብት ይኖራታል።
    • ሊባኖስ፣ ሄዝቦላህ እና ሌሎች "ከመንግሥት ውጭ የሆኑ የታጠቁ ቡድኖች" በእስራኤል ዒላማዎች ላይ ጥቃት እንዳይሰነዝሩ ለመከላከል "ትርጉም ያላቸውን እርምጃዎች" መውሰድ አለባት።
    • በስምምነቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አካላት የሊባኖስ የጸጥታ ኃይሎች ለሊባኖስ ደህንነት ብቸኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ይገነዘባሉ።
    • እስራኤል እና ሊባኖስ "ቀሪ ጉዳዮችን ሁሉ ለመፍታት" አሜሪካ ተጨማሪ ቀጥተኛ ውይይቶችን እንድታመቻች ጠይቀዋል።

    መግለጫው አክሎም የተኩስ አቁም ስምምነቱ እስራኤል በሁለቱ ወገኖች መካከል "በቀና ልቦና ዘላቂ የጸጥታ እና የሰላም ስምምነት ለመድረስ የሚደረግ ድርድር" ለማስቻል “መልካም ፈቃደኝነቷን” ያሳየችበት እንደሆነ ገልጿል።

    ሄዝቦላህ በተኩስ አቁም ስምምነቱ ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆኑን ያሳየ ቢሆንም፣ በሊባኖስ ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን “ሙሉ በሙሉ እንዲቆሙ” እና "የእስራኤል ኃይሎች የመንቀሳቀስ ነፃነት እንደሌላቸው" የሚሉ ሃሳቦች መካተት እንዳለበት ተናግሯል።

  18. በእስራኤል አየር ድብደባ ተፈናቅለው የነበሩ ሊባኖሳውያን ወደ ቤታቸው መመለስ ጀመሩ

    ወደ ቤታቸው ለመመለስ እየተሰናዱ ያሉ ሊባኖሳውያን እቃቸውን በመኪና ላይ ሲጭኑ ታይተዋል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ወደ ቤታቸው ለመመለስ እየተሰናዱ ያሉ ሊባኖሳውያን እቃቸውን በመኪና ላይ ሲጭኑ ታይተዋል

    በሊባኖስ ላለፉት ስድስት ሳምንታት እስራኤል ስታካሄድ የነበረው የአየር ድብደባ በተኩስ አቁም እንዲቆም ከተደረገ በኋላ ቀያቸውን ጥለው የተፈናቀሉ ሊባኖሳውያን መመለስ ጀመረዋል።

    አንዳንድ ነዋሪዎች እቃቸውን በመኪና ጭነው ወደ ደቡባዊ ሊባኖስ ሲያመሩ ታይተዋል።

    የእስራኤል እና የሊባኖስ መሪዎች የተኩስ አቁም ላይ መድረሳቸውን አወድሰውዋል።

    ኔታንያሁ “የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ታሪካዊ ዕድል” መኖሩን ተናግረዋል።

    የተኩስ አቁሙ ለአስር ቀን የሚቆይ ሲሆን የሚደረጉ ድርድሮች ለውጥ ካሳዩ “በጋራ ስምምነት ሊራዘም እንደሚችል” ተገልጿል።

    አሻንጉሊት እና ቀሪ ቁሳቁሶቻቸውን የያዙ ሁለት ሴቶች ወደ መኖሪያ ቀያቸው እየተመለሱ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አምስት ሰዎች በአንዲት አነስተኛ ሞተር ላይ ተጭነው ወደ ሲዶን በሚወስደው ዋና መንገድ ላይ ሲጓዙ ይታያሉ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, አምስት ሰዎች በአንዲት አነስተኛ ሞተር ላይ ተጭነው ወደ ሲዶን በሚወስደው ዋና መንገድ ላይ ሲጓዙ ይታያሉ
  19. የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ የእስራኤልን እና ሊባኖስን የተኩስ አቁም ስምምነት አወደሱ

    የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በእስራኤል እና በሊባኖስ መካከል የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነትን በደስታ እንደሚቀበሉ እና አሜሪካን ስላደረገችው አስተዋጽኦ አመስግነዋል።

    "ይህ ለግጭቱ የረዥም ጊዜ መፍትሄ ለማግኘት ለሚደረገው ድርድር መንገድ እንደሚጠርግ እና በቀጣናው ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ ሰላም ለማምጣት ለሚደረጉ ቀጣይ ጥረቶች አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተስፋ አደርጋለሁ" ሲሉ ጉቴሬዝ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

    ሁሉም ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነቱን እና "ሁልጊዜም ዓለም አቀፍ ሕግን እንዲያከብሩ" አሳስበዋል።

  20. ትራምፕ የኢራን ጦርነት “በጣም በቅርቡ ማብቃት አለበት” አሉ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኔቫዳ ለተሰበሰቡ ሰዎች የኢራን ጦርነት “በቅርቡ ማብቃት አለበት” ሲሉ ተናገሩ።

    ትራምፕ “በኢራን የሚካሄደው ጦርነት ያለምንም እንከን እየተካሄደ ነው” ካሉ በኋላ “በቅርቡ መጠናቀቅ አለበት” ብለዋል።

    ፕሬዚዳንቱ ይህንን ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ ባያብራሩም የአሜሪካ ጦር ሮኬቶችን መትቶ ሲጥል ግን ብቃት እንዳለው ተናግረዋል።

    ባለፈው ሳምነት መጨረሻ ላይ በፓኪስታን ኢዝላማባድ የተካሄደው የሰላም ድርድር ያለምንም ውጤት ተበትኗል።

    ዋሺንግተን በሁለቱ አገራት መካከል ቀጣይ ድርድር ለማድረግ ንግግሮች መኖራቸውን ቢገልጽም መቼ እና የት ይካሄዳል የሚለውን ግን ይፋ ማድረግ አልፈለገም።