ቀጥታ, ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደር ጣልቃ መግባት ውጥረቱን እንደሚያባብስ አስጠነቀቀች

በኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደር ውስጥ ማንኛውም ጣልቃ ገብነት ውጥረቱን እንደሚያባብስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ተናግረዋል። በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል እያለፈ የነበረ በፓናማ የተመዘገበ መርከብ ትናንት ቅዳሜ ጥቃት ከደረሰበት በኋላ አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት ፈጽማለች። የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በአጸፋ ምላሽ በኩዌት እና ባሕሬን በሚገኙ የአሜሪካ መሠረተ ልማቶች ላይ የድሮን እና ሚሳዔል ጥቃቶች ማድረሱን ገልጿል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የነዳጅ ዋጋ ከኢራን ጦርነት ወዲህ ባልታየ መጠን ቀነሰ

    ነዳጅ የሚቀዳ ግለሰብ

    የፎቶው ባለመብት, The Dallas Morning News via Getty Images

    መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መጓጓዝ መቀጠላቸውን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ከኢራን ጦርነት ወዲህ ባልታየ መጠን ቀነሰ።

    የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል ወደ 72.48 ዶላር ወርዷል። ይህም አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ ጥቃት ከሰነዘሩበት ቀን በፊት የነበረው ዋጋ ነው።

    ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመዝጋቷ ባለፉት ወራት የነዳጅ ዋጋ አሻቅቦ ነበር።

    ኢራን እና አሜሪካ የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረሙበት ዕለት አንስቶ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ እያሽቆለቆለ መጥቷል።

    የቴህራን እና ዋሽንግተን ልዑካን በስዊትዘርላንድ ውይይት ካደረጉ በኋላ አሜሪካ የኢራን የነዳጅ የወጪ ንግድ ላይ ጥላ የነበረውን ማዕቀብ አላልታለች።

    ስምምነት ከተፈራሙ በኋላ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚተላለፉ መርከቦች ቁጥር ጨምሯል።

    ድፍድር ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ እንዲሁም ማዳበሪያ እና ሌሎችም ሸቀጦች የጫኑ መርከቦች እየተላለፉ ይገኛሉ።

  2. ፊሊፒንስ በትምህርት ቤት ተኩስ በመክፈት የተጠረጠረ ታዳጊ ሲጫወት የነበረውን ጌም አገደች

    ‘ጎርቦክስ’ የተባለው ጌም

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በፊሊፒንስ ባልተለመደ ሁኔታ ትምህርት ቤት ውስጥ ተኩስ በመክፈት የተጠረጠረ ታዳጊ ሲጫወት የነበረው ‘ጎርቦክስ’ የተባለው ጌም ላይ ጊዜያዊ እገዳ ተጣለ።

    ያለፈው ሰኞ በተከፈተው ተኩስ ሦስት ተማሪዎች ሲገደሉ 20 የሚደርሱ ቆስለዋል።

    ተጠርጣሪዎቹ የ15 እና 14 ዓመት ታዳጊዎች ሲሆኑ፤ ሽጉጥ ይዘው ወደ ክፍል መግባታቸው ተዘግቧል።

    የ14 ዓመቱ ተጠርጣሪ ‘ጎርቦክስ’ የተባለውን ጌም ይጫወት እንደነበር ተገልጿል።

    ጉግል ፕለይ ላይ ጌሙ የተገለጸው “ተጫዋቾች ያሻቸውን ነገር ማውደም ይችላሉ። በመሣሪያ ወይም በፈንጂ በጭካኔ የተሞካ ፍልሚያ ያደርጋሉ” በሚል ነው።

    የፊሊፒንስ የሳይበር ደኅንነት ተቋም “የበይነ መረብ ገጹ ለአሰቃቂው ክስተት አስተዋጽኦ አድርጎ ሊሆን ይችላል” ብሏል።

    ጌሙ በጊዜያዊነት መታገዱ “ለተጠርጣሪዎቹ ድርጊት ምን ያህል ሚና እንደነበረው ለመመርመር እንደሚረዳም” ተገልጿል።

    ቢቢሲ ጌሙን ከሚያመርተው የጀርመኑ ኤፍቱጌምስ ኩባንያ አስተያየት ጠይቋል። በነውጠኛ ባህሪ እና በቪድዮ ጌም መካከል ትስስር መኖሩን የሚያረጋግጡ ሳይንሳዊ ምርምሮች የሉም።

  3. በኢራን ጦርነት ኔቶ "ተጠያቂ እንዲደረግ" የቴህራን ባለሥልጣን ጠየቁ

    ኢስማኤል ባጋይ

    የፎቶው ባለመብት, LightRocket via Getty

    የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ዋና ጸሐፊ የሰጡትን አስተያየት ተከትሎ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ “ኔቶ ተጠያቂ መደረግ አለበት” አሉ።

    ዋና ጸሐፊው ማርክ ሩተ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ “ኔቶ፤ የተባበሩት መንግሥታት አባል በሆነች አገር ላይ በተፈጸመ ሕገ ወጥ ጦርነት መሳተፉን በግልጽ አምነዋል” ሲሉ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

    “ይህም ዓለም አቀፍ ሕግን እንዲሁም የተመድን ስምምነት የሚጥስ” እንደሆነ አክለዋል።

    ኔቶ እና አባል አገራቱ “ተጠያቂ መደረግ አለባቸው” ሲሉም ኢስማኤል ባጋይ አሳስበዋል።

    ማርክ ሩተ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኔቶ በበቂ ሁኔታ አሜሪካን አልደገፈም ሲሉ ላቀረቡት ክስ ምላሽ ሰጥተዋል።

    ማርክ ለትራምፕ በሰጡት ምላሽ “አውሮፓ የአሜሪካ ኃያልነት መሳያ ነው” ብለዋል።

    ጣሊያን እና ሮማኒያን በዋናነት ጠቅሰው በኢራን ጦርነት አሜሪካን መደገፋቸውን ተናግረዋል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ይሄንን ንግግር መነሻ አድርገው “በኢራናውያን ላይ መጠነ ሰፊ ወንጀል ሲፈጸም ለምን እንዳገዙ ለሕዝባቸው እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማስረዳት አለባቸው” ብለዋል።

    በቴህራን፣ ሚንዳብ፣ ላማርድ፣ ኢስፋሀን፣ ሳንዳጅ፣ ሀሜንዳን እና ሌሎችም የኢራን ከተሞች የተፈጠረውን በመጥቀስም ኔቶ ኃላፊነት እንዲወስድ አሳስበዋል።

    ከኔቶ ዋና ጸሐፊ አስተያየት በኋላ የጣሊያን መከላከያ ሚኒስቴር “የተዛባ ምሥል የሚሰጥ” ንግግር ነው ብለዋል።

    ጣሊያን የሰጠችው “የቴክኒክ፣ ሎጅስቲክ እና ወታደራዊ ያልሆነ ድጋፍ” እንደሆነም ተናግረዋል።

    ከአሜሪካ ጋር ካላቸው የትብብር ማዕቀፍ ውጭ የሆነ ጥያቄ ቀርቦ ከሆነ “ጣሊያን ፈቃዷን እንዳልሰጠች” አክለዋል።

    የአሜሪካ ጦር የጣሊያንን ወታደራዊ ሰፈሮች እንዲጠቀም እንዳልፈቀዱም ጠቅሰዋል።

  4. ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ለሚያልፉ መርከቦች ማሳሰቢያ አወጣች

    መርከቦች በሆርሙዝ ላይ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦች ሁሉ ለደኅንነታቸው ሲባል መጠቀም ያለባቸው በኢራን በተፈቀዱ ቦታዎች በኩል እንደሆነ እና እንቅስቃሴያቸውንም ቀድመው ማሳወቅ እንዳለባቸው የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ አስታወቀ።

    ዘቡ ይህንን መግለጫ ያወጣው በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ አዲስ የመርከቦች መተላለፊያ መስመር መከፈቱን የሚያመለክቱ ዘገባዎች መውጣታቸውን ተከትሎ ነው።

    ለወራት መተለላፊያ አጥተው ለቆዩት መርከቦች ተከፈተ የተባለው መስመር “ተቀባይነት የሌለው ሙሉ ለሙሉ ለመርከቦቹ አደገኛ ነው” በማለት አስጠንቅቋል።

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ ባወጣው መግለጫ “በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ለማለፍ የተፈቀደበት መስመር በኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ የተገለጸው ብቻ ነው” መሆኑን በመግለጽ መርከቦች “ቻናል 16 በተባለው መስመር በኩል” ብቻ እና ከኢራን ጦር ኃይል ጋር በመነጋገር መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

    ረቡዕ ዕለት የሆርሙዝ ወሽመጥ ተጎራባች የሆነችው ኦማን ለረጅም ጊዜ መውጫ አጥተው የቆዩ መርከቦችን እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ አዲስ የባሕር መስመር መክፈቷን አሳውቃ የነበረ ቢሆንም፣ የኢራን አብዮታዊ ዘብ ግን በመግለጫው ስለኦማን አዲስ የባሕር ላይ መስመር በቀጥታ ያለው ነገር የለም።

  5. የተመድ የአቶሚክ ኤነርጂ ኃላፊ በስምምነቱ መሠረት ተቆጣጣሪዎች የኢራንን የኒውክሌር ጣቢያዎች ይጎበኛሉ አሉ

    የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤነርጂ ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤነርጂ ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ

    የዓለም አቀፉ የኒውክሌር ተቋም ኃላፊ፤ አሜሪካ እና ኢራን በደረሱት የመጀመሪያ ደረጃ የሰላም ስምምነት መሠረት ተቆጣጣሪዎች በቴህራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ተገኝተው ምርመራ እንደሚያደርጉ ተናገሩ።

    የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤነርጂ ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ ጃፓን ውስጥ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ “በእርግጥም ምርመራ ይካሄዳል” ብለዋል። የሚካሄድበትን “መንገድ፣ ቀን፣ ሂደት፣ ቦታ [በተመለከተ] እንሰራለን፤ በጣም በቅርቡ” ሲሉም አክለዋል።

    የኢራንን እጅግ የበለጸገ ዩራኒየም የመበረዝ ተግባር በዓለም አቀፉ የኒውክሌር ተቋም ቁጥጥር እንደሚካሄድ ባለፈው ሳምንት የተፈረመው ስምምነት ላይ “በግልጽ” እንደሰፈረም ገልጸዋል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ግን ጉዳት የደረሰባቸው የአገሪቱ የኒውክሌር ተቋማት እና የኒውክሌር ቁሶችን የተመለከተ ሥራ ሊከናወን የሚችለው ከአሜሪካ ጋር በሚደረስ የመጨረሻ ስምምነት ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ እንደሚሆን ተናግረዋል።

    የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤነርጂ ዋና ዳይሬክተር ይህንን አስተያየት የሰጡት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ስለ ስምምነቱ ለመወያየት የባሕረ ሰላጤው አገራትን እየጎበኙ ባለበት ወቅት ነው።

    አሜሪካ እና ኢራን የተፈራረሙት የመጀመሪያ ስምምነት፤ ቴህራን በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚደረግ የመርከቦች ጉዞን እንደምትፈቅድ፤ ዋሽንግተን ደግሞ በኢራን ወደቦች ላይ የጣለችውን የጉዞ እገዳ እንደምታነሳ ያትታል።

    ባለፉት ቀናት የተመድ የኒውክሌር ተቆጣጣሪዎች ወደ ቴህራን የመግባታቸው ጉዳይ ላይ አሜሪካ እና ኢራን የተቃረነ አስተያየት ሰጥተዋል።

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ በስዊትዘርላንድ ከኢራን ዋና ተደራዳሪ ጋር ካደረጉት ንግግር በኋላ ቴህራን “የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤነርጂ ተቆጣጣሪዎች ወደ አገሪቱ እንዲመለሱ ለመጋበዝ ተስማምታለች” ሲሉ ተደምጠዋል።

    በቀጣዩ ቀን አስተያየት የሰጡት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ግን በጉዳዩ ላይ የተደረገ “ምንም ዝርዝር ውይይት” እንደሌለ ተናግረዋል።

    ኢራን፤ የተቋሙ ተቆጣጣሪዎች ባለፈው ዓመት ከእስራኤል ጋር በተደረገው የ12 ቀናት ጦርነት ድብደባ ወደተፈጸመባቸው የኒውክሌር ተቋማት እንዲሄዱ የማድረግ እቅድ እንደሌላትም ገልጸዋል።

  6. የአሜሪካ እና ኢራን ቴክኒካዊ ንግግር በሚቀጥለው ሳምንት ድጋሚ እንደሚጀመር ተገለጸ

    የሚጨባበጡ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካ እና ኢራን ቴክኒካዊ ንግግር በሚቀጥለው ሳምንት በድጋሚ እንደሚጀመር የአሸማጋይዋ ፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

    “ምናልባት ማክሰኞ” ዕለት ይጀመራል የተባለው ቀጣዩ ቴክኒካዊ ንግግር የሚካሄድበት ቦታ ግን ይፋ አልተደረገም።

    ስዊትዘርላድ ውስጥ የተካሄደው የሁለቱ አገራት የመጀመሪያው ዙር ንግግር እሁድ ዕለት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ አገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስዊዘርላንድን ለቅቀው ሄደዋል።

    የቴክኒካል ልዑካኖቻቸው ግን ሰኞ ዕለትም ንግግር ማድረግ ቀጥለው ነበር።

    ማክሰኞ ዕለት የኢራን የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ካዜም ኸሪባባዲ የመጀመሪያው ዙር የቴክኒካል ንግግር መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

    ተደራዳሪዎቹ “የማዕቀብ መነሳት”፣ “የኒውክሌር ጉዳይ”፣ “የኢኮኖሚ መልሶ ግንባታ እና ልማት” እንዲሁም “የቁጥጥር እና ትግበራ” ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ አራት ቡድኖችን ማቋቋማቸውንም ገልጸዋል።

    እነዚህ የስራ ቡድኖች አሜሪካ እና ኢራን የፈረሙትን የመግባቢያ ስምምነት ቴክኒካዊ ዝርዝር ጉዳዮች አፈጻጸምን የመከታተል ኃላፊነት ይኖራቸዋል።

  7. ፈረንሳይ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢቦላ የተያዘ ሰው መገኘቱን አረጋገጠች

    የሕክምና ጓንት ያደረገ የጤና ባለሙያ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ የሰብአዊ ረድኤት ተልዕኮ ላይ ሲሳተፍ ቆይቶ የተመለሰ አንድ ዶክተር ላይ የኢቦላ ቫይረስ መገኘቱን የፈረንሳይ መንግሥት አስታወቀ። የሕክምና ባለሙያው ፈረንሳይ ውስጥ በኢቦላ መያዙ የተረጋገጠ የመጀመሪያው ሰው ሆኗል።

    የፈረንሳይ ጤና ሚኒስቴር ዛሬ ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፤ ዶክተሩ "ወዲያውኑ ወደ ልዩ የህክምና ተቋም መግባቱን" እና አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።

    ዴሞክራቲክ ኮንጎ የኢቦላ ወረርሽኝ መከሰቱን ይፋ ያደረገችው ባለፈው ወር ቢሆንም፤ ባለሙያዎች በሽታው መከሰቱ ከመታወጁ ሳምንታት አስቀድሞ ሲሰራጭ እንደነበረ ያምናሉ።

    በማዕከላዊ አፍሪካዊቷ አገር ውስጥ በተከሰተው በሽታ ምክንያት ከ260 በላይ ሰዎች እንደሞቱ ተረጋግጧል። አንድ ሺህ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል።

    ባለፈው ወር ዴሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ በበሽታው የተያዘ ሰው ጀርመን ውስጥ ሕክምና ሲያገኝ የነበረ ቢሆንም በአውሮፓው የኢቦላ መገኘቱ ሲረጋገጠ የአሁኑ የመጀመሪያው ነው።

    የኮንጎ ጎረቤት የሆነችው ዩጋንዳም በኢቦላ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን አረጋግጣለች። የዓለም ጤና ድርጅት ዩጋንዳ ውስጥ 20 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን እና ሁለት ሰዎች መሞታቸውን እንደተረጋገጠ ገልጿል።

    የፈረንሳይ ጤና ሚኒስቴር በዛሬው መግለጫው በሕዝቡ ውስጥ በሽታው የመሠራጨቱ የስጋት መጠን “እጅግ ዝቅተኛ” መሆን በአጽንኦት አንስቷል።

    ባለሥልጣናት ከዶክተሩ ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ለመለየት እየሰሩ መሆኑንም አክሏል።

    የጤና ባለሙያዎች ከሰውነት በሚወጡ ፈሳሾች ለሚተላለፈው ኢቦላ የበለጠ ተጋላጭነት አላቸው።

    አሁን የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ ቡንዲቡግዮ በተባለው የቫይረሱ ዝርያ የመጣ ሲሆን ይህ ዝርያ እስካሁን ክትባት አልተገኘለትም።

  8. ጊቤ የተባለችው የኢትዮጵያ መርከብ ከሆርሙዝ ወሽመጥ ወጥታ ወደ ጂቡቲ ጉዞ ጀመረች

    ጊቤ መርከብ እና ሠራተኞቿ

    የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Shipping and Logistics

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መተላለፊያ አጥታ የነበረችው ጊቤ የተባለችው የኢትዮጵያ መርከብ ጉዞ መጀመሯ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አስታወቀ።

    ባለፈው የካቲት ወር መጨረሻ ላይ በባሕረ ሰላጤው ጦርነት ሲጀመር ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ለወራት ዘግታው ቆይታለች።

    ወሽመጡ በቀን አስከ 140 ግዙፍ የጭነት መርከቦች የሚተላለፉበት ወሳኝ መስመር ነበር።

    መተላለፊያው በመዘጋቱ የኢትዮጵያን ጨምሮ 1,150 የጭነት መርከቦች እና ከ20 ሺህ በላይ የመርከቦቹ ሠራtኞች ለወራት ቆመው ለመጠበቅ ተገደዋል።

    ሁሉም መርከቦቹ በአጠቃላይ 125 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ጭነት ይዘው ነበር የቆሙት።

    በጦርነቱ ወቅት ለማለፍ የሞከሩ 32 የጭነት መርከቦች በሚሳዔል ወይም በድሮን ተመትተዋል። በዚህም ከመርከቦቹ ሠራተኞች 10 ሰዎች መሞታቸው እና ሌሎች በርካታ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተረጋግጧል።

    ኢራን እና አሜሪካ ጦርነቱን ለማቆም ከተስማሙ በኋላ ሆርሙዝ እንደገና ክፍት ተደርጓል። ለወራት መተላለፊያ አጥተው ከነጭነታቸው የቆሙት መርከቦች አሁን ወደየመዳረሻቸው ጉዞ ጀምረዋል።

    ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያዋ መርከብ 'ኤምቪ ጊቤ' ጉዞ መጀመሯን የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አስታውቋል።

    የኢትዮጵያ መርከብ በኦማን ገልፍ በኩል ወደ ጂቡቲ በመጓዝ ላይ መሆኗ ተገልጿል። እሁድ ሰኔ 21 ምሽት 2:00 ሰዓት ጂቡቲ ወደብ እንደምትደርስም እየተጠበቀ ነው።

  9. በኬንያ ታዳጊዎች ከሞቱበት የእሳት አደጋ ጋር በተያያዘ ተማሪዎች ሊከሰሱ ነው

    ክስ የሚመሠረትባቸው ተማሪዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ባለፈው ወር በኬንያ ትምህርት ቤት ከተነሳው እና ታዳጊዎች ከሞቱበት የእሳት አደጋ ጋር በተያያዘ ተማሪዎች ላይ ክስ ለመመሥረት እየተዘጋጀ መሆኑን የአገሪቱ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ።

    ከ15 እስከ 18 ዓመት የሚሆናቸው አስራ ስድስት ተማሪዎች በእሳት አደጋው ምክንያት መሞታቸው ይታወሳል። ሌሎች ብዙ ተማሪዎች ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ዐቃቤ ሕግ እንዳለው በርካታ ተማሪዎች በግድያ ወንጀል ይከሰሳሉ።

    ከመዲናዋ ናይሮቢ በ120 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ጊልጊል ከተማ በሚገኝ የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ በተማሪዎች መኝታ ክፍል እሳት መነሳቱ ሕዝቡን አስቆጥቷል።

    ስምንት ተማሪዎች በእሳት አደጋው እጃቸው አለበት በሚል በፖሊስ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

    ተማሪዎቹ ፍራሽ በማቃጠል እሳቱ እንዲስፋፋ ማድረጋቸው ተገልጿል።

    እሳቱ 135 ተደራራቢ አልጋዎች ባሉበት መኝታ ክፍል የመጀመሪያ ሕንጻ ላይ ነበር የተነሳው። የድንገተኛ ጊዜ በር ለመክፈት ያልቻሉት በሕንጻው የሚኖሩት 202 ተማሪዎች በአንድ አቅጣጫ ብቻ በሚገኝ በር ለመውጣት ተገድደዋል።

    ፖሊስ እንዳለው በተማሪዎች እና በሠራተኞች ላይ ምርመራ ከተደረገ፣ የደኅንነት ካሜራ ተንቀሳቃሽ ምሥል ከተፈተሸ እና የፎረንሲክ ምርመራ ከተደረገ በኋላ ስምንት ተማሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

    ተማሪዎቹ በግድያ ወንጀል ተከስሰው ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡም ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።

  10. የሊባኖስን ጦርነት ማስቆም የኢራንን ጦርነት የማስቆም ያህል ዋጋ እንዳለው የቴህራን ባለሥልጣን ተናገሩ

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ መሐመድ ባጋር ጋባሊፍ

    የፎቶው ባለመብት, Tasnim News Agency via Reuters

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ መሐመድ ባጋር ጋባሊፍ “በሊባኖስ ያለውን ጦርነት ማስቆም የኢራንን ጦርነት የማስቆም ያህል ዋጋ አለው” ሲሉ ተናገሩ።

    በአዘርባጃን፣ ባኩ እየተካሄደ ባለው የእስላዊ ትብብር ተቋማት የምክር ቤት ኅብረት ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር “ለእኛ የሊባኖስ የተኩስ አቁም የኢራን የተኩስ አቁም ያህል ዋጋ አለው። በተጨማሪም በሊባኖስ ያለውን ጦርነት ማስቆም የኢራንን ጦርነት የማስቆም ያህል ዋጋ አለው” ብለዋል።

    ኢራን እና አሜሪካ የፈረሙት የመግባቢያ ሰነድ ሊባኖስን ጨምሮ በሁሉም ግንባሮች ውጊያ ማቆምን ያካትታል።

    ዋነኛው ተደራዳሪ የሆኑት የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ መሐመድ ባጋር ጋባሊፍ “የኢስላማባድ ስምምነት የአሜሪካን ሽንፈት አውጇል” ብለዋል።

    የጦርነቱ ዓላማ “በቀጣናው ስትራቴጂያዊ የአሰላለፍ ለውጥ ለማምጣት እና ይህንንም በነጻ አገር ላይ መጫን” እንደሆነም ተናግረዋል።

    ከቀጣናው “የውጭ ኃይሎችን ማስወጣት ስትራቴጂያዊ ድል ነው” ሲሉም አክለዋል።

    ኢራን እርስ በርስ በመከባበር እና ጣልቃ ባለመግባት መርህ ከሙስሊም አገራት ጋር ለመተባበር ዝግጁ መሆኗንም ገልጸዋል።

  11. አሜሪካ እና እስራኤል ደቡብ ሊባኖስን ለአገሪቱ ጦር የማስረከብ ዕቅድ ማውጣታቸው ተዘገበ

    ትራምፕ እና ኔታንያሁ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አሜሪካ ድጋፏን በሰጠችው ዕቅድ መሠረት እስራኤል እና ሊባኖስ፤ የደቡብ ሊባኖስ አስተዳደርን ለአገሪቱ ጦር ለማስረከብ ማሰባቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።

    ሮይተርስ ከፍተኛ የእስራኤል ባለሥልጣናት የሆኑ ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ በዚህ ዕቅድ ውስጥ የሚካተቱ የሊባኖስ ኃይሎች ከአሜሪካ ሥልጠና ይሰጣቸዋል።

    ከሄዝቦላህ ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው ለማረጋገጥም የደኅንነት ማጣራት ይደረጋል።

    የዜና ወኪሉ የጠቀሳቸው ምንጮች እንዳሉት፤ በደቡብ ሊባኖስ ያሉ አካባቢዎች ለአገሪቱ ጦር ተላልፈው እስከሚሰጡ ድረስ እስራኤል ቀጣናውን እየተቆጣጠረች ትቆያለች።

    አሜሪካ እና እስራኤል በይፋ አስተያየታቸውን አልሰጡም። እስራኤል እና ሊባኖስ ዛሬ ረቡዕ በዋሽንግተን ውይይት እያደረጉ ይገኛሉ።

  12. ተመድ ከሆርሙዝ ወሽመጥ 11 ሺህ መርከበኞችን እንደሚያስወጣ አስታወቀ

    የሆርሙዝ ወሽመጥ

    የፎቶው ባለመብት, Atta Kenare / Getty Images

    የተባበሩት መንግሥታት ማሪታይም ባለሥልጣን በኢራን ጦርነት ሳቢያ በሆርሙዝ ወሽመጥ የቀሩ 11 ሺህ መርከበኞችን እንደሚያስወጣ አስታወቀ።

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ በከፈቱት ጦርነት ሳቢያ መርከበኞቹ ከባሕረ ሰላጤው አካባቢ ለመውጣት ሳይችሉ ቆይተዋል።

    የተመድ ማሪታይም ባለሥልጣን (አይኤምኦ) ዋና ጸሐፊ አርሴኒዮ ዶሚኒገዝ እንደተናገሩት ከኢራን፣ አሜሪካ፣ ኦማን እና ሌሎችም የባሕረ ሰላጤው አገራት እንዲሁም የማሪታይም ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር “መጠነ ሰፊ ኦፕሬሽን” ይካሄዳል።

    “ደኅንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ማስወጣት የምንችልበት መንገድ ዘርግተናል” ብለዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን የመግባቢያ ሰነድ ላይ ፊርማቸውን ቢያኖሩም ዝርዝሩን በተመለከተ የሚቃረኑ መረጃዎች እያወጡ ይገኛሉ።

    በመግባቢያ ሰነዱ መሠረት ዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ በኢራን ፍተሻ ማድረግ እንደሚችል ዋሽንግተን ብትገልጽም፤ ቴህራን አስተባብላለች።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን ምንም ዓይነት ክፍያ መጠየቅ እንደማትችል ገልጸዋል።

    ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ክፍያ መጠየቅ የኢራን እና አሜሪካን ስምምነት የሚጥስ እና ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር የሚቃረን ነው።

    ኢራን በበኩሏ ከኦማን ጋራ ባወጣችው መግለጫ የሆርሙዝ ወሽመጥ የሚገኝበትወሳኝ የባሕር መተላለፊያላይ ሉዓላዊ መብት ያላቸው ሁለቱ አገራት መሆናቸውን አስታውቃለች።

    አገራቱ ጥምር ኮሚቴ አቋቁመው የሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደር እና መርከቦች ለመተላለፍ የሚፈጽሙትን ክፍያ ጉዳይ በጋራ እንደሚመለከቱም ገልጸዋል።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

  13. ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦችን ማስከፈል አትችልም ስትል አሜሪካ አስጠነቀቀች

    መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ከአሜሪካ ጋር በተደረሰው ስምምነት ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን ምንም ዓይነት ክፍያ መጠየቅ እንደማትችል እና ይህንን የምታደርግ ከሆነ ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር የሚቃረን ነው ሲሉ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናገሩ።

    ማርኮ ሩቢዮ ይህንን ያሉት ኢራን እና ኦማን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ስለሚደረጉ የባሕር ላይ ጉዞዎች እና ከሚሰጠው አገለግሎት ጋር ያሉ ወጪዎችን በተመለከተ ውይይት ማድረቸጋውን ተከትሎ ነው።

    ሁለቱ አገራት ኦማን ውስጥ ካደረጉት ውይይት በኋላ ባወጡት የጋራ መግለጫ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮቻቸው አማካኝነት የጋራ ግብረ ኃይል በመመሥረት ከተጎራባች አገራት እና ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር ምክክር እንደሚያካሂዱ ገልጸዋል።

    ኢራን እና ኦማን ከአሜሪካ ጋር በተደረሰው ስምምነት ትግበራ ላይ ለመመካከር ባደረጉት ውይይት አገራቱ በወሳኙ የባሕር መተለላፊያ ላይ ያላቸው ሉዓላዊነት ተከብሮ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን ደኅንነት ለማረጋገጥ ያላቸውን ቁርጠኝነት ለመግለጽ የታለመ ነው።

    አሜሪካ እና አስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ከከፈቱበት ከየካቲት ወር መጨረሻ አንስቶ እስካለፈው ሳምንት ድረስ የሆርሙዝ ወሽመጥ በኢራን ዝግ ተደርጎ የቆየ ሲሆን፣ አሜሪካ ደግሞ በኢራን ላይ የባሕር ላይ እገዳ ጥላ ቆይታለች።

  14. ኢራን እና ኦማን የሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደር እና ክፍያን በጋራ እንደሚወስኑ አስታወቁ

    የሆርሙዝ ወሽመጥ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ኢራን እና ኦማን በጋራ ባወጡት መግለጫ የሆርሙዝ ወሽመጥ የሚገኝበት ወሳኝ የባሕር መተላለፊያ ላይ ሉዓላዊ መብት እንዳላቸው ተናገሩ።

    በመግለጫው የሆርሙዝ ወሽመጥ ደኅንነቱ ተጠብቆ ዓለም አቀፍ የመርከቦች መተለላፊያ ሆኖ እንዲቀጥል በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ እንደሆኑም አስታውቀዋል።

    በቀጣይ የሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደርን እና መርከቦች ለመተላለፊ የሚፈጽሙትን ክፍያ ጉዳይ በጥምር ኮሚቴ አማካኝነት እንደሚመለከቱም ገልጸዋል።

    የሁለቱ አገራት መሪዎች በኦማን ዋና ከተማ ሙስካት ከተወያዩ በኋላ ነው መግለጫውን ያወጡት።

    በስዊትዘርላንድ የነበሩት የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት፤ የእስላማዊ ሪፐብሊክ የፓርላማ አፈ ጉባዔ መሐመድ ባጋር ጋሊባፍ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ ወደ ኦማን አቅንተው ከንጉሥ ሐቲሀም ቢን ታሪቂ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር ቡሳዲ ጋር ተወያይተዋል።

  15. እስራኤል የኢንተርኔት መገናኛዎችን በድብቅ ወደ ኢራን ማስገባቷን የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ተናገሩ

    የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት
    የምስሉ መግለጫ, የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት

    ሕዝባዊ ተቃውሞ ሲቀሰቀስ መንግሥት የኢንተርኔት አገልግሎት በሚያቋርጥበት ጊዜ የሚሠሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የኢንተርኔት መገናኛ መሳሪያዎችን ከዓመታት በፊት እስራኤል ወደ ኢራን አስርጋ ለማስገባት መሥራቷን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ተናገሩ።

    የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት በሥልጣን ላይ ሳሉ ኢራናውያን ተቃዋሚዎች ኢንተርኔት በሚቋረጥ ጊዜ ግንኙነታቸውን ለማስቀጠል የሚያስችሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የስታርሊንክ የኢንተርኔት መቀበያዎችን በድብቅ ወደ ኢራን ለማስገባት ያለመ ዕቅድ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

    ቤኔት ኢየሩሳሌም ውስጥ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት፤ ዓላማቸው የተቃዋሚዎችን ግንኙነት እና እንቅስቃሴ ማቀናጀት በማስቻል የኢራንን መንግሥት ከሥልጣን እንዲወገድ ማድረግ ነበር።

    "በሚያሳዝን ሁኔታ አሁን ያለው [የኔታኒያሁ] መንግሥት እየተካሄደ የነበረውን ፕሮግራም በማስቆሙ ኢራን ውስጥ ተቃውሞው ሲቀሰቀስ አስፈላጊው የግንኙነት መሳሪያ በቦታው አልነበረም” ሲሉ ቁጭታቸውን ገልጸዋል።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ጽህፈት ቤት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት ለሰነዘሩት አስተያየት እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።

    እንዲሁም የስታርሊንክ ኢንተርኔት መገናኛ አቅራቢ ድርጅት የሆነው ስፔስኤክስም በጉዳዩ ላይ ያለው ነገር የለም።

    ናፍታሊ ቤኔት ከእስራኤል ተቃዋሚዎች መካከል ተጠቃሹ ሲሆኑ በመጪው ምርጫ ዋነኛው ዕጩ ሊሆኑ ይችላሉ እየተባለ ነው። ወደ ሥልጣን የሚመለሱ ከሆነ የኢራንን መንግሥት ለማዳከም እንደሚሠሩም ተናግረዋል።

    ለዚህም በኢራን ላይ የሚወሰደው እርምጃ ከቅጥተኛ ወታደራዊ ጥቃት ባሻገር “የኢኮኖሚ እና የኢንዱስትሪ አሻጥሮችንም” እንደሚያካትቱ ገልጸዋል።

    ናፍታሊ ቤኔት ከአራት ዓመት በፊት ለአንድ ዓመት ያህል ቤንያሚን ኔታኒያሁን ለአጭር ጊዜ ከሥልጣን ያስወገደውን የቀኝ እና የግራ ክንፍ እንዲሁም የመሃል ፓርቲዎች ጥምር መንግሥትን በጠቅላይ ሚኒስትርነት መርተዋል።

    ቤኔት ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት የኔታኒያሁ አማካሪ ሆነው ሠርተዋል።

  16. ኢራን የኒውክሌር ቁጥጥር እንዲደረግ ባትስማማ ኖሮ ድርድር ሳይካሄድ ይቀር እንደነበር ትራምፕ ገለጹ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ኢራን ሙሉ በሙሉ እና ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የኒውክሌር ቁጥጥር እንዲደረግ ፈቅዳለች” አሉ።

    ኢራን ዓለም አቀፍ የኒውክሌር ተቆጣጣሪዎች ወደ አገሪቱ እንዲገቡ ልትፈቅድ ነው መባሉን ብታስተባብልም፤ ትራምፕ “ለከፍተኛ ደረጃ የኒውክሌር ቁጥጥር ተስማምታለች” ብለዋል።

    ይህ የኢራን ስምምነት “ለረዥም ጊዜ እና እስከ ወዲያኛው” እንደሚዘልቅ ጠቅሰው “የኒውክሌር ታማኝነትን የሚያረጋግጥ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

    “ኢራን ለዚህ ባትስማማ ኖሮ ተጨማሪ ድርድሮች አይኖሩም ነበር” በማለት አክለዋል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢስማኤል ባጋይ ከሰዓታት በፊት ዓለም አቀፍ የኒውክሌር ተቆጣጣሪዎች ወደ አገሪቱ እንዲገቡ እና የደረሰውን ጉዳት እንዲመለከቱ አለመፈቀዱን ገልጸዋል።

    የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ኢራን ለኒውክሌር ተቆጣጣሪዎች ፈቃድ መስጠቷን ተናግረዋል።

    ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ “በዚህ እና በሌሎችም ኢራን ባቀረበቻቸው ስምምነቶች መነሻነት ነው የሆርሙዝ ወሽመጥ ተከፍቶ እንዲቀጥል እንዲሁም በባሕር መተላለፊያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዳይጣል የተስማማሁት” ብለዋል።

  17. የኬንያው የጤና ሚኒስትር የኢቦላ ለይቶ ማቆያ ማዕከል ግንባታ እንዲቆም ወሰኑ

    የኢቦላ ምርመራ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የኬንያ የጤና ሚኒስትር ኤደን ዱአሌ በአሜሪካ የሚደገፈው አወዛጋቢው የኢቦላ ለይቶ ማቆያ ማዕከል ግንባታ እንዲቋረጥ ውሳኔ አሳለፉ።

    ሚኒስትሩ ውሳኔውን ከማሳወቃቸው ከአንድ ቀን በፊት ፍርድ ቤትን በመድፈር ጥፋተኛ መባላቸው አይዘነጋም።

    ዛሬ ማክሰኞ ፍርድ ቤት የቀረቡት ሚኒስትሩ ይቅርታ ጠይቀው በኛኙኪ ግዛት በሚገኝ ወታደራዊ ሰፈር የሚገነባው የኢቦላ ለይቶ ማቆያ ማዕከል “በአፋጣኝ እና ሙሉ በሙሉ እንዲቆም” ማዘዛቸውን አስታውቀዋል።

    ባለፈው ወር የመብት ተሟጋች ቡድኖች ያቀረቡትን አቤቱታ ተከትሎ የኬንያ ፍርድ ቤት 50 አልጋዎች ያሉት የለይቶ ማቆያ ማዕከል ግንባታ እንዲቆም ውሳኔ አሳልፏል።

    ሆኖም ግን ሰኞ ዕለት የዋለው ችሎት የጤና ሚኒስትሩ ትዕዛዝ ችላ ብለው ግንባታው እንዲቀጥል በመወሰናቸው ፍርድ ቤትን በመድፈር ጥፋተኛ ብሏቸዋል።

    ማዕከሉ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተቀሰቀሰው የኢቦላ ቫይረስ የተጠረጠሩ አሜሪካዊያን ለይቶ ማቆያ እንዲሆን ታስቦ ነበር።

    የጤና ሚኒስትሩ ኤደን ዱአሌ “ድርጊቴ፣ ችላ ባይነቴ፣ አለመረዳቴ ወይም የተዛባ ግንዛቤዬ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እንዳላከብር በማድረጉ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብለዋል።

    የከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኛ ፓትሪሽያ ናዩንዲ የሚኒስትሩን ይቅርታ ተቀብለው “በጥብቅ ማስጠንቀቂያ” አሰናብተዋቸዋል።

    የኢቦላ ለይቶ ማቆያ ማዕከል ግንባታ በኬንያውያን ዘንድ ቁጣ እና ተቃውሞ አስነስቷል። ፖሊስ ተቃዋሚዎችን ለመበተን ሲሞክር ሦስት ሰዎች ተገድለዋል።

  18. የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ለኢራን ጦርነት ላወጣው 80 ቢሊዮን ዶላር ጥያቄ አቀረበ

    የመከላከያ ሚኒስትር ፔት ሄግሴት
    የምስሉ መግለጫ, የመከላከያ ሚኒስትር ፔት ሄግሴት

    የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር በአብዛኛው ለኢራን ጦርነት ያወጣውን ወጪ ለመሸፈን ወደ 80 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው ለአገሪቱ ምክር ቤት አባላት አስታወቀ።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት የበጀት ጥያቄው ገና በይፋ አለመቅረቡን ቢገልጽም፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ፔት ሄግሴት ባለፉት ቀናት ወደ አሜሪካ ምክር ቤት በመሄድ ከእንደራሴዎች ጋር እየተገናኙ መሆናቸው ተዘግቧል።

    አሶሺየትድ ፕሬስ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ነገር ግን በይፋ ለመግለጽ ሥልጣን የሌላቸውን ሁለት ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ለኢራን ጦርነት የወጣውን ገንዘብ የተመለከተ ጥያቄ ባለፈው ዓመት ለምክር ቤት አባላት ቀርቧል።

    ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር ስቴፈን ፋይንበርግ በበኩላቸው ከበርካታ የምክር ቤት አባላት ጋር በቀረበው የገንዘብ ጥያቄ ላይ ከመነጋገራቸው በተጨማሪ ዝርዝሩ ለምክር ቤቱ የአስተዳደር እና የበጀት ጽህፈት ቤት መቅረቡ ተገልጿል።

    ፔንታገን በመባል የሚታወቀው የመከላከያ መሥሪያ ቤት ግን በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን ተጠይቆ ምላሽ አልሰጠም።

    ይህ የበጀት ጥያቄ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከኢራን ጋር ጦርነት ውስጥ መግባታቸውን ከተቃወሙት የምክር ቤት አባላት በአሜሪካውያን ላይ ያጋጠመውን የኑሮ ውድነት እንደምክንያት በማቅረብ ቀላል የማይባል ተቃውሞ እንደሚገጥመው ይጠበቃል።

    ግንቦት ወር ላይ በምክር ቤቱ በተካሄደው የጥያቄ እና መልስ መድረክ ላይ “በርካታ ሕዝብ ለተቃወመው ጦርነት አሜሪካውያን ለፍተው ያገኙትን ገንዘብ እያወጣችሁ ነው” በማለት ዴሞክራቷ የምክር ቤት አባል ፓቲ መሪ የመከላከያ ሚኒስትሩ ሄግሴትን መናጋራቸው ይታወሳል።

  19. የአሜሪካ ባለሥልጣናት ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ የሰው ሕይወት ባጠፋው ቴስላ መኪና ላይ ምርመራ ጀመሩ

    ቴስላ መኪና የውስጥ ክፍል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ቴስላ ሞዴል 3 እጅግ ዘመናዊ እና በራሱ መሽከርከር የሚችል ተሽከርካሪ ነው (ፎቶው አደጋው የደረሰበት መኪና አይደለም)

    የአሜሪካ የትራንስፖርት ደኅንነት ባለሥልጣናት አንድ ቴስላ መኪና በድንገት ከመንገድ ወጥቶ ከመኖሪያ ቤት ጋር በመጋጨት የአንድ ሰው ሕይወት ካለፈ በኋላ ምርመራ ማድረግ መጀመራቸው ተገለጸ።

    ባለፈው ሳምንት አርብ በአገሩ ሰዓት አቆጣጠር ምሽት ሁለት ሰዓት ቴክሳስ ግዛት ውስጥ ከመንገድ ወጥቶ አደጋ ስላደረሰው ቴስላ መኪና የአሜሪካ ብሔራዊ የመንገዶች ትራፊክ ደኅንነት አስተዳደር ሰኞ ዕለት ምርመራ ማድረግ ጀምሯል።

    በቴስላ በተገጨመው ቤት ውስጥ የነበረችው ሴት ከባድ ጉዳት ከደረሰባት በኋላ በአደጋው ምክንያት ሕይወቷ ማለፉን ፖሊስ አስታውቋል።

    ፖሊስ ጨምሮም የመኪናው ሹፌር በአደጋው ወቅት በአደገኛ ዕጽም ሆነ በአልኮል ተጽእኖ ስር አልነበረም። አሽከርካሪው ለመርማሪዎች እንደተናገረው አደጋው የደረሰው መኪናው አውቶማቲክ ሆኖ በራሱ እየተሽከረከረ በነበረበት ጊዜ ነው።

    የአሜሪካ መንገዶች ደኅንነት አስተዳደር ቃል አቀባይ እንዳሳወቀው "መሥሪያ ቤቱ በአደጋው ላይ ልዩ ምርመራ ማካሄድ ጀምሯል።”

    የዓለማችን የመጀመሪያው አሜሪካዊው ትሪሊየነር ንብረት የሆነው የዘመናዊው መኪና አምራች ቴስላ ተወካይ መንግሥት በተሽከርካሪው ላይ እያካሄደ ስላለው ምርመራ አስተያየት ቢጠየቅም ምላሽ አልሰጠም።

    የፖሊስ ሪፖርት እንደሚያመለክተው ሞዴል 3 የተባለው ቴስላ መኪና አሽከርካሪ “መኪናው ከቁጥጥሩ ውጪ ሆኖ ከመንገድ በመውጣት ከመኖሪያ ቤት ጋር በመጋጨቱ” የሰው ሕይወት ጠፍቷል።

  20. የምያንማር ጦር በስድስት ወር ውስጥ ከ700 በላይ ንጹኃንን መግደሉን የተባበሩት መንግሥታት ገለጸ

    የምያንማር ወታደራዊ መሪ መኪና ላይ

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የምያንማር ጦር ባለፈው ዓመት በምርጫ ወቅት በስድስት ወር ውስጥ ለተመዘገቡት ከ700 በላይ የንጹኃን ሰዎች ሞት ተጠያቂ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ገለጸ።

    ካለፈው ነሐሴ እስከ ጥር ድረስ ያለውን ጊዜ የሸፈነ አዲስ ሪፖርት ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው 224 ሴቶች እና 153 ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 702 ሰዎች እንደተገደሉ ከታማኝ ምንጮች ተረጋግጧል።

    ጥናቱ የሸፈነው ከአምስት ዓመት በፊት መፈንቅለ መንግሥት ያወጀው ሠራዊት ምርጫ እንደሚካሄድ ያፋ ካደረገ በኋላ ያሉትን ስድስት ወራት ነው። ምርጫው ተቃዋሚዎች በመገለላቸው ምክንያት የተጭበረበረ እንደሆነ በሰፊው ይታመናል።

    “የዓለም አቀፍ እገዛ መቀነስ የሚሊዮን ሰዎችን ስቃይ እያባባሰ ነው” ሲል ሪፖርቱ አስጠንቅቋል።

    የምያንማር ጦር በ2021 መፈንቅለ መንግሥት መካሄዱን ካወጀ በኋላ በተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ፤ ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል። ሰፊው የአገሪቱ ክፍልም በታጣቂዎች እጅ ወድቋል።

    የተመድ የሰብአዊ መብቶች ጽሕፈት ቤት ያወጣው ሪፖርት እንደሚገልጸው የአየር ጥቃት “ብቸኛው ግዙፍ የውድመት እና ስቃይ ምክንያት” ሆኖ ቀጥሏል።

    ጥቅምት ወር ላይ በተፈጸመ ጥቃት አራት ሕጻናትን ጨምሮ 23 ሰዎች ተገድለዋል። ትምህርት ቤት ፊት ለፊት ተሰብስበው 60 ሰዎች ደግሞ ተተኳሽ ሲወድቅ በፍንጥርጣሪ ተጎድተዋል።

    ታኅሣሥ ላይ ደግሞ ሠራዊቱ በሻይ ቤት ላይ በፈጸመው ጥቃት ኳስ ለመመልከት ተሰብስበው የነበሩ ቢያንስ 19 ሰዎች እንደተገደሉ እና 20 ሰዎች እንደቆሰሉ ሪፖርቱ ገልጿል።