በእስራኤል እና ሊባኖስ መካከል የተደረሰው የአስር ቀን የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ መሆን ጀመረ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በእስራኤል እና ሊባኖስ መካከል የተደረሰው የአስር ቀን የተኩስ አቁም ከእኩለ ለሊ ት ጀምሮ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የተኩስ አቁም ስምምነቱ ለአስር ቀን ብቻ የተደረሰ ቢሆንም ሊራዘም እንደሚችል ጠቁመዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከሊባኖስ ጋር “ታሪካዊ የሰላም ስምምነት” ዕድልን ይፈጥራል ብለዋል።
በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ የተኩስ አቁሙን እንደሚያከብር ጠቅሶ በኋላ ላይ “በሁሉም የሊባኖስ ግዛቶች የተሟላ ጥቃቶችን ማቆም” እንዲያካትት እና “የእስራኤል ጦር በነጻነት እንዳይንቀሳቀስ” ጠይቋል።
ኔታንያሁ ጦራቸው በደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ 10 ኪሜ ያሀል ዘልቆ በመግባት “የደህንነት ቀጣና” ውስጥ እንደሚቆዩ የተናገሩ ሲሆን ይህ ግን ከሄዝቦላህ ፍላጎት ውጭ ነው።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በስምምነቱ መሠረት የሊባኖስ መንግሥት ሄዝቦላህ እስራኤል ላይ ጥቃት እንዳይፈጽም ለማድረግ “ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰድ” ይኖርበታል ብሏል።
አክሎም የሊባኖስ የጸጥታ ኃይል ለሊባኖስ ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ መከላከያ “ሙሉ ኃላፊነት” እንዳለበት አስታውቋል።
የተኩስ አቁሙ ተግባራዊ መሆን እንደጀመረ የእስራኤል መከላከያ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኙ ከ380 በላይ የሄዝቦላህ ዒላማዎችን መደብደቡን ገልጿል።
ዒላማ ከሆኑት መካከል የሮኬት ማስወንጨፊያዎች፣ ዋና መስሪያ ቤቱን እና የሄዝቦላህ አባላት ይገኙበታል።
ትራምፕ የሊባኖስ እና የእስራኤል መሪዎች በዋሺንግተን ተገናኝተው በቀጣይ ጉዳዮች ላይ እንዲወያዩ መጋበዛቸውን ተናግረዋል። እስካሁን ግን ከየትኛውም ወገን ስለግብዣው ማረጋገጫ አልተገኘም።
ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ ዛሬ ለሊባኖስ “ታሪካዊ” ቀን ነው ሲሉ ጽፈዋል።
“መልካም ነገሮች እየሆኑ ነው” ያሉት ትራምፕ በሌላ የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፋቸው “ሄዝቦላህ በዚህ ወሳኝ ጊዜ ተገቢውን እና የተረጋጋ ባህሪውን እንደሚያሳይ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters




















