ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደር ጣልቃ መግባት ውጥረቱን እንደሚያባብስ አስጠነቀቀች

በኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደር ውስጥ ማንኛውም ጣልቃ ገብነት ውጥረቱን እንደሚያባብስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ተናግረዋል። በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል እያለፈ የነበረ በፓናማ የተመዘገበ መርከብ ትናንት ቅዳሜ ጥቃት ከደረሰበት በኋላ አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት ፈጽማለች። የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በአጸፋ ምላሽ በኩዌት እና ባሕሬን በሚገኙ የአሜሪካ መሠረተ ልማቶች ላይ የድሮን እና ሚሳዔል ጥቃቶች ማድረሱን ገልጿል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የኡጋንዳ ጦር አዣዥ የአገሪቱ ዋነኛ መገናኛ ብዙኃን እንዲዘጉ አዘዙ

    ጄነራል ሙሆዚ ካኒሩግባ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኡጋንዳ ጦር አዛዥ እና የፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ልጅ የሆኑት ጄነራል ሙሆዚ ካኒሩግባ የአገሪቱ ዋነኛ መገናኛ ብዙኃን እንዲዘጉ ትዕዛዝ አስተላለፉ።

    የኡጋንዳ ቀዳሚው ገለልተኛ ሚዲያ “ወታደራዊ እቀባ” እንደተጣለበትም አስታውቋል።

    የጦር አዛዡ ቴሌቭዥን ጣቢያዎች፣ ጋዜጣዎች እና ራድዮ ጣቢያዎች እንዲዘጉ አዝዘዋል።

    ‘ዴይሊ ሞኒተር’ ጋዜጣ እንዳለው በዋና መሥሪያ ቤቱ የታጠቁ ወታደሮች ተሰማርተዋል። ኤንቲቪ እና ስፓርክ ቲቪ በካምፓላ ስርጭት ማቆማቸውም ተገልጿል።

    መገናኛ ብዙኃኑን የሚያስተዳድረው ‘ኔሽን ሚዲያ ግሩፕ’ በምሥራቅ አፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑት መካከል ተጠቃሽ ነው።

    መገናኛ ብዙኃኑ ለምን እንዲዘጉ እንደተወሰነ ግልጽ አይደለም።

    ሆኖም የኡጋንዳ ጦር አዛዥ በኤክስ ገጻቸው “በነጻ ሚዲያ አላምንም! መገናኛ ብዙኃን መመራት ያለባቸው በአብዮቱ ካድሬዎች ነው” ብለው ጽፈዋል።

    ተቃዋሚዎች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንደሚሉት የሙሴቬኒ ጨቋኝ አስተዳደር የሚዘወረው በጄነራል ሙሆዚ ካኒሩግባ ነው።

  2. ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደር ጣልቃ መግባት ውጥረቱን እንደሚያባብስ አስጠነቀቀች

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    በኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደር ውስጥ ማንኛውም ጣልቃ ገብነት ውጥረቱን እንደሚያባብስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ተናገሩ።

    ወደ ባግዳድ የተጓዙት አራግቺ ከኢራቅ አቻቸው ጋር በጥምረት በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ በኢራን እና አሜሪካ ስምምነት መሠረት በ30 ቀናት ውስጥ የሆርሙዝ ወሽመጥ ከጦርነቱ በፊት ወደነበረበት አስተዳደር ይመለሳል።

    “ሙሉ በሙሉ በኢራን ሥር የሚተዳደር ሲሆን፤ ብቸኛው ኃላፊነት ያለውም እስላማዊ ሪፐብሊኩ ነው” ብለዋል።

    “ማንኛውም ጣልቃ ገብነት ወይም ትይዩ ስምምነት ነገሩን ውስብስብ ያደርጋል፤ ውጥረቱን ያባብሳል፤ ቁልፉ መተላለፊያ የሚከፈትበትን ቀንም ያዘገያል” ሲሉም አክለዋል።

    አራግቺ፤ ባለፉት ሁለት ቀናት የተከሰቱ “አደጋዎች እና የተኩስ ልውውጦች ለዚህ ማሳያ ናቸው” ብለዋል።

    ባለፉት ሦስት ቀናት በሆርሙዝ ወሽመጥ ሲያልፉ የነበሩ ቢያንስ ሁለት መርከቦች ላይ ጥቃት ደርሷል። በዚህም ምክንያት አሜሪካ እና ኢራን የተኩስ ልውውጥ አድርገዋል።

  3. በካሊፎርኒያ የእንሰሳት ማቆያ ውስጥ የ117 ዉሻዎች አስከሬን መገኘቱ ተገለጸ

    መርማሪዎች በቁፋሮ ላይ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በአሜሪካ ሰሜን ካሊፎርኒያ የእንሰሳት ማቆያ ውስጥ የ117 ዉሻዎች አስከሬን መገኘቱን መርማሪዎች አስታወቁ።

    “እንሰሳት አይገደሉበትም” በተባለው ማቆያ ውስጥ አስከሬናቸው ከተገኙት ዉሻዎች አብዛኞቹ በጥይት መመታታቸው ተገልጿል።

    ‘ሚራንዳስ ሬስኪው አኒማል ሳንክችወሪ’ የተባለው ማቆያ ለእንሰሳት ጥበቃ የሚሰጥ ሲሆን፤ መርማሪዎች በቅጥር ጊቢው ያገኟቸው አስከሬኖች በጅምላ እንደተቀበሩ ይገመታል።

    ወደ 600 የሚጠጉ የዉሻ ማሰሪያዎች በሥፍራው እንደተገኙ ፖሊስ አስታውቋል።

    ፖሊስ በማጭበርበር ወንጀል እና እንሰሳት ላይ የተፈጸመ ስቅይትን በሚመለከት ምርመራ ከፍቷል።

    ከተቋሙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዉሻዎች መጥፋታቸው ተገልጿል።

    የእንሰሳት ማቆያው ባለቤት ሻኖን ሚራንዳ “ድምዳሜ ላይ ከመድረሳችሁ በፊት ሁሉንም እውነታ ማወቅ አለባችሁ” ብላለች።

    አስከሬኖቹ በመርማሪዎች ከመገኘታቸው በፊት፤ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባ እና የማኅበራዊ ሚዲያ ትርክት “ጎዶሎ እና በአንዳንድ ሁኔታዎች የተዛባ ምሥል የሚሰጥ ነው” ስትል ተናግራለች።

    ቢቢሲ ከማቆያው ባለቤት አስተያየት ጠይቋል።

    የመጠለያው ባለቤት አሁን ላይ በወንጀል ክስ አልተመሠረተባትም።

  4. ኩዌት እና ባሕሬን በኢራን የተፈጸመባቸውን ጥቃት አወገዙ

    ሆርሙዝ ወሽመጥ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኩዌት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢራን የፈጸመችው ጥቃት “ሉዓላዊነታችንን የጣሰ ነው” ሲል አወገዘ።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ባወጣው መግለጫ፤ ዋሽንግተን ለፈጸመችው ጥቃት በአጸፋው በኩዌት እና ባሕሬን በሚገኙ የአሜሪካ መሠረተ ልማቶች ላይ የድሮን እና ሚሳዔል ጥቃቶችን ማድረሱን ገልጿል።

    የባሕሬን አየር ኃይል ከኢራን የተወነጨፉ ሚሳዔሎችን ማክሸፉን እንዲሁም ድሮኖችን ማውደሙን አስታውቋል።

    “ኢራን በአደገኛ ጥቃቷ ያስወነጨፈችውን ብዙ መሣሪያ ማምከን እና ማውደም ተችሏል” ብሏል። ጦሩ “በከፍተኛ ተጠንቀቅ” ላይ እንደሚገኝም አስታውቋል።

    የኩዌት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “ኢራን በአገራችን ላይ ያደረሰችውን ተደጋጋሚ ጥቃት በጽኑ እናወግዛለን” ብሏል።

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል እያለፈ የነበረ በፓናማ የተመዘገበ መርከብ ጥቃት ከደረሰበት በኋላ አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት ፈጽማለች።

    አሜሪካ እና ኢራን የተኩስ አቁምን በመጣስ እርስ በርስ እየተካሰሱ ነው።

  5. ከስምምነት በኋላም እስራኤል በሊባኖስ ላይ ጥቃት ማድረሷ ተገለጸ

    ደቡብ ሊባኖስ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    እስራኤል እና ሊባኖስ ስምምነት ከተፈራረሙ ከአንድ ቀን በኋላ እስራኤል ጥቃት መፈጸሟ ተገለጸ።

    ሁለቱ አገራት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ስምምነት ቢፈራረሙም እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ ባደረሰችው የአየር ጥቃት አንድ ሰው መገደሉን የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

    የሊባኖስ ብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ እንደዘገበው፤ በደቡባዊ ከተማዋ ናባቲያህ አል-ፋውቃ እስራኤል የድሮን ጥቃቶች አድርሳለች። ቢያንስ ሁለት ሰዎች መጎዳታቸው ተገልጿል።

    የእስራኤል ጦር ለወታደሮቹ አደጋ የጋረጠ ግለሰብ ላይ የድሮን ጥቃት መፈጸሙን ከመግለጽ በዘለለ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።

    በአሜሪካ አሸማጋይነት እስራኤል እና ሊባኖስ የስምምነት ማዕቀፍ ቢፈራረሙም የሄዝቦላህ መሪ ስምምነቱ የሊባኖስን ሉዓላዊነት ይጥሳል ሲሉ ተችተዋል።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በዋሽንግተን የተደረሰውን ስምምነት “ታሪካዊ” እንዲሁም “ኢራን እና ሄዝቦላህን የሚያንኮታኩት” ብለውታል።

    አራት ነጥብ ባለው የስምምነት ማዕቀፍ መሠረት እስራኤል ጦሯን ከደቡብ ሊታኒ አካባቢ አስወጥታ የሊባኖስ ወታደሮች ይረከባሉ።

    እስራኤል ጦሯ በደቡብ ሊባኖስ መቆየት እንደሚችል አስታውቃለች።

    የሄዝቦላህ መሪ ናይም ቃሲም የሊባኖስ መንግሥት “ጎጂ ስምምነቶች” ላይ ደርሷል ሲሉ ኮንነዋል።

  6. አሜሪካ እና ኢራን የተኩስ አቁምን በመጣስ አንዳቸው ሌላቸውን እየከሰሱ ነው

    ሆርሙዝ ወሽመ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አሜሪካ እና ኢራን ተኩስ መለዋወጣቸውን ተከትሎ የተኩስ አቁምን በመጣስ አንዳቸው ሌላቸውን እየከሰሱ ነው።

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል እያለፈ የነበረ በፓናማ የተመዘገበ መርከብ ትናንት ቅዳሜ ጥቃት ከደረሰበት በኋላ አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት ፈጽማለች።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በንግድ መርከቦች ላይ “ትንኮሳ ስለቀጠለ” በኢራን በርካታ ዒላማዎችን መምታቱን አስታውቋል።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በአጸፋ ምላሽ በኩዌት እና ባሕሬን በሚገኙ የአሜሪካ መሠረተ ልማቶች ላይ የድሮን እና ሚሳዔል ጥቃቶች ማድረሱን ገልጿል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ባወጣው መግለጫ “ኢራን የተኩስ አቁሙን እንድታከብር ዕድል ተሰጥቷት ነበር። ጦሯ የድሮን ጥቃት በማድረስ ስምምነቱን መጣስን መርጧል” ብሏል።

    የአሜሪካ ተዋጊ ጄቶች በ10 የኢራን ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ ድብደባ ማድረሳቸውን አስታውቋል። በሆርሙዝ ወሽመጥ አቅራቢያ የተፈጸሙት ጥቃቶች የመገናኛ ሥርዓቶች፣ የአየር መከላከያዎች እና የድሮን ማከማቻ ላይ ያነጣጠሩ ናቸው ተብሏል።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ባወጣው መግለጫ፤ አሜሪካ በአምስት የባሕር ዳርቻ ይዞታዎች ላይ ጥቃድ ማድረሷን ገልጿል።

    “በኩዌት አሊ አል-ሳሊም ወታደራዊ መቀመጫ እና በባሕሬን ፊፍዝ ናቫል ፍሊት የሚገኙ ስምንት ቁልፍ መሠረተ ልማቶች ላይ የአጸፋ እርምጃ ተወስዷል” ሲልም አክሏል።

  7. ትራምፕ በቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ታክስ ምክንያት የአውሮፓ አገራት ላይ 100% ታሪፍ ለመጣል ዛቱ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዋሽንግተን ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ላይ የዲጂታል አገልግሎት ታክስ በሚጥል ማንኛውም የአውሮፓ አገር ላይ የ100 ፐርሰንት ታሪፍ እንደሚጥሉ ዛቱ።

    ፕሬዝዳንሩ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ "በርካታ የአውሮፓ አገራት" ይህንን አይነት ታክስ ስለመጣል ሲወያዩ መቆየታቸውን እና የተወሰኑት ደግሞ እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ መቃረባቸውን ገልጸዋል።

    ታክስ በሚጥሉ አገራት ላይ ወዲያውኑ የቅጣት እርምጃ እንደሚወሰድ ያስጠነቀቁት ትራምፕ፤ የቀደሙ የሁለትዮሽ የንግድ ስምምነቶችን ሙሉ በሙሉ በአጸፋ እርምጃው “እንደሚተኩም” ዝተዋል።

    ትራምፕ አክለውም፤ “ይህንን አይነቱን ታክስ የሚጥል የትኛውም አገር ወደ አሜሪካ በሚልካቸው ማንኛውም እና ሁሉም ሸቀጦች ላይ ወዲያውኑ የ100% ታሪፍ እንደሚጣል” ተናግረዋል።

    ብሪታንያ የምትጥለው የ2% የዲጂታል አገልግሎት ታክስ በዋና የኢንተርኔት ፍለጋ አገልግሎት ኩባንያዎች፣ ማኅበራዊ ሚዲያዎች እንዲሁም የኦንላይን ገበያ መድረኮች ላይ ተግባራዊ ይሆናል።

    ይህ ታክስ እንደ አፕል፣ ጎግል፣ ሜታ እና አማዞን ያሉ ትላልቅ የአሜሪካ ኩባንያዎች ላይ ተፅዕኖ አለው። ብሪታኒያ በ2024/25 በጀት ዓመት ብቻ ከዚህ የታክስ አይነት 800 ሚሊዮን ፓውንድ ሰብስባለች።

    ትራምፕ ባለፈው ሚያዝያ ላይ ዩናይትድ ኪንግደም ግዙፍ የአሜሪካ ኩባንያዎች ላይ ታክስ መጣሏን በመግለጽ "ከፍተኛ ታሪፍ" እንደሚጥሉ ተናግረው ነበር።

    ፈረንሳይ፣ ጣሊያን እና ስፔንም በአገራቸው በሚንቀሳቀሱ ግዙፍ ኩባንያዎች ላይ የ3% የዲጂታል አገልግሎት ታክስ ጥለዋል።

    ሌሎች በርካታ የአውሮፓ ህብረት አገራትም ተመሳሳይ ታክስ ተግባራዊ እንዳደረጉ ወይም ለማድረግ ማቀዳቸውን ታክስ ፋውንዴሽን የተባለው በታክስ ፖሊሲ ላይ የሰሚራ ተቋም መረጃ ያሳያል።

  8. ኢራን የአሜሪካ ጥቃት የተፈረመውን ስምምነት “በግልጽ ጥሷል” ስትል፤ ባህሬን በቴህራን ጥቃት እንደደረሰባት አስታወቀች

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሜሪካ አገሪቱ ግዛት ውስጥ የፈጸመችው ጥቃት በሁለቱ አገራት ጦርነቱን ለማቆም የፈረሙትን የመግባቢያ ስምምነት “በግልጽ የጣሰ ነው” ሲል ከሰሰ።

    ኢራን ባልተፈቀደ የሆርሙዝ ወሽመጥ ክፍል ሲጓዝ ነበር ያለቸው መርከብን መምታቷን ተከትሎ፤ የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ቴህራን ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።

    ከዚህ በኋላ መግለጫ ያወጣው የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ አሜሪካ በአገሪቱ “የባሕር ዳርቻ ቁጥጥር ተቋማት” ላይ የፈጸመችው ጥቃት የተባበሩት መንግሥታትን ቻርተር የጣሰ ነው ብሏል።

    በተጨማሪም ጥቃቱ ባለፈው ሳምንት የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት የመጀመሪያ አንቀጽ ላይ የተፈጸመ “ግልጽ ጥሰት” እንደሆነ በመግለጽ ከስሷል። የእስራኤልን ሊባኖስ ላይ ያደረሰችው ጥቃትም የመግባቢያ ስምምነቱን አንቀጽ “በግልፅ የጣሰ” እንደሆነ ገልጿል።

    “አሜሪካ በኢራን ላይ ለፈጸመችው የጥቃት እርምጃ በማንኛውም መልኩ የተባበሩ” አካላት በዚህ ምክንያት ለሚመጣው መዘዝ ተጠያቂ እንደሆኑም አስታውቋል።

    አርብ ምሽት የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ፤ የአገሪቱ ተዋጊ አውሮፕላኖች የኢራንን ሚሳዔል እና የድሮን ማከማቻዎች እንዲሁም የባሕር ዳርቻ የራዳር ተቋማትን ዒላማ ያደረገ ጥቃት መፈጸማቸውን አስታውቆ ነበር።

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ በበኩሉ የአሜሪካ ጦር ይዞታዎችን በመምታት አጸፋውን መመለሱን አስታውቋል። አብዮታዊ ዘቡ የትኛው የአሜሪካ ይዞታ ላይ ጥቃት እንደፈጸመ አልገለጸም።

    ባህሬን ግን ኢራን ግዛቷ ውስጥ የድሮን ጥቃት እንዳደረሰችባት በመግለጽ ድርጊቱን አውግዛለች። ባህሬን የግዛት አንድነቷን እና ደኅንነቷን የማስጠበቅ ሙሉ መብት እንዳላት ገልጻለች።

  9. የታንዛኒያ መንግሥት ከሦስት ዓመት በኋላ በድጋሚ ፖለቲካዊ ሰልፍ እንዳይደረግ አገደ

    ሰልፍ ላይ የተሳተፉ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የታንዛኒያ መንግሥት ተጨማሪ ትዕዛዝ እስከሚሰጥ ድረስ በመላው ታንዛኒያ ፖለቲካዊ ሰልፎችን ማድረግ የተከለከለ መሆኑን አስታወቀ። ይህ እርምጃ የተወሰደው አገሪቱን ደኅንነት ለማጠበቅ አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነ ገልጿል።

    የደኅንነት ስጋት የሆኑ ጉዳዮችን መለየቱን የገለጸው የአገሪቱ መንግሥት፤ የወንጀል ድርጊቶችን ለመፈጸም ሲያቅዱ የነበሩ ግለሰቦች የጦር መሣሪያ ይዘው መገኘታቸውን አስታውቋል።

    ተቃዋሚ ቡድኖች ዕገዳው ሕገ ወጥ እንደሆነ በመግለጽ ትችታቸውን አሰምተዋል። ‘ኤሲቲ ዋዛሌንዶ’ የተሰኘው ተቃዋሚ ፓርቲ፤ ትዕዛዙን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶ እንደሚሞግት ገልጿል።

    የታንዛኒያ መንግሥት ይህንን ውሳኔ ያስተለላፈው ባለፈው ዓመት ከተካሄደው ምርጫ በኋላ የተነሳውን ተቃውሞ በኃይል ለማፈን በተወሰደው እርምጃ ለደረሰው የሰዎች ሞት ተጠያቂነት እንዲሰፍን የሚጠይቅ ሰልፍ ሊካሄድ መታቀዱ ከተሰማ በኋላ ነው።

    በአገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ እንዲካሄድ መጠየቅም ሌላኛው የሰልፉ ዓላማ ነበር።

    የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ ተክተው ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ 2023 ላይ ለስድስት ዓመታት ተጥሎ የነበረውን የፖለቲካ ሰልፎች ዕገዳ አንስተው ነበር። የአሁኑ ውሳኔ በወቅቱ የወሰዱትን የሪፎርም እርምጃ የቀለበሰ ሆኗል።

    ፕሬዝዳንቷ በወቅቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰልፍ የማካሄድ መብት እንዳላቸው እውቅና ሰጥተው፤ “በጨዋነት” እንዲንቀሳቀሱ እና "ስድብ ከመለዋወጥ" እንዲቆጠቡ አሳስበው ነበር።

    የአሁኑን ዕገዳ ይፋ ያደረጉት የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ ፓትሮባስ ካታምቢ፤ "ትኩረታችንን ኢኮኖሚያችንን መገንባት ላይ ማድረግ አለብን" ሲሉ ለፓርላማው ተናግረዋል።

    አገሪቱ በቅርቡ የምታስተናግደውን እና "ከተለያዩ አገራት እንግዶችን እንደሚመጡ የሚጠበቅበትን” ዓለም አቀፍ የንግድ ዝግጅት በማብራሪያቸው አንስተዋል።

    "በዚህ ወቅት ማንኛውም ዓይነት ሁካታ ውስጥ የሚሳተፍ ሰውን አንታገስም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    ‘ኤሲቲ ዋዛሌንዶ’ የተባለው ተቃዋሚ ፓርቲ ግን ገዢው ‘ሲሲኤም’ ፓርቲ ተቃዋሚዎችን ለማፈን የመንግሥት ተቋማትን እየተጠቀመ ነው ሲል ከስሷል።

  10. እስራኤል እና ሊባኖስ በአሜሪካ አሸማጋይነት የስምምነት ማዕቀፍ ተፈራረሙ

    ሊባኖስ ውስጥ በተፈጸመ ጥቃት የወደመ ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በአሜሪካ አሸማይነት ለበርካታ ቀናት ዋሽንግተን ድርድር ሲያካሂዱት የነበሩት እስራኤል እና ሊባኖስ፤ የስምምነት ማዕቀፍ ላይ ተፈራረሙ።

    የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እንደገለጹት አሁን በተፈረመው ስምምነት አማካኝነት ዘላቂ ሰላም እና ደኅንነትን ለማስፈን የሚያስችል ማዕቀፍ መዘጋጀት ይጀምራል።

    ሁለቱ አገራት መፈራረማቸው የተሰማው፤ በእስራኤል ኃይሎች እና በኢራን በሚደገፈው ሄዝቦላህ ተግባራዊ እየሆነ ያለው ተኩስ አቁምን ወደ ጎን በማለት ደቡብ ሊባኖስ ውስጥ የተወሰነ ውጊያ ማድረግ በቀጠሉበት ወቅት ነው።

    የእስራኤል ጋር እየተዋጋ ያለው ሄዝቦላህ አርብ ዕለት የተፈረመው ስምምነት አካል አይደለም። ቡድኑ በስምምነቱ አማካኝነት በደቡብ ሊባኖስ ከሚገኘው ደቡብ ሊታኒ አካበቢ ለማስወጣት ይስማማ እንደሆን ግልጽ አይደለም።

    አሜሪካ፤ በእስራኤል እና ሄዝቦላ መከካል ያለው ውጥረት ከኢራን ጋር የተደረገውን የሰላም ስምምነት ሊያደናቅፍ ይችላል የሚል ስጋት ገብቷታል።

    ከአሜሪካ ጋር በተፈረመው ስምምነት ላይ ኢራን ሊባኖስን ጨምሮ "በሁሉም ግንባሮች" ውጊያ እንዲቆም ያቀረበችው ጥያቄ ተግባራዊ እንደሚሆን ቃል ተገብቶላታል።

    እስራኤል እና ሊባኖስ በተፈራረሙት ባለ 14 ነጥብ የማዕቀፍ ስምምነት ላይ አንዳቸው ሌላኛቸው "በሰላም የመኖር" መብት እንዳለው "ማረጋገጫ" ሰጥተዋል። "እንደ ተጎራባች ሉዓላዊ አገራት በደኅንነት ለመኖር ያላቸውን የጋራ ፍላጎትም" ገልጸዋል።

    ሁለቱ አገራት "በዓለም አቀፍ የፖለቲካ ወይም የሕግ መድረኮች ላይ የሚደረጉ ማናቸውንም ጠበኛ ወይም የጠላትነት ድርጊቶች ለማቆምም" ተስማምተዋል። እስረኞችን ለመልቀቅ እና የሞቱ ሰዎችን ማንኛውም ቅሪት አሳልፎ ለመስጠትም ቃል ገብተዋል።

    ይሁን እንጁ ሁለቱም መንግሥታት የተፈረመው “ማዕቀፍ ራሳቸውን የመከላከል ተፈጥሯዊ መብታቸውን ከመጠቀም እንደማያግዳቸው" ዕውቅና ሰጥተዋል።

    ስምምነቱ እንደሚገልጸው "መንግሥታዊ ያልሆኑ ታጣቂ ቡድኖች ትጥቅ መፍታታቸው እና ተያያዥ መሠረተ ልማቶች መፍረሳቸው እስኪረጋገጥ ድረስ" የሊባኖስ ጦር ኃይሎች በሁሉም የሊባኖስ ግዛቶች ውስጥ ሉዓላዊ ሥልጣን ይኖራቸዋል።

    ይህንን ዕቅድ ለማሳካት ሲባል ሊባኖስ “በአሜሪካ መሪነት” የዓለም አቀፍ እና “በተለይም የአረብ አጋሮችን” ድጋፍ ትጠይቃለች።

    ማዕቀፉን ለማስፈጸም እንዲቻልም በአሜሪካ የሚደገፍ ወታደራዊ የቅንጅት ቡድን እንደሚቋቋምም ተገልጿል።

  11. አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት መፈጸሟን ስትገልጽ፣ ኢራን አጸፋ መመለሷን አስታወቀች

    መርከብ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ባልተፈቀደ መስመር ሲጓዝ ነበር ያለችውን መርከብ ከመታች በኋላ የአሜሪካ ጦር ኢራን ውስጥ ጥቃት መፈጸሙን ሲገልጽ ኢራን ደግሞ በምላሹ የአሜሪካ ይዞታዎችን ማጥቃቷን አስታወቀች።

    የአሜሪካ ጦር ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ አርብ ዕለት በኢራን የሚሳዔል እና የድሮን ማከማቻ እንዲሁም የባሕር ጠረፏን በምትቆጣጠርባቸው የራዳር ማዕከላት ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።

    እርምጃው በሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት ለረጅም ጊዜ ቆመው የነበሩ መርከቦችን የማስወጣት ሥራ እንዲቆም ላደረገው እና ኢራን በአንድ የጭነት መርከብ ላይ ሐሙስ ዕለት ለፈጸመችው ጥቃት ምላሽ መሆኑ ተገልጿል።

    ኢራን ግን የጭነት መርከቡ የተመታው ወሳኙን የባሕር መተላለፊያ ለማቋረጥ ባልተፈቀደ መስመር በመጓዙ ምክንያት መሆኑን ገልጻለች።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ኢራን ላይ የፈጸመውን ጥቃት “ኃይለኛ ምላሽ” ሲል ገልጾታል። “የኢራን ኃይሎች በጭነት መርከብ ላይ የፈጸሙት ተቀባይነት የሌለው ጥቃት በግልጽ የተኩስ አቁሙን የሚጥስ ነው” ብሏል ባወጣው መግለጫ።

    "በተጨማሪም በወሳኙ ዓለም አቀፍ የንግድ መስመር በኩል የሚተላለፉት መርከቦች ቁጥር እየጨመረ ባለበት ጊዜ የኢራን አደገኛ ባህሪ የባሕር ላይ እንቅስቃሴን የሚያደናቅፍ ነው” ብሏል።

    ወታደራዊ ዕዙ እንዳለው የአሜሪካ ጦር “በሆርሙዝ በኩል የሚተላለፉ የንግድ መርከቦች በሰላም እንዲያልፉ የሚያስችል ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል።”

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ባወጣው መግለጫ አሜሪካ “መርከቦች በሆርሙዝ ላይ ከተፈቀደው መስመር ውጪ መጓዛቸውን እና የተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረብ” በአገሪቱ የባሕር ዳርቻዎች ላይ የአየር ጥቃት ፈጽማለች ብሏል።

    አብዮታዊ ዘቡ ዝርዝር መረጃ ሳይሰጥ ለተፈጸመው ጥቃት በአካባቢው በሚገኙ የአሜሪካ ይዞታዎች ላይ የአጸፋ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል። ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ከአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት መልስ ለማግኘት ጥያቄ አቅርቧል።

    በተጨማሪም "ጥቃቱ የሚደገም ከሆነ ምላሻችን ከአሁኑ የበለጠ ይሆናል” ሲል የኢራን አብዮታዊ ዘብ አስጠንቅቋል።

    ለወራት ተዘግቶ የቆየው የሆርሙዝ ወሽመጥ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ ተከፍቶ መርከቦች ከአካባቢው መውጣት ጀምረዋል።

  12. ኢራን የባሕረ ሰላጤው አገራት እና አሜሪካ ያወጡትን መግለጫ ተቃወመች

    ማርኮ ሩቢዮ በምሽት ወደ አውሮፕላን ሲያመሩ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በስብሰባው ላይ ተሳታፊ ነበሩ

    ኢራን የባሕረ ሰላጤው ትብብር ምክር ቤት አባል አገራት እና አሜሪካ በጋራ ያወጡት መግለጫን “ጣልቃ ገብነት፣ ኃላፊነት የጎደው እና ጠብ ጫሪ” ስትል አወገዘች።

    ባህሬን ውስጥ የተካሄደውን ስብሰባ ተከትሎ የወጣውን መግለጫ በመቃወም ኢራን በሰጠችው ምላሽ የአሜሪካ ጦር ሠራዊት በባሕረ ሰላጤው አካባቢ መገኘቱ ለአካባቢው አለመረጋጋት እና ክፍፍል ምክንያት ነው ብሏል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው አሜሪካ እና አስራኤል ለፈጸሙት ጥቃት በቀጣናው ያሉትን የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን መጠቀማቸው ዋሽንግተን ለአካባቢው ደኅነንት ግድ እንደሌላት ያሳያል።

    ጨምሮም የሆርሙዝ ወሽመጥን የማስተዳደሩ ጉዳይ በኢራን እና በኦማን መካከል በሚኖር ትብብር እንዲሁም ከአሜሪካ ጋር በተደረሰው የመግባቢያ ሰነድ አማካኝነት የሚፈጸም መሆኑን አመልክቷል።

    ሐሙስ ዕለት በተካሄደው የባሕረ ሰላጤው አገራት ትበብር ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የተገኙ ሲሆን፣ በቀጣናው ባለው ውጥረት ላይ ተወያይቷል።

    ከስብሰባው በኋላ በወጣው የጋራ መገግለጫ ላይ አባል አገራቱ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረሰውን ስምምነት የተቀበሉት ሲሆን፣ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የበላይነት ለመያዝ እንዲሁም መርከቦችን ለማስከፈል ያሚታሰብ የትኛውንም ፖሊሲ ተቃውመዋል።

    ባህሬን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኳታር፣ ኦማን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ኩዌት የባሕረ ሰላጤው አገራት ትብብር ምክር ቤት አባላት ናቸው።

  13. በቬንዙዌላ የመሬት መንቀጥቀጥ የሞቱ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ መጨመሩ ተገለጸ

    በመሬት መንቀጥቀጡ የወደመ ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በቬንዙዌላ በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ወደ 589 መድረሱን እና 2,980 ሰዎች መጎዳታቸውን የአገሪቱ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዴልሲ ሮዴሪጌዝ አስታወቁ።

    በፍርስራሾች ውስጥ ያሉ ሰዎችን ለማውጣት የሚደረገው ጥረት በቀጠለበት በአሁኑ ጊዜ ከተለያዩ አገራት እርዳታ ወደ ቬንዙዌላ እየገባ ነው።

    አሜሪካ ትናንት ሐሙስ ከፍተኛ መጠን ያለው እርዳታ ወደ አገሪቱ መላኳን ስታሳውቅ።ከስዊትዘርላንድ የተላኩ ሰማንያ የነፍስ አድን ሠራተኞች እና 18 ቶን ቁሳቁሶች ቬንዙዌላ መድረሳቸውን የአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘገበ።

    የቬንዙዌላ ቴሌቪዥን እንደዘገበው ከሆነ፣ ቡድኑ ዓርብ ማለዳ ላይ የደረሰ ሲሆን፣ ስምንት አነፍናፊ ውሻዎችም የተካተቱበት ነው።

    አክሎም፣ ከመሬት መንቀጥቀጡ ክስተት በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ በመስጠት ስዊትዘርላንድ ከመጀመሪያዎቹ አገራት መካከል መሆኗን ገልጿል።

    ከሜክሲኮም እንዲሁ ቁሳቁሶችን የያዙ የነፍስ አድን ሠራተኞች ወደ አገሪቱ መድረሳቸውን የቬንዙዌላ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ዴልሲ ሮድሪጌዝ ገልጸዋል።

    የዩናይትድ ስቴትስ ደቡባዊ ዕዝ ደግሞ አንድ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣኑ የዕዙን የድጋፍ ጥረት ለመከታተል መድረሳቸውን አስታውቋል።

  14. ኢራን ከዕውቅናዋ ውጪ በሆርሙዝ በኩል የሚደረጉ ጉዞዎች አደገኛ እንደሚሆኑ አስጠነቀቀች

    መርከብ

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚደረግ የመርከቦች እንቅስቃሴ በሙሉ ከኢራን ጋር በመቀናጀት ካልተደረገ ደኅንነቱ አስተማማኝ እንደማይሆን የኢራን ባለሥልጣን አስታወቁ።

    የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዚም ጋሪባባዲ እንደተናገሩት በሆርሙዝ በኩል የሚደረግ ጉዞ ከኢራን ዕውቅና ውጪ ከሆነ ዋስትና እንደማይኖረው በማመልከት የትኛውም በመተላለፊያው ላይ የሚከፈት የባሕር መስመር ከኢራን ጋር በመቀናጀት ካልሆነ ዕግድ እንደሚጣልበት አስጠንቅቀዋል።

    ባለሥልጣኑ ይህንን ማስጠንቀቂያ በኤክስ ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት ኦማን ከተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የባሕር ትራንስፖርት ድርጅት ጋር በመሆን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ጊዜያዊ የመርከቦች የመተላለፊያ መስመር መክፈቷ ከተገለጸ በኋላ ነው።

    ቀደም ሲል ኢራን አዲስ ያቋቋመችው የሆርሙዝ ወሽመጥ እንቅስቃሴን የሚቆያጠረው ባለሥልጣን ዕውቅና ባልተሰጠው የባሕሩ ክፍል በኩል የሚተላለፉ መርከቦች ላይ ለሚያጋጥሙ ችግሮች ኃላፊነቱን የመርከቦቹ ካፒቴኖች እና የመርከቦቹ ባለቤቶች የሚወስዱ ይሆናል በማለት አስጠንቅቆ ነበር።

    የተባበሩት መንግሥታት መውጫ አጥተው በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ለወራት የቆዩ መርከቦችን ለማሳለፍ በከፈተው መንገድ ጉዞ በጀመረ መርከብ ላይ ሐሙስ ዕለት ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ እንቅስቃሴዎች ተገትተዋል።

    ጥቃቱ የተፈጸመው የኢራን አብዮታዊ ዘብ በተባበሩት መንግሥታት የተከፈተው አዲስ የመርከቦች መተላለፊያ መስመር ከኢራን ዕውቅና ውጪ መሆኑን በማመልከት “ተቀባይነት የሌለው እና ሙሉ ለሙሉ አደገኛ” መሆኑን ካሳወቀ በኋላ ነው።

    የብሪታኒያ የባሕር ላይ ጉዞ ደኅንነት ተቋም ሐሙስ ዕለት እንዳለው መርከቡ ከኦማን ወደብ ደቡብ ምሥራቅ ላይ “ምንነቱ ባልታወቀ ተወንጫፊ” መመታቱን እና በሰው ላይ ጉዳት አለመድረሱን አስታውቋል።

    ኢራን በመርከቡ ላይ ጥቃቱን መፈጸሟን የአሜሪካ ባለሥልጣናት መናገራቸውን የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

  15. የተመድ የአቶሚክ ኃላፊ ለኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም “እጅግ ጠንካራ” የማረጋገጫ ስርዓት ያስፈልጋል አሉ

    የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤነርጂ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤነርጂ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ከመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ማብቃት በኋላ ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ እንዳይኖራት ለማረጋገጥ እንዲቻል “እጅግ ጠንካራ” የማረጋገጫ ስርዓት መዘርጋት እንዳለበት ተናገሩ።

    ጃፓን ውስጥ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ራፋኤል ግሮሲ፤ አሜሪካ እና ኢራን የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት የሚመሩት ተቋም ወደ የቴህራን የኒውክሌር ጣቢያዎች እንዲገባ ይፈቅዳል የሚል አቋማቸውን በድጋሚ ገልጸዋል።

    ይህንን አቋም ውድቅ ያደረገችው ኢራን፤ ከአሜሪካ ጋር የመጨረሻ ስምምነት እስከሚደረስ እና ማዕቀቦች እስከሚነሱ ድረስ ተቆጣጣሪዎች ወደ ቁልፍ የኒውክሌር ጣቢያዎች እንዲገቡ እንደማትፈቅድ ገልጻለች።

    ዋና ዳይሬክተሩ ግሮሲ ጃፓን ውስጥ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ይህ ስምምነት ነው፤ ስምምነቱን ለማስፈጸም ደግሞ የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤነርጂ ተቋም ሊፈቀድለት እና ምርመራ ሊያካሄድ ይገባል። በቅርቡ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

    ግሮሲ፤ በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት “ዓላማው ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ ወደማምረት እንደማትሻገር ማረጋገጥ ይመስለኛል። የኢራን መንግሥት ይህ ዓላማ እንደሌለው በግልጽ አስታውቋል” ሲሉም ተናግረዋል።

    አክለውም ግን “እርግጥ ነው ዓላማን መግለጽ ብቻውን በቂ አይደለም። ተግባራዊ ሊሆን በሚችል መልኩ በተቻለ ፍጥነት እጅግ ጠንካራ የማረጋገጫ ስርዓት መዘርጋት ያስፈልገናል” ብለዋል።

    ኢራን ለአሁኑ የዋና ዳይሬክተሩ አስተያየት ምላሽ አልሰጠችም። ከዚህ ቀደም ግን የኒውክሌር ጉዳይ በሁለት ወራት ውስጥ ይደረሳል ተብሎ የሚጠበቀው የመጨረሻ ስምምነት እስከሚፈረም ድረስ እንደሚዘገይ ገልጻለች።

  16. በፈረንሳይ የተከተሰውን ከፍተኛ ሙቀት ተከትሎ ፓሪስ ውስጥ የመጠጥ ሽያጭ ላይ ዕገዳ ተጣለ

    ፊቷ ላይ በረዶ የምታደርግ እና ሌላ ሴት ተቀምጠው

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የፈረንሳይ ባለሥልጣናት በአገሪቱ በተከሰተው ከፍተኛ ሙቀት ምክንያት በሆስፒታሎች ውስጥ የሚፈጠረውን ጫና ለመቀን ሲሉ በዋና ከተማዋ ፓሪስ ውስጥ የአልኮል መጠጥ አጠቃቀም እና ሽያጭ ላይ ዕገዳ ጣሉ።

    የፓሪስ ከተማ ነዋሪዎች ከረቡዕ ከሰዓት እስከ ቅዳሜ ጠዋት ድረስ በሕዝብ ቦታዎች አልኮል እንዳይጠጡ ተከልክለዋል። ይህ ዕግድ ቅዳሜ እና እሁድ በተመሳሳይ ሰዓትም ተግባራዊ እንደሚሆን ተገልጿል።

    ከአርብ እስከ እሁድ ባሉት ዕገዳ በተጣለባቸው ሰዓታት ውስጥ መጠጥ ገዝቶ መንቀሳቀስም ተከልክሏል። ፈቃድ ያላቸው ባሮች እና ሬስቱራንቶች ግን ከዚህ ዕገዳ ውጪ ናቸው ተብሏል።

    ስፔን፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይን ያስጨነቀው የሙቀት ማዕበል ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ እየዞረ መሆኑ ተነግሯል። ጀርመን እና ቼክ ሪፐብሊክ እጅግ ከባድ ሁኔታ ሊገጥማቸው እንደሚችል የአየር ትንበያ ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል።

    ፈረንሳይ ውስጥ የሆስፒታሎችን ዝግጁነት ለማጠናከር እና ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን ለመጠበቅ ሲባል የጤና ስጋት ምጣኔው ወደ ከፍተኛ ደረጃ ከፍ መደረጉን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሴባስቲያን ሌኮርኑ ተናግረዋል።

    ረቡዕ በፈረንሳይ ለተከታታይ ሁለተኛ ቀን ከፍተኛ ሙቀት የተመዘገበበት ዕለት ሆኗል። የሙቀት ክብረ ወሰኑም መሰበር ቀጥሏል። ረዕቡ ምሽት አማካይ የሙቀት መጠኑ ቢያንስ 22 ሴሊሺዬስ እንደደረሰ ተመዝግቧል።

    በአገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ የሆነ የሙቀት መጠን ከተመዘገበ በኋላ የፈረንሳይ ባለሥልጣናት ሕዝቡ ልማዱን እንዲያስተካክል አሳስበዋል። ወጣቶች እና አረጋውያን ተጋላጭ እንደሆኑም ተገልጿል።

  17. በሆርሙዝ የጭነት መርከብ ላይ ጥቃት በመድረሱ ተመድ ባሕርተኞችን ለማስወጣት የያዘውን እቅድ ገታ

    በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚጓዙ መርከቦች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በወሳኙ የባሕር መተላለፊያ ሆርሙዝ በኩል ስታልፍ በነበረ አንድ የጭነት መርከብ ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ፤ የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የማሪታይም ድርጅት በወሽመጡ ማለፊያ አጥተው የቆዩ ከ11,000 በላይ ባሕርተኞችን ለማስወጣት የያዘውን እቅድ በጊዜያዊነት አቆመ።

    ከዚህ ጥቃት አስቀድሞ በርካታ ጀልባዎች ማለፋቸውን የገለጹት የተቋሙ ዋና ኃላፊ አርሴኒዮ ዶሚንጌዝ፤ ሌሎች ጉዞዎችን ለማድረግ ግን በቅድሚያ “አስፈላጊው የደኅንነት ማረጋገጫ” መኖሩ ሊረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።

    የብሪታንያ የባህር ላይ የደህንነት ተቋም ትናንት ሐሙስ ባወጣው መረጃ፤ በኦማን ከሚገኘው የዳሂት ወደብ በስተደቡብ ምስራቅ 7.5 ኖቲካል ማይል ርቀት ላይ አንዲት መርከብ “ምንነቱ ባልታወቀ ተተኳሽ” መመታቷን አስታውቋል። በዚህ ጥቃት በሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ አልተገለጸም።

    ቫንጋርድ የተባለው የማሪታይም የስጋት አስተዳደር ተቋም ደግሞ ‘ኤቨር ላቭሊ’ የተባለችው ይህቺ በሲንጋፖር ባንዲራ የምትንቀሳቀስ መርከብ ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላም ጉዞዋን መቀጠሏን አስታውቋል።

    የአሜሪካ ባለስልጣናት፤ ኢራን መርከቧ ላይ ጥቃት ፈጽማለች ማለታቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስተዳደር ያቋቋመችው መስሪያ ቤት በበከሉ ከተቀመጡት መስመሮች ውጭ የሚጓዙ መርከቦች ደኅንነቱ የተጠበቀ ጉዞ የማድረግ ማረጋገጫ እንደማይኖራቸው አስጠንቅቋል።

    የፋርስ ባሕረ ሰላጤ ወሽመጥ ባለስልጣን በኤክስ ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍ፤ "ከተፈቀዱት መንገዶች ውጭ በመጠቀም ምክንያት ለሚፈጠር ማንኛውም መዘዝ ኃላፊነቱ የመርከቡ ባለቤት፣ ኦፕሬተር እና ዋና ኃላፊ ይሆናል" ብሏል።

    አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር እያደረጉ ባለው ጦርነት የተነሳ ከየካቲት አንስቶ በመቶዎች የሚቆጠሩ መርከቦች እና በሺህዎች የሚቆጠሩ ባሕርተኞች በፋርስ ባሕረ ሰላጤ መውጫ አጥተው ቆመዋል።

    የተባበሩት መንግሥታት ማክሰኞ ዕለት እነዚህን መርከበኞች የማስወጣት እቅዱን ይፋ ያደረገው የሆርሙዝ ወሽመጥ በድጋሚ መከፈቱን ተከትሎ ነበር።

    ኢራን፣ ኦማን፣ አሜሪካ እና ሌሎች የባሕር ዳርቻው አገራት እንዲሁም የማሪታይም ኢንዱስትሪው የዚህ “ግዙፍ ኦፕሬሽን” ተባባሪዎች እንደሆኑ የተቋሙ ኃላፊ ዶሚኒጌዝ ገልጸው ነበር።

    አሁን የጭነት መርከቧ ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ባወጡት መግለጫ ግን፤ “የተቀናጀ አካሄድ እና የጉዞ ደኅንነትን ለማረጋገጥ ሲባል ተጨማሪ ግልጽነት እስከሚኖር ድረስ የማስወጣት እቅዱ በጊዜያዊነት ይቆማል" ብለዋል።

  18. ኢራን በሆርሙዝ የሚያልፉ መርከቦችን ለማስከፈል ያላት ፍላጎት አደገኛ መሆኑን አሜሪካ አስጠነቀቀች

    በሆርሙዝ ላይ መርከቦች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን ለማስከፈል ያላት ፍላጎት ወደ ሌሎች የባሕር ላይ መተላለፊያዎች በመስፋፋት “ከባድ ቀውስ” ይፈጥራል ሲሉ አስጠነቀቁ።

    “የዓለም አቀፍ የባሕር መተላለፊያዎች የትኛውም አገር ንብረት አይደሉም። ይህም የዓለማችን መሠረታዊ መርኅ ሲሆን፣ ከዚያ ውጪ ቢሆን ኖሮ ግን ዓለማችን ሙሉ ለሙሉ በቀውስ ትታመስ ነበር” ሲሉ ባህሬን ውስጥ እየተካሄደ ባለው የባሕረ ሰላጤው አገራት የትብብር ምክር ቤት ስብሰባ ላይ መናገቸራውን ኤኤፍፒ ዘግቧል።

    “አገራት በአቅራቢያቸው ያሉ ዓለም አቀፍ የባሕር ላይ መተላለፊያዎችን በመቆጣጠር ገንዘብ ማስከፈል እንደሚችሉ ከተቀበልን፣ ይህ እንደ ወረርሽኝ በመላው ዓለም ይስፋፋል” በማለት ሩቢዮ አስጠንቅቀዋል።

    አሜሪካ እና አስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት መክፈታቸውን ተከትሎ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ከመዝጋቷ ባሻገር መተላለፊያውን በመቆጣጠር መርከቦች ክፍያ እንዲፈጽሙ የሚያስገድድ ሕግ አዘጋጅታለች።

    ነገር ግን ጦርነቱን ባስቆመው ከአሜሪካ ጋር በተደረሰው የመግባቢያ ሰነድ ላይ ሆርሙዝ ያለክፍያ ለሁሉም መርከቦች ክፍት እንደሚሆን ከስምምነት ቢደረስም ኢራን ግን ወሽመጡን ለመቆጣጠር የሚያስችላትን እርምጃ እየወሰደች ነው።

  19. በ3 ቀናት 57 የጭነት መርከቦች ከሆርሙዝ መውጣታቸውን ተመድ አስታወቀ

    ነዳጅ ጫኝ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የተባበሩት መንግሥታት የባሕር ትራንስፖርት ድርጅት መረጃ በሆርሙዝ መዘጋት ምክንያት መውጫ አጥተው ከቆዩ መርከቦች መካከል ባለፉት ሦስት ቀናት 57 መርከቦች እና 1,100 ሠራተኞቻቸው ማለፋቸውን አስታወቀ።

    ከሆርሙዝ መከፈት በኋላ ለወራት የቆሙ በርካታ መርከቦች እና ከ11 ሺህ በላይ ሠራተኞቻቸው ከአካባቢው መውጣት ከጀመሩበት ካለፈው ሰኞ ወዲህ ምን ያህል መርከቦች መንቀሳቀሳቸውን ድርጅቱ መረጃ ሲያጋራ የመጀመሪያው ነው።

    ዓለም አቀፉ የባሕር ትራንስፖርት ድርጅት መርከቦችን እና ሠራተኞቸቻውን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል እንዲያልፉ የማድረጉ ሥራ በአሜሪካ እና በአካባቢው አገራት ቅንጅት የሚካሄድ መሆኑን ገልጿል።

    ድርጅቱ ባሠራጨው መረጃ ዛሬ ሐሙስ ጠዋት ላይ 12 መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ማለፋቸውን፣ ትናንት ረቡዕ 32፣ ማክሰኞ ደግሞ 13 መርከቦች ከባሕረ ሰላጤው አካባቢ ውጥተዋል።

    ከእነዚህ መርከቦች መካከል የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ንብረት የሆነችው ኤምቪ ጊቤ መርከብ ከወራት ቆይታ በኋላ ሐሙስ ዕለት ከሆርሙዝ ወሽመጥ መውጣቷን ድርጅቱ አስታውቋል።

  20. የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እናት አረፉ

    ወ/ሮ አዳነሽ በርሄ
    የምስሉ መግለጫ, ወ/ሮ አዳነሽ በርሄ

    የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እናት ወ/ሮ አዳነሽ በርሄ በ97 ዓመታቸው ማረፋቸውን የአገሪቱ ማስታወቂያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ከኤርትራ ነጻነት አንስቶ ከ35 ዓመታት በላይ በብቸኝነት ኤርትራን እየመሩ ያሉት የ80 ዓመቱ አዛውንት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ እናት ያረፉት ሰኞ ዕለት ነበር።

    ትናንት ረቡዕ ሰኔ 17/2018 ዓ. ም. አሥመራ አቅራቢያ በሚገኘው የትውልድ ስፍራቸው በተፈጸመው ቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ፕሬዝዳንት ኢሳያስን ጨምሮ ቤተሰቦች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ከፍተኛ ባለሥልጣናት መገኘታቸውን የማስታወቂያ ሚኒስቴሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ አመለክቷል።

    የፕሬዝዳንት ኢሳያስ እና ወ/ሮ አዳነሽ በርሄ ከአቶ አፈወርቂ አብርሃ ጋር በትዳር በቆዩባቸው ጊዜያት 14 ልጆችን ያፈሩ ሲሆን፣ ዘጠኙ ለነጻነት በተካሄደው እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳተፊ እንደነበሩ ይነገራል።

    ወ/ሮ አዳነሽ በኤርትራ ውስጥ ጦርነቱ በሚካሄድበት ወቅት ወደ አሜሪካ ሄደው የኖሩ ሲሆን፣ ኤርትራ ነጻ አገር ስትሆን ተመልሰው እስከ ኅልፈታቸው ድረስ በኤርትራ ኖረዋል።