ቀጥታ, ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደር ጣልቃ መግባት ውጥረቱን እንደሚያባብስ አስጠነቀቀች

በኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደር ውስጥ ማንኛውም ጣልቃ ገብነት ውጥረቱን እንደሚያባብስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ተናግረዋል። በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል እያለፈ የነበረ በፓናማ የተመዘገበ መርከብ ትናንት ቅዳሜ ጥቃት ከደረሰበት በኋላ አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት ፈጽማለች። የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በአጸፋ ምላሽ በኩዌት እና ባሕሬን በሚገኙ የአሜሪካ መሠረተ ልማቶች ላይ የድሮን እና ሚሳዔል ጥቃቶች ማድረሱን ገልጿል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ኢራን የኒውክሌር ተቆጣጣሪዎች እንዲገቡ ልትፈቅድ ነው መባሉን አስተባበለች

    የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ጦርነቱን ለመቋጨት ከአሜሪካ ጋር የተደረገው የመጀመሪያው ዙር ንግግር መጠናቀቁን ተከትሎ ኢራን ዓለም አቀፍ የኒውክሌር ተቆጣጣሪዎች ወደ አገሪቱ እንዲገቡ ልትፈቅድ ነው መባሉን የቴህራን መንግሥት አስተባበለ።

    የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ በስዊትዘርላንድ ከተካሄደው ድርድር ባደረጉት ንግግር ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኤነርጂ ኤጀንሲ ጋር የሚካሄዱ ውይይቶች “ዛሬ ጭምር” ሊጀመሩ ይችላሉ ብለው ነበር።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን ለአገሪቱ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በሰጠው ማብራሪያ፤ የኒውክሌር ቁጥጥርን በተመለተከተ የተገባ “አዲስ ቃል የለም” ብለዋል።

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ቫንስ ሰኞ ጠዋት ላይ በስዊትዘርላንድ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት የኒውክሌር ተቆጣጣሪዎች ወደ ኢራን የሚመለሱት መቼ እንደሆነ ተጠይቀዋል።

    ለዚህም ምላሽ ሲሰጡ ሂደቱ “ቢያንስ በዚህ ሳምንት” እንደሚጀመር፤ ከተቆጣጣሪዎቹ ጋር የሚደረገው ንግግር ግን “ዛሬ ጭምር ሊካሄድ እንደሚችል” ገልጸዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ኢራን "በዋና ዋና የጦር መሣሪያዎች ላይ ፍተሻ እንዲካሄድ ትስማማለች” ሲሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ጽፈዋል።

    ‘ኢርና’ ለተሰኘው ለኢራን መንግሥት የዜና ወኪል ቃለ መጠይቅ የሰጡት የቴህራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኤል ባቃኢ ግን አገራቸው የኔውክሌር ተቆጣጣሪዎችን በተመለከተ "ምንም አይነት አዲስ ቃል" እንዳልገባች ተናግረዋል።

    ከተባበሩት መንግሥታት ተቆጣጣሪዎች ጋር የሚደረግ ማንኛውም ግንኙነት የሚከናወነው “በፓርላማው እና በጠቅላይ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት በተቀመጡት ነባር አሰራሮች" መሠረት እንደሆነም አጽንኦት ሰጥተዋል።

    ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ እስካሁን በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጠም።

    ኢራን የኤጀንሲው ወደ የኒውክሌር ስፍራዎች እንዳይጓዝ የከለከለችው ባለፈው ዓመት በተካሄደው የ12 በቀናት ጦርነት ወቅት እስራኤል እና አሜሪካ የኒውክሌር ጣቢያዎችን ከደበደቡ በኋላ ነው።

    ይህንን ውሳኔ ተከትሎም የመንግሥታቱ ድርጅት ተቆጣጣሪ ተቋም የቀሩትን ባለሙያዎቹን ከኢራን አስወጥቷል።

  2. አሜሪካ በኢራን ነዳጅ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ አላላች

    የኢራን ባንዲራ እና የሚቃጠል ነዳጅ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ዋሽንግተን ከአስርት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢራን ነዳጅ በአሜሪካ ዶላር እንዲሸጥ በመፍቀድ ቴህራን ላይ የጣለችውን ማዕቀብ በጊዜያዊነት አነሳች።

    ለ60 ቀናት የሚቆየውን የማዕቀብ ማላላት እርምጃ ሰኞ ምሽት ይፋ ያደረገው የአሜሪካ ግምጃ ቤት ነው። ይህ እርምጃ የኢራንን ኢኮኖሚ አንቆ የያዘው እና ለረጅም ጊዜ የቆየው የአሜሪካ ማዕቀብ ዋነኛ ምሰሶዎች እንዲወገዱ ያደርጋል።

    በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ ፈቃድ መሠረት ኢራን እስከ ነሐሴ ወር ድረስ ድፍድፍ ነዳጅ እንዲሁም የፔትሮኬሚካል ምርቶችን ማምረት፣ መሸጥ እና መላክ ትችላለች። ይህ የማዕቀብ እፎይታ የኢራን ነዳጅ በቀጥታ ወደ አሜሪካ እንዲገባም ያስችላል።

    በተጨማሪም የኢራን የባንክ ዝውውር፣ ኢንሹራስ እና ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ የተጣለው ማዕቀብ መነሳቱ ቴህራን ከዚህ ቀደም ድፍድፍ ነዳጇን ለመሸጥ ስትከተል የነበረውን ውስብስብ አሰራር ያስቀራል።

    የግምጃ ቤት ኃላፊው ስኮት ቤንሰንት እንደተናገሩት ለ60 ቀናት የሚቆይ የማዕቀብ እፎይታ የተሰጣት ኢራን በምላሹ ወሳኙ የባሕር መተላለፊያ የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥ ለመክፈት ቃል ገብታለች።

    የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤነርጂ ኤጀንሲ የኒውክሌር ተቆጣጣሪዎችም ወደ አገሪቱ እንዲገቡ ትፈቅዳለች ብለዋል።

    ኢራን ግን ይህ ተቆጣጣሪዎች ወደ አገሪቱ እንዲገቡ ልትፈቅድ ነው መባሉን አስተባብላለች።

    አሜሪካ የማዕቀብ ማላላት እርምጃውን የወሰደችው ስዊዘርላንድ ውስጥ ሁለቱን አገራት ሲያደራድሩ የነበሩት አሸማጋዮች ጥሩ መሻሻል መታየቱን ከገለጹ በኋላ ነው።

    ኳታር እና ፓኪስታን ሰኞ ዕለት ባወጡት መግለጫ አሜሪካ እና ኢራን “በ60 ቀናት ውስጥ የመጨረሻ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ” ላይ መስማማታቸውን አስታውቀዋል።

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስም የመጀመሪያው ዙር ንግግር “በጣም ጥሩ መሠረት” መጣሉን ተናግረዋል።

  3. በኳታር የጋዝ ማቀነባበሪያ ላይ ባጋጠመ ፍንዳታ 13 ሰዎች ሞቱ

    ፍንዳታ

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    በግዙፉ የኳታር የጋዝ ማምረቻ ተቋም ላይ በደረሰ ፍንዳታ ቢያንስ 13 ሰዎች እንደሞቱ እና 66 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገለጸ።

    ራስ ላፋን በተሰኘው የኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ የሚገኘው እና ወደ ፈሳሽነት የተቀየረ የተፈጥሮ ጋዝ ዋነኛ ማቀነባበሪያው የሆነው ስፍራ እሁድ ምሽት “የቴክኒካል አደጋ” እንዳጋጠመው የኳታር የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

    በዚህ አደጋ ምክንያት የከተማው ሰማይ ብርቱካናማ ቀለም ይዞ ታይቷል። የእሁድ ዕለቱ ፍንዳታ ከራስ ላፋን 70 ኪሎ ሜትር ርቀት በሚገኘው ማዕከላዊ ዶሃ ጭምር ተሰምቷል።

    በዚህ ጥቃት የሞቱት ሰዎች የሕንድ እና የፓኪስታን ዜግነት ያላቸው እንደሆኑ ተገልጿል።

    ፍንዳታው በአገሪቱ ኤክስፖርት ምርት ላይ ተጽዕኖ እንደማይኖረው የተናገሩት የኳታር የኤነርጂ ሚኒስትር ሳዐድ ሸሪዳ አል ካቢ፤ “ያጋጠመው አደጋ ነው፤ በተፈጥሮውም ትንኮል ወይም በጠበኛ ድርጊት [የተከሰተ] አይደለም” ብለዋል።

    ጥቃቱ የደረሰበት ስፍራ የሚገኝበት ራስ ላፋን በዓለም ትልቁ ሰው ሰራሽ ወደብ ሲሆን በውስጡም የዓለም ትልቁን ወደ ፈሳሽነት የተቀየረ የተፈጥሮ ጋዝ ለውጭ ገበያ ማቅረቢያ ተቋምን ይዟል።

    የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነትን ተከትሎ ስፍራው በኢራን ጥቃቶች ተፈጽመውበት ነበር። የአሁኑን ፍንዳታ ምክንያት ለማወቅ ምርመራ መጀመሩን የኤነርጂ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

  4. የአሜሪካ እና ኢራን ንግግር ውጤት እያስገኘ መሆኑን ምክትል ፕሬዝዳንት ቫንስ ገለጹ

    አሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አሜሪካ እና ኢራን ስዊትዘርላንድ ውስጥ እየካሄዱት ባለው ንግግር “መልካም ውጤቶች መገኘታቸውን” እና የተሳካ የመጨረሻ ስምምነት ላይ ለመድረስ “ጥሩ መሠረት መጣሉን” የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ተናገሩ።

    ንግግሩ ከተጀመረ በኋላ የኢራን ልዑካን ረግጠው ለመውጣት ቢዝቱም በሁለቱ አገራት ተወካዮች መካከል የሚካሄደው ድርድር ለረጅም ሰዓታት ቀጥሎ ነው አዎንታዊ ደረጃ ላይ መድረሱ የተነገረው።

    የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤነርጂ የኒውክሌር ተቆጣጣሪዎች ተመልሰው ወደ ኢራን በመግባት በመጀመሪያ ደረጃው ንግግር ስምምነት የተደረሰባቸውን ነጥቦች ማክበሯን ያረጋግጣሉ ተብሏል።

    በአሜሪካም በበኩሏ ኢራን የተለያዩ የእህል ምርቶችን ከውጭ ለመግዛት እንድትችል ለማድረግ ሲባል የታገደባት ሀብት እንዲንቀሰቀስ ትፈቅዳለች።

    ወሳኙ የባሕር ላይ መተላለፊያ ሆርሙዝ ወሽመጥ “ክፍት ነው” ያሉት የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት፣ በሊባኖስ የሚካሄደውን ጦርነት በተመለከተም ተገቢው ቅንጅት እና ቴክኒካዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ንግግር ማድረግ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

  5. የመጀመሪያው ቀን ድርድር ሲጠናቀቅ፤ በቀጣይ ቀናት የቴክኒክ ውይይት እንደሚቀጥል ተገለጸ

    የኢራን ልዑካን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኢራን እና አሜሪካ የመጀመሪያ ቀን ድርድር የተገባደደ ሲሆን፤ ሳምንቱን በሙሉ በስዊትዘርላንድ የቴክኒክ ጉዳዮች ውይይት እንደሚቀጥል ተገልጿል።

    አደራዳሪዎቹ ኳታር እና ፓኪስታን “የኢስላማባድ የመግባቢያ ሰነድ ማዕቀፍን በተመለከተ የመጀመሪያው ዙር ንግግር ተገባዷል” ብለዋል።

    በተቀረው የሳምንቱ ቀናት የቴክኒክ ውይይት እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን በቀጣይ 60 ቀናት ውስጥ የመጨረሻ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ላይ መስማማታቸው ተመልክቷል።

    በሊባኖስ ጦርነቱን ማስቆም የሚቻልበት መንገድ መዘርጋት ላይም መግባባት ላይ መደረሱን አሸማጋዮቹ አስታውቀዋል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ድርድሩን “ትልቅ ለውጥ” የታየበት እንደሆነ በኤክስ ገጻቸው ተናግረዋል።

    “በነዳጅ እና በፔትሮኬሚካል የወጪ ንግድ ላይ የተጣለው እገዳተነስቷል” ሲሉም አክለዋል።

    የኢራን እና አሜሪካ የመጀመሪያ ቀን ድርድር

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

  6. በኢራን እና አሜሪካ የመጀመሪያ ቀን ድርድር ምን ጉዳዮች ተነሱ?

    ሉስርኔ በተባለ ሐይቅ የተካሄደው ድርድር አወንታዊ እና ገንቢ ድባብ እንደታየበት ተገልጿል

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ሉስርኔ በተባለ ሐይቅ የተካሄደው ድርድር አወንታዊ እና ገንቢ ድባብ እንደታየበት ተገልጿል

    አሸማጋዮቹ ኳታር እና ፓኪስታን በጋራ ባወጡት መግለጫ የድርድር ሒደቱን የሚከታተል የፖለቲካ ኮሚቴ እና በሊባኖስ ጦርነት የሚያስቆም ቡድን መመሥረቱን አስታውቀዋል።

    “ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ኮሚቴ በ60 ቀናት ውስጥ የመጨረሻ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ላይ ተስማምቷል” ብለዋል።

    የአሜሪካ እና ኢራን ድርድር በስዊትዘርላንድ የተካሄደ ሲሆን፤ ኳታር እና ፓኪስታን በጋራ ባወጡት መግለጫ የመጀመሪያውን ቀን ድርድር ነጥቦችን እንደሚከተለው ዘርዝረዋል፦

    • ሉስርኔ በተባለ ሐይቅ የተካሄደው ድርድር አወንታዊ እና ገንቢ ድባብ እንደታየበት ተገልጿል።
    • ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ኮሚቴ ድርድሩን በዋናነት የሚከታተል ይሆናል።
    • ዋነኛ ተደራዳሪዎች የደረሱበትን ለኮሚቴው ያስታውቃሉ።
    • ኮሚቴው ግጭትን ለማስቆም ከተቋቋመው ቡድን ጋር በመሆን የኒውክሌር፣ የማዕቀብ እና የመግባቢያ ሰነዱ አተገባበርን ይከታተላል።
    • በስምምነቱ አንቀጽ 5 መሠረት የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት እንዲሁም በተደራዳሪዎች መካከል አለመግባባት እንዳይኖር የንግግር መስመር ክፍት ይሆናል።
    • ግጭትን ለማስቆም የተቋቋመው ቡድን በሊባኖስ ድርድር እንዲደረግ እና ወታደራዊ ግጭት እንዲቆም ያደርጋል።
  7. ኢራን የነዳጅ ማዕቀብ እንደተነሳላት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገለጹ

    ድርድር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ “በነዳጅ እና በፔትሮኬሚካል የወጪ ንግድ ላይ የተጣለው እገዳ መነሳቱን” ገለጹ።

    ከድፍድፍ ነዳጅ እና ከተፈጥሮ ጋዝ የሚገኘው ፔትሮኬሚካል የወጪ ንግድ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ከመነሳቱ በተጨማሪ በኢራን የባሕር መተላለፊያ ላይ ተጥሎ የነበረው ክልከላ መነሳቱንም አክለዋል።

    በተጨማሪም ማዕቀብ ተጥሎባቸው የነበሩ “የተወሰኑ የኢራን ሃብቶች እንደተለቀቁ” ተናግረዋል።

    የማዕቀቦች መነሳት የኢራንን የምጣኔ ሃብት መልሶ ግንባታ እንደሚደግፍ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል።

    “በሊባኖስ ያለው ጦርነት እንዲቆም” የኳታር እና ፓኪስታን ልዑካን ላበረከቱት አስተዋጽኦም አመስግነዋል።

    ኢራን እና አሜሪካ የተስማሙበት መግባቢያ ሰነድ አንቀጽ 1፣ 10 እና 11 ለድርድሩ ዋነኛ መነሻ መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

    አንቀጽ 1- አሜሪካ፣ ኢራን እና አጋሮቻቸው ሊባኖስን ጨምሮ በሁሉም ግንባሮች “በአፋጣኝ እና በዘላቂነት” ተኩስ ማቆም አለባቸው ይላል።

    አንቀጽ 10- ዋሽንግተን ለነዳጅ ኤክስፖርት እና ለፔትሮሊየም ምርቶች አስፈላጊውን ፈቃድ እንድትሰጥ እና ባንክ እና መጓጓዣን ጨምሮ በሌሎችም ዘርፎች ውሳኔው እንደሚተገበር ይገልጻል።

    አንቀጽ 11- ማዕቀብ የተጣለባቸውን የኢራን ሃብቶች ይመለከታል።

  8. የአሜሪካ እና የኢራን የመጀመሪያ ዙር ድርድር ‘አበረታች ውጤት’ እንዳሳየ ተገለጸ

    የአሜሪካ ልዑካን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካ እና የኢራን የመጀመሪያ ዙር ድርድር “አበረታች ውጤት” እንዳሳየ አሸማጋዮቹ ኳታር እና ፓኪስታን አስታወቁ።

    ድርድሩ ትናንት እሑድ በስዊትዘርላንድ ተጀምሯል። ሁለቱ አገራት ከስምምነት ላይ የደረሱት ባለፈው ሳምንት እንደነበር ይታወሳል።

    ኳታር እና ፓኪስታን ዛሬ ሰኞ በጋራ ባወጡት መግለጫ “ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ኮሚቴ በ60 ቀናት ውስጥ የመጨረሻ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ላይ ተስማምቷል” ብለዋል።

    በያዝነው ሳምንት የቴክኒክ ጉዳዮችን በተመለከተ ውይይት እንደሚቀጥል በመግለጫው ተመልክቷል።

    በድርድሩ ተሳታፊ የሆኑ የአሜሪካ ዲፕሎማት እንደተናገሩት ውይይቱ “ከኢራን የወጡ አወዛጋቢ መልዕክቶችን ማጥራት ላይ ያተኮረ ነው”።

    በተጨማሪም በሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነትን ማስተግበር እና የሆርሙዝ ወሽመጥን ማስከፈት የውይይቱ ግቦች መሆናቸውን ገልጸዋል።

    ተደራዳሪዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters